‹‹ጣይቱ
ፀሐይቱ
ደማቂቱ
ጣይቱ!…
ብቸኛይቱ
በቅኔ
ተካዥቱ፤
የሩቅ አስተዋይቱ፣
ጠበብቲቱ
ጣይቱ፡፡››
ይህ ዜማዊ ግጥም ለጉልላትዋ ለግርማዊት እቴጌ ጣይቱ (1832-1910) የተቀኘው ጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ነበር፡፡ ያቺ አዲስ አበባ ከተማን ለፈጠረች፣ ያቺ በዓድዋው የጦር አውድማ ሁነኛ ሥፍራ ለነበራት እቴጌ ጣይቱ ብጡል ባለቅኔው የተቀኘላት ‹‹ምኒልክ›› በተሰኘው ተውኔቱ ላይ ነበር፡፡ ተውኔቱ ለአሜሪካ የቴአትር መድረኮች የበቃውን ያህል የአዲስ አበባን መድረኮች እየናፈቀ ቢገኝም፡፡
የ1888 ዓ.ም. የየካቲት 23 ቀን (ማርች 1 ቀን 1896) የዕለተ ሰንበቱ የዓድዋ ድል ሲነሳ ከቅድመ ዓድዋ ጦርነቶች ከተድዓሊ (ዶግዓሊ) እስከ አምባላጀ ድረስ በተደረጉ የኢትዮጵያውያን የበላይነት ከታየባቸው የጦር አውድማዎች ታላላቅ እርመኛ አርበኞች ከነራስ አሉላ፣ ራስ መንገሻ ዮሐንስ አንስቶ እንደሚዘረዘሩት ሁሉ ከዓድዋ በፊት ከመቐለው ጥይት አልባ ጦርነት ስኬት ውኃን በመንፈግ በኢጣሊያ ላይ ከተገኘው ድል አንስቶ የእቴጌ ጣይቱ ብርሃን ዘኢትዮጵያ የሩቅ አስተዋይነት ጠቢባዊትነት ጎልቶ ይታያል፡፡
በ120ኛው ዓመት የዓድዋ ድል መታሰቢያ አጋጣሚ ‹‹ብርሃን ዘኢትዮጵያ›› (የኢትዮጵያ ብርሃን) የተሰኘ ቅጥያ ስላላቸው እቴጌ ጣይቱ ማንነት እናነሳለን፡፡
እቴጌ ጣይቱ ሲገለጹ
በአንድ ጥናታዊ ሐተታቸው የታሪክ ምሁሯ ዶ/ር ኄራን ሠረቀብርሃን እንደገለጹት፣ ጣይቱ ብጡል በ1832 ዓ.ም. አካባቢ መወለዳቸው፣ የትውልድ አካባቢያቸው በአባታቸው በብጡል ኃይለ ማርያም በኩል ሲቆጠር እስከ ስሜን አገረ ገዢ ሔሎስና ባለቤታቸው የአፄ ሱስንዮስ ሴት ልጅ እንደሚደርስ፣ በጣይቱ ሴት አያት በወ/ሮ ሒሩት ጉግሳ በኩልም የትውልድ ሐረጋቸው እስከ የጁው ኦማር ሼህ ይቆጠራል፡፡
በ40 ዓመት ዕድሜያቸው ምኒልክን ያገቡት ጣይቱ ለንጉሡ ሦስተኛ ሚስታቸው ነበሩ፡፡ በሁለቱ ጋብቻ ወቅት ምኒልክ የሸዋ ንጉሥ እንደነበሩና የጣይቱ የትውልድ ዘርና ማንነት ወደፊት አፄ ለመሆን ለሚያቅዱት ምኒልክ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው ስለ እቴጌ ጣይቱ ታሪክ  ሲወሳ ‹‹ምኒልክ ይረሳሉ ወይም ያንሱብናል›› በሚል አስተሳሰብ መኖሩን ጠቁመው ነገሩ በሌላ በኩል ያለውን አንድምታ እንደሚከተለው ይገልጹታል፡፡
የምኒልክ ጣይቱን ማግባት የሳቸውን ተራማጅ አስተሳሰብና የሴቶችም አስተዋጽኦ ተቀባይነት እንደነበረው ያመላክታል፡፡ ምኒልክ ከጣይቱ በፊት ያገቧቸው ወ/ሮ ባፈናም እንዲሁ ተሰሚነት የነበራቸው፣ ከወቅቱ ከምኒልክ ዘመድ ከመሸሻ ሰይፉ ጋር በመሆን በ1870 ዓ.ም. አካባቢ ሸዋ ውስጥ የመንግሥት ግልበጣ ሙከራ ያደረጉ ሴት ነበሩ፡፡ ልጆቻቸውንና ዘመዶቻቸውን እየሾሙ፣ በጋብቻ እያስተሳሰሩ ቆይተው በመጨረሻ የግልበጣው ሙከራ ስላልተሳካ ግዞት እንዲላኩ ተፈርዶባቸው ነው ከምኒልክ ጋር የተለያዩት፡፡ የወ/ሮ ባፈና እና የእቴጌ ጣይቱ መመሳሰል ምኒልክም ምን ዓይነት ሴቶችን እንደሚመርጡ በዚህ ማስተዋል ይቻላል፡፡
በእቴጌ ጣይቱ ዘመን ከዚያም ቀደም ብሎ በነበረው ሁኔታ አንዱ ትልቁ የፖለቲካ ማራመጃ ጋብቻ ነበር፡፡ ወሎ፣ ዋግ፣ ወረሼህ፣ የጁ፣ ጎንደር፣ ጎጃም፣ ትግራይ፣ ሸዋ፣ ስሜን፣ በሰተኋላም ወለጋንና ከፋን ጨምሮ፣ የንጉሣዊ ቤተሰቦች ጋብቻ አገሪቷን ለማስተሳሰርና የአንድነት ስሜት ለመፍጠር ዋና አስተዋጽኦ ነበረው፡፡
ጣይቱ እቴጌ ሆነው ከነገሡ በኋላ፣ ‹‹የሸዋ መርፌ›› የሚል ስያሜ ሊሰጣቸው የቻለበትን ምክንያት አጥኚዎች ሲቃኙ ዘመዶቻቸውን የመሾምና በመዳር የፖለቲካ መሠረታቸውን ማስፋት መያያዛቸውን በምሳሌ እንደሚከተለው አስረድተዋል፡፡ የወንድሞቻቸውን ልጆች ወ/ሮ ከፋይ ወሌን ለትግራዩ ራስ መንገሻ ዮሐንስ፣ ወ/ሮ ምንተዋብ ወሌን ለሸዋው ራስ መኰንን (በኋላም ለጎጃሙ ራስ ከበደ መንገሻ አቲከም)፣ ወ/ሮ የተመኙ አሉላን ለሹም ተምቤን ገብረ መድኅን ከዚያም ለነጋድራስ ኃይለ ጊዮርጊስ፣ የእህታቸውን ልጅ ወ/ሮ አሰለፈች ወልደ ሃናን (በአራት ልዩ ልዩ አጋጣሚ) ለራስ ልዑል ሰገድ፣ ለራስ ደምሰው ነሲቡ፣ ለደጃዝማች ይልማ መኰንን እና ደጃዝማች ሥዩም ተክለ ሃይማኖት  (በኋላ ራስ ኃይሉ ለተባሉት) ድረዋቸዋል፡፡
የእቴጌ ጣይቱን ዘመዶች ሥልጣንና የጋብቻ ትስስር በማድነቅም በመደንገጥም የታዘቡት ኢጣሊያዊው አስተዳዳሪ ፈርዲናንድ ማርቲን በ1892 እስከ 93 ዓ.ም. አካባቢ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፡፡
‹‹ግማሽ አገሪቷ በዘመዶቻቸው እጅ ናት፡፡ ራስ ወሌ (ወንድማቸው) ትግራይና የየጁ ገዢ ናቸው፣ ራስ ጉግሣ ወሌ (የወንድማቸው ልጅ) በጌምደርን፣ ደጃዝማች ገሠሠ (የአክስታቸው ልጅ) ስሜንና ወልቃይትን ይዘዋል፡፡ ራስ መኰንንም ለምንትዋብ ወሌ ድረው በቁጥጥራቸው ሊያውሏቸው ያስባሉ፡፡››
ጋብቻ በጊዜው ለነበረው ፖለቲካ ዋና መሣሪያ እንደነበር ያስረዱት ዶ/ር ኄራን፣ ምናልባትም እንደ እቴጌ ጣይቱ ለሥልጣን የቀረቡ ሴቶች የፖለቲካ ሚዛኑን የሚቆጣጠሩበት፣ መረጃ የሚሰበስቡበት፣ ወዳጅን አቅርቦ ጠላትን የሚያርቁበት ጠቃሚ መሣሪያቻው ጋብቻ ነበር ማለት እንደሚቻል አስምረውበታል፡፡
እቴጌ ጣይቱ የእቴጌነት ማዕረግ ሲቀበሉ የመጀመሪያዋ አልነበሩም፡፡ ከሳቸው በፊት እቴጌ አድማስ ሞገሳ (የአፄ ሚናስ ሚስት (1559 እስከ 63)፣ እቴጌ ማርያም ሥና (የአፄ በካፋ ሚስት (1721 እስከ 30)፣ እቴጌ መነን (የራስ አሊ እናት)፣ እቴጌ ተዋበች (የአፄ ቴዎድሮስ ሚስት) እቴጌ ድንቅነሽ (የአፄ ዮሐንስ እህትና የአፄ ተክለ ጊዮርጊስ ሚስት) ነበሩ፡፡ የእቴጌ ማዕረግ የአስተዳደር ኃላፊነት ነበረው፡፡ ምኒልክ በማይገኙባቸው አጋጣሚዎች በኋላም ታመው በተገኙበት ጊዜ እቴጌ ጣይቱ የመንግሥትን አስተዳደር ሥልጣንና ኃላፊነት ተረክበው የራሳቸውን ሹም ሽር እስከ ማድረግ ደርስው ነበር፡፡
ጣይቱ በሳል ዲፕሎማት እንደነበሩ ያወሱት አጥኝዋ በአውሮፓውያን የአፍሪካ ሽሚያ ወቅት፣ ጣሊያን ኢትዮጵያን በቅኝ ግዛት ለማዋል ባደረገችው ጥረት፣ እቴጌይቱ አርቀው በማሰብና የጣሊያን መንግሥት ወኪሎችን እንቅስቃሴ በቅርብና በጥርጣሬ በማጤን የግጭቱን አዝማሚያ አስቀድመው በመገመታቸውና አዝማሚያው ሲገባቸውም፣ ጦርነት እንደማይወገድ አውቀው ቁርጠኛ አቋም መያዛቸውንና ለቁስለኞች የሚያስፈልገውን ዝግጅት፣ ለስንቅ የሚያስፈልግውን ምግብ አሰናድተው ሲያበቁ፣ ከአፄ ምኒልክ ጦር ጋር የራሳቸውን ፈረሰኛ ጦርና እግረኛ ሠራዊት እየመሩ ወደ ትግራይ መዝመታቸወን ያስታውሳሉ፡፡ በቤተ መንግሥት ያካበቱት ዕውቀት በጦር ሜዳም አገልግሏቸው ኖሮ፣ እንዳ ኢየሱስ ላይ ጣሊያን የመሸገበትን ለማስለቀቅ በኃይል ሳይሆን በብልሃት ብለው በነደፉት እቅድ መሠረት የእቴጌ ጣይቱ ጦር ጠላትን ማርኳል፡፡ የዓድዋ ድል ለሚቀጥሉት 40 ዓመታት የአገሪቷን ነፃነት አረጋግጧል፡፡
እቴጌ ጣይቱ ዘመናዊነትን በአገር ውስጥ ለማስፋፋት ጥረት ያደርጉ እንደነበር በቀደመው ጥናታቸው ያስታወሱት ዶ/ር ኄራን፣ በጊዜው በነበሩ አንዳንድ አውሮፓውያን  በተጻፉ ሰነዶች ላይ አገር ወዳድ ብሎም በዚያው ልክ ለውጥ የማይፈልጉ፣ አዲስ የሆነውን ሁሉ በጥላቻና በፍርሃት የሚመለከቱ ተደርገው ቢጻፍም ጣይቱ የአውሮፓውያንን ዓላማ ይጠራጠሩ እንጂ ለውጥን የሚያናንቁ ሰው እንዳልነበሩ በማስረጃ ጠቅሰዋል፡፡
እንደ ዶ/ር ኄራን አገላለጽ ምኒልክ ወደ ሐረር ዘምተው ሳለ፣ መናገሻውን ከእንጦጦ ወደ አዲስ አበባ ያሸጋገሩት፣ እቴጌ ዋና ከተማችንን ቆርቁረው ሰየሟት፡፡ ይህችን የቆረቆሯትን ከተማ የዘመናዊ ሥልጣኔ መንገድን እንድትከተል በአገሪቷ የመጀመሪያውን ሆቴል ከፍተው፣ ሰው ከቤቱ ወጥቶ መብላትን እንዲለመድ ለማድረግ ምግብ ዝግጅቱን መጀመሪያ ላይ ራሳቸው ይከታተሉ እንደነበር ይወሳል፡፡ በሌላ በኩል  በጊዜው ልዩ የነበሩ ባለሃብቶችን ያቀፈ የኢትዮጵያ ባንክ ለመመሥረት ሞክረዋል፡፡ ለአጭር ጊዜ አቋቁመውት የነበረው እርሻና ንግድ ማስፋፊያ ማኅበር ገንዘብ በማበደር ይታወቅ ነበር፡፡ ታዲያ በነዚህ ሁሉ መንገዶች ስንመለከታቸው፣ እቴጌ ጣይቱ ለኢትዮጵያ ህልውና እና ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው እንረዳለን፡፡
እቴጌ ጣይቱ ከኢትዮጵያ ከአፍሪካውያት መሪዎች ንግሥታት አንፃርም አጥኚዋ እንደሚከተለው ተመልክተዋቸዋል፡፡
ቀደም ባለው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደ እቴጌ ጣይቱ ተሰሚነት የነበራቸው ብልህ ሴት መሪዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም መሀል በ15ኛው ክፍለ ዘመን የሐድያ ተወላጅ የነበሩት ከአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ቤተ መንግሥት ወደ ሥልጣን የቀረቡት ንግሥት እሌኒ፤ በ18ኛው ክፍለ ዘመን ደግሞ እንደ ሚስት፣ እንደ እናትና እንደ አያት የእቴጌነት ማዕረግ የነበራቸው የቋራዋ ኦሮሞ እቴጌ ምንትዋብ ይጠቀሳሉ፡፡ ጎንደርን ከወሎና ከትግራይ በጋብቻ በማስተሳሰር ይጥሩ የነበሩ እቴጌ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡
ከአውሮፓ ቅኝ ግዛት አስቀድሞ በ1870ዎቹ ዓመታት የአፍሪካ ሴቶች የፖለቲካ ሥልጣንና የአስተዳደር ኃላፊነት ሴቶች የፖለቲካ ሥልጣንና የአስተዳደር ኃላፊነት የነበራቸው ሲሆን በዑጋንዳ፣ በዳሆሜ (ቤኒን)፣ በጋና አሳንቴ መንግሥታት፣ ሴቶች በአማካሪነት በአገር ገዢነትና በሚኒስትርነት ያገለግሉ ነበር፡፡ ‹‹ንግሥት እናት›› (Queen Mother) ተብለው የሚታወቁት ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ሴቶች በ19ኛው ክፍለ ዘመን ምዕራብ አፍሪካ ውስጥ ነግሠው ነበር፡፡ ልጆቻቸውን ለአመራር እስኪደርሱ አገር እያስተዳደሩ፣ በጋብቻ ነገዶቻቸውን በማስተሳሰር ሰላም እየፈጠሩ ኖረዋል፡፡ ቅኝ ግዛት ከሰፈረም በኋላ የበኩላቸውን ተጋድሎ አድርገዋል፡፡ በ16ኛው ክፍል ዘመን በአንጎላ የፖርቱጋልን የቅኝ ግዛት ዓላማ በመታገል የሚታወውት አርበኛና ዲፕሎማት ንግሥት ንዚንጋ ምባንዴን ስመጥር መሆናቸውን ያወሱት ዶ/ር ኄራን፣ በዚህ መልኩ ሲታዩ እቴጌ ጣይቱም ከሌሎች አፍሪካውያን ንግሥታት አንዷ መሆናቸውን፣ ቅኝ ግዛትን በመታገል የበኩላቸውን ሥፍራ መያዛቸውን ገልጸውታል፡፡
‹‹ጣይቱ ፀሐይቱ ደማቂቱ ብርሃኒቱ ጣይቱ!…›› እንዳለ ባለቅኔው ጸጋዬ ገብረመድኅን፡፡