Thursday, February 18, 2016

‹‹ነፃ መሆኔን ያወቅኩት ሰዎች ነፃ ነሽ ሲሉኝ ነው››




በብዙዎች የምትታወቀው ኢቢኤስ ቲቪ ላይ በምታቀርበውና ጆርዳና ኪችን በሚሰኘው የምግብ ዝግጅት ፕሮግራሟ ነው፡፡ የአርባ ስድስት ዓመቷ ወ/ሮ ጆርዳና ከበዶም ኢትዮጵያ ውስጥ ትወለድ እንጂ ያደገችው ውጭ አገር ነው፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነች፡፡ የምግብ ዝግጅት ፕሮግራሟን መሠረት በማድረግ ከምሕረት አስቻለው ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ያደግሽው የት ነው?
ጆርዳና፡- ያደግኩትም የተማርኩትም ጣሊያን አገር ውስጥ ነው፡፡ እዚያ ላድግ የቻልኩት ልጆች ሳለን ቤተሰቦቼ ለኑሮ ወደዚያ በመሄዳቸውና እዚያው በመቅረታቸው ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ግን እኔ ወደ አገሬ ተመልሻለሁ፡፡ ከመጣሁ እንኳ አሥራ ስምንት ዓመት ሆኖኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በቲቪ የምግብ ዝግጅት ፕሮግራምሽ ላይ ከምታሳያቸው ነፃ መሆንን ከሚያንፀባርቁ የተለያዩ ሁኔታዎች በመነሣት ብዙዎች ውጭ አገር መኖርሽን ይገምታሉ?
ጆርዳና፡- አዎ ነፃ ሰው ነኝ፤ ነገር ግን በመጀመርያ ደረጃ ነፃ መሆን ተፈጥሮዬ ነው፡፡ አስተዳደጌ ቤተሰቦቼም በርግጥ ለዚህ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ነፃ መሆኔ ለኔ ኖርማል የተፈጥሮዬ ነገር ነው፡፡ ነፃ መሆኔን ያወቅኩት ሰዎች ነፃ ነሽ ሲሉኝ ነው፡፡ ነፃ መሆን ለኔ ሌሎችን ሳያስቀይሙ የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ መቻል ነው፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ግን እብደት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነፃ መሆኔ የተፈጥሮዬና የአስተዳደጌ እንጂ ውጭ የመኖሬ ውጤት ብቻ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲ ሳለሽ ያጠናሽው ምንድን ነው?
ጆርዳና፡- የተማርኩት እንግሊዝ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ያጠናሁት ማርኬቲንግ ነው፡፡ የምግብ ነክ  ሥራ ግን በፍላጎትና ከቤተሰብ ጋር የተያያዘ እንጂ በትምህርት ያገኘሁት አይደለም፡፡ እናቴ ምግብ የማዘጋጀት ከፍተኛ ፍላጎትም ችሎታም ያላት አብሳይ ናት፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁም  ፍላጎቱ ስለነበረኝ የተለያዩ ሬስቶራንቶች እሠራ ነበር፡፡ ምግብ የማዘጋጀት ችሎታዬ ከፍቅርና ከልምድ የመጣ እንጂ ትምህርት ቤት ሄጄ አይደለም፡፡ የተለያዩ ሬስቶራንቶች ውስጥ ከተለያዩ ሼፎች ጋር ሠርቻለሁ፡፡ በትምህርት ላገኝ የምችለውን ነገር በእነዚህ አጋጣሚዎች ማግኘት ችያለሁ፡፡ ሬስቶራንቶች ውስጥ መሥራትም ብቻ ሳይሆን ከቤተሰቦቼ ጋር ከፍተን ሠርቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ከረዥም ዓመታት የጣሊያን ቆይታ በኋላ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሽ?
ጆርዳና፡- የመጣሁት በአጋጣሚ ለስድስት ወር እረፍት ነበር፡፡ ልጅ እያለሁ የማውቀውን የዛሬውን ባለቤቴን በዚህ ወቅት አገኘሁት፡፡ እዚህ የፈረንሳይ ሬስቶራንት ከፈተ፤ ሁለታችንም አብረን መሥራት ጀመርን፡፡ የሀበሻ ምግብ ከዚያም ኬተሪንጉን እያልን እያልን በኢትዮጵያ ፍቅር እዚህ ቀረሁ፡፡ ይህ ውሳኔ በወቅቱ ለእኔ ከባድ አልነበረም፤ ምክንያቱም ብቻዬን ነኝ ውሳኔውም የእኔ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- የቴሌቪዥን የምግብ ዝግጅት ፕሮግራም መሥራት ያሰብሽው መቼ ነበር?
ጆርዳና፡- የዛሬ አሥር ዓመት ሐሳቡ ነበረኝ፡፡ ምን መቅረብ አለበት? ሕዝቡ ምን ይፈልጋል? እንዴትስ ይቀበለዋል? የሚለውን ሳስብበት ነው የቆየሁት፡፡ ከምግብ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው በሽታዎች አሉ፡፡ አመጋገብና ጤናንም ከግንዛቤ ከትቻለሁ፡፡  በመጨረሻ ነፃ ሆኜ መሥራት የምችልበትን ሁኔታ ኢቢኤስ ስላመቻቸልኝ፣ በምፈልገው መንገድ እንድሠራ ሰፊ እድል ስለሰጡኝ አሳቤን አሁን ተግባራዊ ላደርገው ችያለሁ፡፡ እንደዚሁ ጊዜና ሁኔታዎችን የሚጠብቁ በርካታ በወረቀት አስፍሬ ያስቀመጥኳቸው የሥራ ሐሳቦች አሉኝ፡፡
ሪፖርተር፡- አንድን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ አሥር ዓመት መጠበቅ ረዥም አይደለም?
ጆርዳና፡- ረዥም ነው፡፡ ግን እኔ ቅድመ ሁኔታዎች እየተቀመጡልኝ መሥራት የምወድ ሰው ስላልሆንኩኝ በምፈልገው መልኩ ለመሥራት ጊዜ መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ ሁኔታዎች ከተቀመጡ ሁሌም እኔ ይሄን አድርጊ ያንን እየተባልኩ አሻንጉሊት እሆናለሁ፡፡ ይህን ደግሞ አልፈቅድም፡፡ ፕሮፖዛሌን ኢቢኤሶች አዩት፣ ወደዱት በምፈልገው መልኩ በነፃነት እንድሠራ ሁኔታዎችን አመቻቹልኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ቀደም ባሉት ጊዚያት ምግብ ማብሰል የሴቶች ኃላፊነት ፍላጎቱም የሴቶች ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡ አሁን ግን ወንዶችም ምግብ የማብሰል ፍላጎት እያሳዩ የመጡበት ሁኔታ አለ እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለሽ?
ጆርዳና፡- መሠረታዊው ነገር የማብሰል ፍላጎት መኖሩ ነው፡፡ ምግብ የማብሰል ፍላጎት ያለው ሰው ያበስላል፡፡ ሴት ወንድ የሚለውን ነገር ያመጣው ባህል ነው፡፡ ሆዱን የሚወድ፣ ጥሩ ምግብ የሚወድና የሚያስደስተው ሴትም ወንድም ያበስላል፡፡ እውነት ነው ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ወንዶች ማብሰል ጀምረዋል፡፡ ለምሳሌ ሴቷ ደህና ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ካላትና የወንዱ እስከዚህም ከሆነ ወንዱ ቁጭ ብሎ እያበሰለ ልጆች የሚያሳድግበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ ደስ የሚያሰኝ ለውጥ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያየ መልኩ አስተያየታቸውን የሚገልጹልሽ እነማን ናቸው?
ጆርዳና፡- የመጀመርያዎቹ ልጆች ናቸው፡፡ ትልልቅ ሴቶችም አስተያየት ይሰጡኛል፤ ወንዶች ግን ይበዛሉ፡፡ ከሁሉም የሚያስደስተኝ ግን የልጆች አስተያየት ነበር፡፡ ምክንያቱም ልጆች ነፃ መንፈስ ያላቸው በመሆናቸው ነው፡፡ አድገው ከዓመታት በኋላ ጆርዳና እንዲህ ትል ነበር፣ እንደዚያ ማለታቸውን ሳስበው እደሰታለሁ፡፡ ምንም እንኳ የእኔን የምግብ ፕሮግራም ተመልክተው አስተያየት ሰጡ ማለት ወንዶች ምግብ ማብሰል ጀመሩ ማለት ባይሆንም ፍላጎት እያደረባቸው ለውጥም እየታየ የመሆኑ ምልክት ነው፡፡ ስለዚህም ምግብ ለማብሰል ወደ ማዕድ ቤት መግባት ይሞክራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የምግብ ዝግጅት የሙሉ ጊዜ ሥራሽ ነው?
ጆርዳና፡- አዎ የሙሉ ጊዜ ሥራዬ ነው፡፡ አዳዲስ ሬስቶራንቶች ሲከፈቱ አማክራለሁ፡፡ ሠርጎችና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ምግብ አዘጋጃለሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልኩ የምሠራቸው ሥራዎች በአጠቃላይ በምግብ ዝግጅት ዙርያ ያሉ ናቸው፡፡ የኢቢኤሱ የምግብ ዝግጅት ፕሮግራም ግን ከሁሉም በላይ ጊዜዬን ይወስዳል፡፡ በመሀል ክፍተት ሳገኝ ግን ሌሎቹን ሥራዎች እሠራለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ስለ አመጋገባችን አስተያየት አለሽ?
ጆርዳና፡- ይህ ምግብ ምን ይዘት አለው? ምን የለውም ብሎ የመጠየቅ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ዛሬንና የዛሬ አሥራ ስምንት ዓመት የነበረውን ሁኔታ ስናነፃፅር አሁን ብዙ ለውጥ አለ፡፡ ስለዚህ ከምግብ ጋር በተያያዘ ሰው የተለያየ ነገርን ማወቅ የሚፈልግበት ጊዜ መጥቷል፡፡ ዓመት በዓል ካልሆነ በቀር ዛሬ ሰው በደንብ የተቁላላ ወጥ መብላት አይፈልግም፡፡ ቀለል ያለ ብዙ ያልተጠበሰ ምግብ ምርጫው እየሆነ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ በምግብ ዝግጅት ላይ የሚያተኩር ጋዜጣ የመጀመር ሐሳብ አለኝ፡፡ ሐሳቤ በወረቀት ላይ ሰፍሮ ተቀምጧል፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ይህ ዓይነቱን ጋዜጣ የምንፈልግበት ደረጃ ላይ ስንደርስ ሐሳቤ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ሕዝቡ ስለአመጋገብ ጆሮውን መክፈቱን መረጃ መፈለጉን በሚመረቱ ምርቶች፣ እላያቸው ላይ በሚለጠፉ መረጃዎች ማወቅ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- የምግብ አዘገጃጀታችንን በሚመለከት የምትይው ይኖራል?
ጆርዳና፡- ዘይት ይበዛል፡፡ አትክልቱ ምንነታቸው እስኪለወጥ ድረስ ይጠበሳሉ፡፡ ይህ በሒደት የሚቀየር ነው፡፡ የምግቦችን የንጥረ ነገር ይዘት መመልከት ደግሞ ሌላ ትኩረት ልናደርግበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ካርቦሀይድሬት ፕሮቲንና አትክልት ያስፈልገናል፡፡ አቅም በፈቀደ በተቻለ እነዚህን ማመጣጠንና ጤናችንን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እንደ ጎመን፣ ሰላጣ ያሉ ነገሮች ብዙ ውድ አይደሉም፡፡ እኔ በነሱ ብኖር ደስተኛ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርብ ልትሠሪ የምታስቢው ነገር ካለ?
ጆርዳና፡- ያለኝን የቲቪ የምግብ ዝግጅት ፕሮግራም ማጠናከር ነው፡፡ ሠርቼ አልጠግብም፣ አይደክመኝም፡፡ አሁን በሳምንት ሁለት ጊዜ ነው የምሠራው፣ የሚታየው ግን አራት ጊዜ ነው፡፡ ጥያቄውም ስፖንሰሩም ካለ በቀን የመሥራት አቅም አለኝ፡፡

No comments:

Post a Comment