Sunday, March 13, 2016

ጌታ የጾመው 40 ቀን ሆኖ ሳለ 15 ቀን ከየት አምጥተን ጨመርን?

፻፯ (107).  
ገዳመ  ቆሮንቶስ  ስለመሔዱ
ተጠምቆም ፤ ሳይውል ሳያድር ሌቱን፡
 ገዳም  ሔደ ፤ እናንተም  ሒዱ ሲለን፡፡       
   ከዚያም ሔዶ ፤ የዘረጋውን  ሳያጥፍ፡
 ከቁመቱም  አንድ  ደቂቃ  ሳያርፍ፡
 ተከልክሎ ፡ ከእህል  ከውኃ  ከዕንቅልፍ፡፡  
     እንዲህ  ጾመ ፤ ዐርባ  ቀንና  ሌሊት፡
 ሊሠራልን ፡ ሊወስንልን  ሥራት፡፡
-       (ማቴ 4፡1  ማር 2፡ 12-13)
ይህ ግጥም ‹‹ልብ ወለድ ሳይሆን ከቅዱሳት መጻሕፍት ያገኘሁትን፣ ከሊቃውንት የሰማሁትን ፍሬ ፍራውን ለቅሜ፤ የረቀቀውን ተርጕሜ፣ ግጥሙ ለእንጕርጕሮ፤ ዜማው ለጐረሮ፤ ምሥጢሩ ለዦሮ እንዲስማማ አድርጌ ባ፩ሺ፱፻፲፬ [1914] ዓ.ም. ጻፍኩት፡፡›› ብለው በበገና መዝሙር መጽሐፋቸው መቅድም ላይ የጻፉት የታላቁ ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ ነው፡፡ በመዝሙረ ዳዊት አምሳል በ151 መዝሙሮች የተደራጀው ‹‹የበገና መዝሙር፡፡ ምሥጢረ ሃይማኖት ዘይነግር፡፡›› መጽሐፍ ‹‹እኔ መልአከ ብርሃን አድማሱ ባህሉን ከቅዱስ ዳዊት፣ ምሥጢሩን ከመጻሕፍት፣ ጣዕመ ዜማውን ከጅማት አግኝቼ ጻፍኩ፡፡›› ብለውታል፡፡
ዛሬ የዘንድሮውን (2008 ዓም) ዐቢይ ጾም ከጀመርን ሰባተኛው ቀን ላይ እንገኛለን፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአንድ ሺሕ ዘጠኝ መቶ ሰባ ሰባት ዓመታት በፊት በፈለገ ዮርዳኖስ በተጠመቀ በማግስቱ ጥር 12 ቀን 31 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ የካቲት 21 ቀን ድረስ በቆሮንቶስ ገዳም የጾመው የዐርባ ቀንና ሌሊት ጾም ምሳሌ አድርገን የጾሙን ዘመን ጀምረናል፣ ተያይዘነዋል፡፡ ታዲያ ጌታ የጾመው ዐርባ ቀን ሆኖ ሳለ እኛ እንዴት ዐሥራ አምስት ቀኖችን ከየት አምጥተን ጨመርን የሚል አስተያየት ሁዳዴ በመጣ ቁጥር ይሰማል፡፡ ባሕረ ሐሳባችንን ምርኩዝ አድርገን ልንጽፍ ወደድን፡፡
ዐቢይ ጾም በኢትዮጵያ ቀለንቶን (ካሌንደር) እጅጉን የተቀደሰ የመንፈሳዊነት መገለጫ ወቅት ነው፡፡ ዐቢይ/ ትልቅ ያሰኘውም የጌታችን ጾምን በዋናነት ይዞ ለ55 ቀኖች ስለሚጾም ነው፡፡ አደረጃጀቱም የመጀመርያዎቹ ሰባት (7) የጾም ቀኖች የዝግጅት ሳምንትን፣ ቀጣዩ የተቀደሰው የዐርባ (40) ቀኖች ጾም፣ በመጨረሻም የሕማማት ሳምንት- ስምንት (8) ቀኖችን ይዟል /7+40+8=55/፡፡ በዚህም መሠረት ዛሬ መጋቢት 4 ቀን 2008 ዓ.ም. የዝግጅት ጾማችን በቅዱስ ያሬድ አመዳደብ የ‹‹ዘወረደ›› ሳምንት ከተጀመረ ሰባተኛው ቀን ላይ ደርሰናል፡፡ በስድስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረው ታላቁ ኢትዮጵያዊ ቲዮሎጂያን ቅዱስ ያሬድ ይህን ሰሞን ‹‹ሙሴኒ›› ይለዋል፡፡ ነቢዩ ሙሴ ዐሥሩን የኦሪት ቃላት ደብረ ሲና ወጥቶ ከልዑል እግዚአብሔር ከመቀበሉ በፊት አንድ ሱባኤ ያህል በጾም በጸሎት በጽሞና አሳልፏልና (ዘፀ. 24፡ 15-18) እኛም ቃል የተባለው ጌታችን የጾመውን የዐርባ ቀኖች ጾም ለመጾም እንደ ሙሴ በጾም በጸሎት በጽሞና እንድናሳልፍ ሥርዓት ተሠርቶልናል፡፡ በየመጻሕፍቱ በየምዕላዱ በየክታቡ እንደተጻፈው እነዚህን ሰባት ቀኖች የሕርቃል ጾም ሲባሉ ኖረዋል፡፡ ሕርቃል በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ የቁስጥንጥንያ ንጉሥ (610- 641) ሲሆን በትውፊት እንደሚወሳው፣ ፋርሳውያን ኢየሩሳሌምን ወረው ቅዱስ መስቀሉን በ614 ዓ.ም. ወደ አገራቸው መውሰዳቸው ተከትሎ ለማስመለስ የተደረገው ትግልን በግንባር ቀደምትነት መርቶታል፡፡ የከተማው ምዕመናን ቅዱስ መስቀሉ እንዲመለስ ጾም ጸሎት ከመያዛቸው ባሻገር ለክብሩም በየዓመቱ አንድ ሳምንት እንደሚጾሙ ቃል ገብተዋል፡፡ ሕርቃልም በ630 ዓ.ም. አካባቢ ቅዱስ መስቀሉን ከኢየሩሳሌም ማስመለሱን በታሪክ ተመዝግቧል:: ከዐቢይ ጾም ጋር የተያያዘውና የመጀመርያው ሳምንት በደባልነት ‹‹ሕርቃል›› የገባው በ15ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነበር (Fr.Emmanuel Fritsch: The Liturgical Year of Ethiopian Church: pp 178-179)፡፡ ይህ ታሪክ በግብፅ (ኮፕቲክ) ቤተ ክርስቲያን የሚታወቅ ሲሆን የመጀመርያውን ሳምንት ‹‹የዝግጅት ጾም›› እያሉ ይጠሩታል፡፡ ከሕርቃል በፊት ቅዱስ ያሬድ ነበርና የሁዳዴው መንደርደርያ ቀዳሚዎቹ የሰባት ቀኖችን ጾም በቀበላ መነሻነት ሙሴኒ፣ የዝግጅት ጾም እያልን እንጠራዋለን፡፡ ከዐርባው ቀኖች ጾም በኋላ የሚመጡት ስምንት የጾም ቀናትም የጌታችንን የሕማማት ሰሙንን ያመለክታሉ፡፡
በመሆኑም ዛሬ ሙሴኒን ፈጽመን ከዘወረደ እሑድ በኋላ የመጣችውን ቅድስት ይዘን ነገ መጋቢት 5 ቀን 2008 ዓ.ም. ጌታችን የጾማቸውን የዐርባ ቀኖች ጾምን እንቀጥላለን፡፡ ጾመ ዐርባ የሚያበቃውም ዓርብ ሚያዝያ 14 ቀን ይሆንና ከማግስቱ ቅዳሜ ሚያዝያ 15 እስከ ሚያዝያ 22 ቀን ድረስ የሚኖሩትን ስምንት ቀኖች ሰሙነ ሕማማት ሆነው ያልፋሉ፡፡ ለፋሲካችንም ለትንሣኤያችንም ያደርሱናል፡፡ ያብቃንና ስለጥንቱ ነገረ ጾም ጥቂት እንበልና እንሰናበት፡፡-
በጥንት ዘመን ቅዱሳን አበውና ምዕመናን ቅዱሱን ጾም ይይዙ የነበረው በቅዱስ ወንጌል እንደተጻፈው (ሉቃ. 4) በጥምቀት በዓል ማግስት ጥር 12 ቀን ሲሆን ፋሲካውን ያከብሩ የነበረውም በመጋቢት ወር ሰሙነ ሕማማትን በማሳለፍ ነበር፡፡ በዘመኑ ዐቢይ ጾምና ሰሙነ ሕማማት በተለያዩ ወሮች መዋላቸው ቀርቶ እንዳሁኑ በአንድነት የተሳሰሩት በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የእስክንድርያ ፖፕ በነበሩት አቡነ ድሜጥሮስ አማካይነት ነው፡፡
ከዚህ መጣጥፋችን ራስጌ የሚገኘው ሥዕል ከዓመታት በፊት ታትሞ የተሰራጨ ነበር፡፡
ይቆየን፡፡
የተባረከ የጾም ዘመን ይሁንልን፡፡  
ወልደ ያሬድ ሔኖክ

No comments:

Post a Comment