Sunday, February 14, 2016

የቀለሙ ቀንድ - ኪዳነ ወልድ

29 June 2014 ተጻፈ በ 


(አ) ፊት በር
ካፍሪቃ ወንዞች ወርቅና አልማዝ - እንደሚያስገኘው እንደ ዓባይ ወንዝ
ተርፎን እንዲፈስ ትምርቱ ንግድ - በዚህ ሰዋስው ጥርጊያ መንገድ
ይልቅ ኑ እንውጣ ወደ ገበያ - ገበያችንም ኢትዮጵያ፡፡

መደብሮቿ የተዘጉቱ - ባራቱ ማዕዘን እንዲከፈቱ
ልጆቿን በሙቀት እያሳደገ - መንገዶቿንም እያስጠረገ
እግዜር ያቆማት ከማኽል ቦታ - በውጭ አገር ሰው እንዳትፈታ፡፡
ያፍሪቃ ደንደስ ሻኛና ጫንቃ - ጦቢያው እንጂ ናት ምሥራቅ አፍሪቃ
የሰማይ ምደር የምድር ሰማይ - የተከበበች በነጭ አባይ 
ዐይኗም ሲመስል በገነት ዐይን - ነጩ አባይ መደብ ጥቁሩ ብሌን
ባስተያየትም ሲመረመሩ - ማየት አይችልም ነጭ አለ ጥቁሩ፡፡ 
ነጩ ሲፈተሽ ውስጠ ጥቁር - ጥቁሩም ሲፈተሽ ውስጥ ነጭ ዘር፤
ሕብረ ሰማይ ነው ጥቁሩ አባይማ - በቂጥኛም አፍ የማይታማ፡፡ 
ነጭና ጥቁር የዓለም ዐይን - ኹሉም ተገልጦ የሚከድን፤
መክደኛውም ሞት ወዝ ከንባይ ነው፤ ያዳም ሌባ ጣት የሰፋችው፡፡
ይህ በሰምና ወርቅ መንገድ የቀረበው የቅኔ ገበታ ከሰማንያ ዓመታት በፊት ታላቁ ኢትዮጵያ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከደረሱት ሰፊ የቅኔ አዝመራ የተቀነጨበ ነው፡፡ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በሚባለው የግእዝ ቋንቋ ሰዋስውና ግስ፣ የግእዝ አማርኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ውስጥ የተገኘው ሰማዊና ወርቃዊው ቅኔያቸው የግእዝን ትምህርት በአባይ ወንዝ የመሰሉበት ኢትዮጵያም የአፍሪቃ አውራ፣ የአፍሪቃ ቀንድ መሆኗን ያጠየቁበት ነው፡፡ በግእዝ ኢትዮጵያ የዕውቀት መደብሮች ውስጥ የሚገኙትን መክሊቶች በግእዝ ሰዋስው መሰላልነት መሠረትነት እናውጣቸው፣ እንጠቀምባቸው የሚል ሴማ አለው፡፡ 
በኢትዮጵያ የቋንቋዎች ሕዋ፣ በሥነ ጽሑፍ ገበታ፣ በአንድምታ ትርጓሜ እልፍኝ ውስጥ ላቅ ያለ ስፍራ የሚሰጣቸው ሊቁ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በአፀደ ሥጋ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን፣ ዓለምንም ከተለዩ ሰኔ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ልክ 70 ዓመት፣ 70 ክረምት፣ 70 መፀው፣ 70 በጋ፣ 70 ፀደይ ይሞላቸዋል፡፡ 
በቀለም - አበባ ይዘከሩና እኚህን ታላቅ የጥበብ ሰው እንዘክራለን፡፡
(ቡ) አለቃ ኪዳነ ወልድ ማን ናቸው?
ከሰባ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 24 ቀን ስላረፉት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ዜና ዕረፍት፣ በወቅቱ በሳምንታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ደቀ መዝሙራቸው አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ከታሪካቸው ጋራ ሐምሌ 1 ቀን 1936 ዓ.ም. ጽፈውት ተገኝቷል፡፡ በጋዜጣውና በመጽሐፈ ሰዋስው ላይ የሰፈረውን ዜና ሕይወታቸውን አዛምደን ለማቅረብ ወደድን፡፡  
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በ1862 ዓ.ም. የተወለዱት በይፋት ወረዳ [ሰሜን ሸዋ] ነው፡፡ በጎንደር ባለቃ ዘዮሐንስ ዘንድ የዳዊት ትርጓሜ ተምረው ከጨረሱ በኋላ በ1891 ዓ.ም. በዘመነ ሉቃስ ከጎንደር ተነሥተው በአክሱም በኩል ምፅዋ ኼደዋል፡፡ ከምፅዋም በመስከረም 1892 ዓ.ም. በግብፅ አስቄጥስ ገዳም በመግባት ለስምንት ወራት ቆይተዋል፡፡ በሚያዝያ ወርም ለ20 ዓመታት ወደኖሩባት ኢየሩሳሌም ተጉዘዋል፡፡ በኢየሩሳሌም ቆይታቸው ካገኟቸው መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የብሉይንና የሐዲስን፣ የሊቃውንትንና የመጻሕፍተ መነኮሳትን፣ የፍትሕ ነገሥትን ትርጓሜ ለዐሥር ዓመት ተማሩ፡፡ አቡሻህርና መርሐ ዕውርም [ባሕረ ሐሳብ] ዐወቁ፡፡ መምህራቸው ካረፉ በኋላ በኢየሩሳሌም የዓመታት ቆይታቸው የግእዝ ቋንቋ ቤተኛ የሆኑትን ዕብራይስጥ፣ (የእሥራኤል ቋንቋ)፣ ሱርስት (የሶርያ ቋንቋ) እና ዐረብኛ አጠኑ፡፡ የብሉያትንም ትርጓሜ ከዕብራይስጥ አጥብቀው አጥልቀው መረመሩ፣ በዕብራይስጥና በጽርእ (ግሪክ) በግእዝ መጻሕፍት መካከል እንዴት ያለ ልዩነት እንዳለ ተረዱ፡፡ ከዚህም በዃላ ጃንሆይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዐልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን ይባሉ በነበረ ጊዜ የግእዝን መጻሕፍት እያስተረጎሙ ሲያስጥፉ ሕዝቅኤልን መጥተው እንዲተረጉሙላቸው ስላስጠሯቸው በ1912 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ የሕዝቅኤልንም ንባብ በዕብራይስጥ ዐርመው አጥርተው አብርተው፣ ትርጓሜውንም ከዕብራይስጥና ከሮማይስጥ አውጥተው፣ ዐልፎ ዐልፎም ማስረጃ ሥዕል አግብተው በ1916 ዓ.ም. አሳትመው ለግርማዊነታቸው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስረከቡ፡፡ በ1926 ዓመተ ምሕረትም መዝገበ ፊደል አውጥተው ከየት መጣውን ከነማስረጃው ጥፈው ሌላም ታናሽ ፊደል ከዕብራይስጥና ካረብኛ ጋራ አቆራኝተው አሳትመዋል፡፡ 
በድሬዳዋም ኅሊና ያልደረሰበትን የግእዝ ቋንቋ እየመረመሩ ሲጥፉ 22 ዓመት ተቀመጡ፡፡ ጠላት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ጣሊያን ለቅጣት ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያን አይገዛም፣ ጃንሆይም ሲኼዱ እንዳየናቸው ተመልሰው እናያቸዋለን እያሉ ሳይፈሩ ሳያፍሩ በግልፅ ስለሰበኩ በ1929 ዓ.ም. ኹለት ወር አሰራቸው፡፡ ዳግመኛም በ1933 ዓ.ም. አንድ ወር ካሰራቸው በዃላ እንግሊዞች ፈቷቸው፡፡ የታሰሩበት በጨለማ ውስጥ ነበርና በፊተኛው እስራት ግራ ዐይናቸው በኹለተኛው ቀኝ ዐይናቸው ታወረ፡፡ 
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐይንኽን አሳክምኻለኹ ስላሏቸው በ1936 ዓ.ም. ኅዳር 15 ቀን አዲስ አበባ መጥተው ተቀምጠው ሳሉ የስኳር በሽታ ነበረባቸውና 15 ቀን ከታመሙ በኋላ በራስ ደስታ ሆስፒታል በተወለዱ በ73 ዓመታቸው ሰኔ 24 ቀን ከማታው በ12 ሰዓት ተኩል ዐርፈው ሬሳቸው በክቡር አባ ሐና ርዳታ ካዲስበባ በካሚዮን ተጉዞ በ11 ሰዓት ተኩል ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ፡፡ ሐሳባቸው ኹሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በማንኛውም ነገር ራሷን እንድትችል ነበር፡፡ 
(ጊ) ሥራዎቻቸው
አራት ዐይናው ኪዳነ ወልድ ከቋንቋና ከመዝገበ ቃላት፣ ከሃይማኖትም ጋራ የተያያዙ ታላላቅ መጻሕፍት አዘጋጅተዋል፡፡ በሕይወት እያሉ የታተሙላቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም የመዠመርያው፣ ‹‹መጽሐፈ ሕዝቅኤል ከትርጓሜው ጋራ ንባቡ በግእዝ ትርጓሜው ባማርኛ ከኪዳነ ወልድ ክፍሌ ተጽፎ ታተመ፡፡ ፲፱፻፲፮ (1916)›› ኹለተኛው፣ ‹‹አበገዳ ፊደልና ፊደላዋሪያ የልጆች አፍ መፍቻ››፣ ሦስተኛው ‹‹መዝገበ ፊደላት ሴማውያት››ኹለቱም በድሬዳዋ ከተማ በቅዱስ አልዓዛር ማተሚያ ቤት በ1926 ዓ.ም. የታተሙት ናቸው፡፡
የአለቃ ኪዳነ ወልድን ስም በግዘፍ ከሚያስነሡት ሥራዎቻቸው ዋነኛው ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› ነው፡፡ ይህ በአንዳንዶች አገላለጽ ኢንሳይክሎፔዲያ መሰል መጽሐፍ የኅትመት ብርሃን ያየው ሊቁ ባረፉ በ12 ዓመት፣ በ1948 ዓ.ም. በደቀ መዝሙራቸው (ተማሪያቸው) አለቃ ደስታ ተክለወልድ ዘብሔረ ወግዳ አማካይነት ነው፡፡
መጽሐፈ ሰዋስውን በቅድሚያ ማዘጋጀት የጀመሩት መምህራቸው ክፍለ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ያንኮበሩ ሊቅ መምህር ክፍሌ ወልደ አባ ተክሌ አለቃ ደስታ እንደጻፉት፣ ትምርት ከጥፈት ያስተባበሩ፣ በትምህርታቸውም የተደነቁና የታወቁ የውጭ አገር ባህል ቋንቋና ፊደል ያጠኑ ነበር፡፡ በምፅዋ ደሴት ግሱን የጨረሱት ለማረምና ለማሳተም ዕረፍትና ጊዜ አላገኙም፡፡ ተከረን ወደ ሮማ፣ ከሮማ ወደ የሩሳሌም ሲሉ ብዙ ጊዜ ዐለፈ፡፡ ኋላም በጊዜ ሞት 10 ዓመት ሙሉ ከርሳቸው ጋራ በኢየሩሳሌም ለነበረው ለሀገራቸው ልጅ ለተማሪያቸው (ኪዳነ ወልድ) እንዲህ ብለውታል፤ ‹‹ልጄ ሆይ ይህነን ግስ ማሳተም ብትፈልግ እንደገና ጥቂት ዕብራይስጥ ተምረኽ ማፍረስና ማደስ አለብኽ፤ በመዠመሪያው አበገደን ጥፈኽ የፊደሉን ተራ በዚያው አስኪደው፡፡ አንባቦችም እንዳይቸገሩ ከፊደል ቀጥለኽ ዐጭር ሰዋስው አግባበት፣ የጎደለውና የጠበበው ኹሉ መልቶ ሰፍቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው፤ ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን አንድ መክሊት ለማብዛትና ለማበርከት ትጋ ዘር ኹን፣ ዘር ያድርግኽ ካላጣው ዕድሜ አይንፈግኽ ለሀገርኽ ያብቃኽ ብለው ተሰናበቱት፡፡››
አለቃ ኪዳነ ወልድ ‹‹ዐደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ›› ነውና ከመምህራቸው የተቀበሉትን ዐደራ ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ 22 ዓመት ሙሉ ሠርተው አጠናቀቁት፡፡ ሒደቱን አለቃ ደስታ ባጭሩ እንዲህ ይገልጹታል፡፡ ‹‹ሕዝቅኤልንም ንባቡን ከምሉ ትርጓሜው ጋራ [1916 ዓ.ም.] አሳትመው ካስረከቡ በዃላ በቅድስት አገር [ኢየሩሳሌም] የወጠኑትን ይህን ብርሃናዊ መጽሐፍ  [መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ] እንደገና በድሬዳዋ ማዘጋጀት ዠመሩ፡፡ በሥራ ውለው ማታ ነፋስ በመቀበል ጊዜ አንድ ሐሳብ ቢያገኙ በማስታወሻ ለመጻፍ ከውጭ ወደ ቤት ይመለሳሉ፡፡ በምሳ ወይም በራት ጊዜ አንድ ትርጓሜ ቢታሰባቸው ምግቡን ትተው ብድግ ይላሉ፡፡ ሌሊትም ተኝተው ሳሉ አንድ ምስጢር ቢገጥማቸው ከመኝታቸው ተነሥተው መብራት አብርተው ይጽፋሉ፡፡
‹‹ያን ጊዜም ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያዘዙላቸውን ቀለብና ድርጎ እያደራጁ በዕለት መፍቅድ ይረዷቸው የነበሩ የክቡር ብላታ አሸኔ ኪዳነ ማርያም ባለቤት ክብርት ወይዘሮ በላይነሽ ጎበና [የራስ ጎበና ዳጨው ልጅ] ናቸው፡፡ 
የአለቃ ኪዳነ ወልድ ሌላኛው መጽሐፍ ‹‹ግእዝ መሠረተ ትምህርት›› ነው፡፡ ለዚህ መጽሐፍ መዘጋጀት መንሥኤ የሆነው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላለቃ ኪዳነ ወልድ መፍቅድኽን  [ቀለብህን] እየሰጠኹ በምትፈልገው ነገር ኹሉ እረዳኻለሁ (እጦርኸለኹ)፣ ስላገራችንም ጥቅም ብዙ ዘመን የደከሙበትን የግእዝ ሰዋስውና ግስ አሳትምልኻለኹ ብለው ተስፋ ስለሰጧቸው በ1936 ዓ.ም. ኅዳር 26 ቀን ወዳዲሳበባ መምጣታቸው ነበር፡፡ ቀበና በተቀመጡ ጊዜ ሦስት ሰዎች የግእዝ ቋንቋ መማር እንፈቅዳለን ቢሏቸው የስምና የአንቀጽ ርባታ በቃል በጽፈት ማታ ማታ ማስተማር ዠመሩ፡፡ ይህንንም ከ60 ዓመት በፊት አለቃ ደስታ ሰብስበውና ጽፈው በ1946 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የኅትመት ብርሃን እንዲያይ አደረጉት፡፡ 
ሌላው የሊቁ ሥራ በ1980ዎቹ በሀገረ ጀርመን በቁም ጽሕፈት ለኅትመት የበቃው የነገረ መለኮት (ቲኦሎጂ) መጽሐፍ የኾነው ‹‹ሃይማኖት አበው ዘቀደምት ወዘደኃርት›› ነውና፡፡ ሊቄ ኪዳነ ወልድ፣ መጸሐፉን በግእዝና ባማርኛ ንባብና በኹለት ዐይነት ግጥም አድርገው አዘጋጅተውና ጽፈው ያጠናቀቁት በ1934 ዓ.ም. ነበር፡፡ 
አለቃ እስካሁን ያልታተሙ መጻሕፍት እንዳሏቸውም ይነገራል፡፡ አንዱ ‹‹የዕብራይስጥ ግስ በግእዝ ፊደል ተጽፎ በግእዝ ቋንቋ የተተረጐመው›› ነው፡፡ ማን ይኾን ባለተራው ባለዐደራ የሚያሳትመው፣ ከኅትመት ብርሃንስ ጋራ የሚያገናኘው? 
(ዳ) ቅንጫቢ
ሊቁ ከጻፏቸው መጻሕፍት ለማሳያ፣ አንድም ለአንክሮ ለተዝክሮ ይኾን ዘንድ ባጭሩ እንጽፋለን፡፡ 
1.የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ትርጓሜ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት አንዱ ‹‹ትንቢተ ሕዝቅኤል›› ነው፡፡ በ1916 ዓ.ም. ንባቡ በግእዝ ትርጓሜ በአማርኛ አድርገው አዘጋጅተውታል፡፡ አተረጓጐሙ አንድምታ ነው፡፡ ከነጠላ ትርጉም ያልፋል፡፡ ምዕራፍ 27 ቁጥር 17 እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ይሁዳና እስራኤል ምድር ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሚኒትን ስንዴ ጣፋጭም እንጐቻ ማር ዘይትም በለስንም ስለአንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር፡፡››
ሊቁ ግእዝና አማርኛውን ከአንድምታው ጋር ጂኦግራፊያዊ ተዘምዶውንም ከኢትዮጵያ ጋር አያይዘው እንዲህ አቀረቡት፡፡ 
‹‹ይሁዳ ወምድረ እስራኤል እሙንቱ ሠየጥኪ፡፡ ይሁዳ ሠማሪያ አሥሩ ነገድ፣ ሁለቱ ነገድ የሚገዙና የሚሸጡ ነጋዶችሽ ነበሩ፡፡
‹‹ወረሰዩ ማዕረብተኪ በሥርናየ ሚኒት ወበሰምዕ ወመዓር ወቅብዕ ወርጢን፡፡ 
ሚኒት ከሸዋ እንደ ቡልጋ፣ ከትግሬ እንደ እንደርታ ያለች የስንዴ አገር ናት፡፡ ርስትነቷ የደቂቀ አሞን ነበረ፡፡ ገለዓዳዊ ዮፍታሔ በጦርነት ወስዷታል፡፡ ንግድሽን ከሚኒት በሚወጣ ስንዴ በሰምና በማር በዘይትና በበለሳን አደረጉት፡፡ በለሳን ጥሩ ሽቱ ነው፤ በኢያሪሆ ይበቅላል፤ ኢያሪሆ ማለት ሠናየ መዓዛ ዘመዓዛሁ ሠናይ ማለት ነው፡፡ ቦ ርጢን በቁሙ መድኃኒት ማለት ነው፡፡ በምድረ እስራኤል የማይበቅል እንጨት የለምና፡፡
2.‹‹አበገደ - ፊደልና ፊደላዋሪያ የልጆች አፍ መፍቻ››
በአበገደ ፊደል ገበታ የተዘጋጀው መማሪያ መጽሐፍ፣ ከፊደል ገበታው በተጨማሪ ንባብና ሥርዓተ ነጥብ፣ ከግእዝ ጋራ የሚዛመዱት የሱርስትና የዕብራይስጥ የዐረብም ፊደል ከነስሙና ከነቁጥሩ ይዟል፡፡ ፊደላቱ ዲቃሎቻቸውም ሳይቀሩ፣ ድምፀ ልሳኑ የሚነገርበትን ባምስት ጾታ በጉሮሮና በትናጋ፣ በምላስና በከንፈር በጥርስ የሚነገሩትን ያሳያል፡፡ 
‹‹የፊደላዋሪያ መቅድም›› በሚለው ክፍል ተማሮች ከፊደል ጋራ በግጥም ቃል የተመላለሱበት ተውኔታዊ ምልልስም ይገኝበታል፡፡
ከ80 ዓመት በፊት በታተመችው መጽሐፍ ብዙ ቋንቋዎችን መማር ልዩ ልዩ ጥበባትን መቅሰም እንደሚያስፈልግ ታሳስባለች፡፡ ጵጵስናን ከግብፅ መፈለግ የለብንም፤ የራሳችንን ሊቃውንት ጳጳሳት አድርገን መሾም አለብንም ትላለች፡፡ የኪዳነ ወልድ ድምፅ፡፡
(ተማሪ)   ‹‹ሃይማኖት ያስለውጥ እየመሰለን
            እጅግ አንወደውም ቋንቋን መማሩን
            ከሃይማኖት ኹሉ የኛ ሃይማኖት
            ትበልጣለችና በውነተኛነት፡፡
(ፊደል) ‹‹የልጅ ነገር ወትሮ ሁለት ቅንጣት ፍሬ
       አንዱ ፍጹም ብስል አንዱ ፍጹም ጥሬ፤
        አባቴ ታናሽ ነው ሃይማኖቴ ክፉ
        የሚል የለምና በዚህ አትስነፉ፡፡ 
       ቋንቋና እጅ ሥራ ካልጨመራችኹ
       ንግድና መኪና ካላቆማችኹ
       ባንድ ክፍል ትምርት በድጓ በቅኔ
       አይገኙምና ብዕልና ሥልጣኔ
      ይልቅስ ተማሩ ኹሉን በያይነቱ
     ቶሎ እንዲለቃችኹ ስንፍናው ንዴቱ፡፡
     … አንድ ዐረግ ቢስቡ ዱር ይሰበስቡ
     የተባለውን ቃል ስለ ቋንቋ ዐስቡ፡፡ 
    በዚህ ላይ መምሩ ያገር ልጅ ሲኾን
    መሰወር አይችሉም ጥበብና ኪን፤
    ያገር ልጅ የማር እጅ የሚሉት ተረት 
    ከመምር ከጳጳስ አለው መስማማት፡፡
   ንጉሥና ጳጳስ ግራና ቀኝ ዐይን 
  አንድ ዐይነት ሊኾኑ አይገባምን?
  ንጉሥ እያላችኹ ጳጳስ መበደር
  ይኸ ነው የዘጋው የትምርቱን በር፡፡
  መበደሩ ቀርቶ ክህነትና አቡን
  ሊቀ ጵጵስናው በጃችኹ ቢኾን፤
  ኢትዮጵያችሁ እንደ ፀሐይ ሙቃ
  ታንዣብቡ ነበር አፍሪቃ ላፍሪቃ፤
  ወደ እስያም ክፍል እንዳፄ ካሌብ
   ትሻገሩ ነበር በወንጌል መርከብ፡፡››
3.‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ መመዝገበ ቃላት ሐዲስ››
ባለታሪካዊው የ922 ገጹ የግእዝ - አማርኛ መጽሐፍ በ19ኛው ምእት ዓመት አጋማሽ ተዠምሮ በ20ኛው ምእት አጋማሽ የኅትመት ብርሃን ያየ መጽሐፍ ነው፡፡ በዝግጅትና በኅትመት ጉዞው ሦስት ትውልዶችን አሳልፏል፡፡ ከመዝገበ ቃላቱ የኹለት ቃላት አፈታት እነሆ፡፡
ወንጌል፤ (ላት፡፡ ጽርዕ (ግሪክ) ሄዋንጌሊዎን፡፡ ዐረብ ኢንጂል)፣ በቁሙ፤ ብሥራት፣ ምሥራች፤ ሐዲስ ዜና መልካም ወሬ፣ ደስ የሚያሰኝ ስብከት፤ አምላካዊ ሰማያዊ ነገር፤ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፡፡
-፤መጽሐፍ የመጽሐፍ ስም፤ የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ አራት ክፍል ያለው፣ አራት ሰዎች የጣፉት፤ ፍችው ያው ብሥራት ነው፡፡
ወይ፤ (ዐረብ ዋእ፣ ወይ፡፡ ሱርስት (የሶርያ) ዋይ፡፡ ዕብራይስጥ ኦይ)፤ ንኡስ አገባብ፡፡ በቁሙ፤ ወዮ ወየው፤ ዋይ ውይ፤ አወይ የልቅሶ የሐዘን፣ የቁጣ፣ የንዴት፣ የብስጭት ቃል ነው፡፡ ወይ ሊተ፣ ወይ ልየ፣ ወይ ለከ እያለ እንደ አሌ በለ ይዘምታል፡፡ አሌንና ለይን ተመልክት የዚህ ጎሮች ናቸው፡፡
ወይ፤ (ዐማርኛ)፤ በቁሙ፤ (ዋዌ አው) የማማረጥ ቃል፤ አውን እይ፡፡ (ግጥም፤ ሐፄ ቴ፡ ባሏን የሰቀሉባት)፣ ወይ አልተቀደሰ የባረኩት ሰው፤ ንጉሥ መስቀልዎን ቢተዉት ምነው፡፡ ፪ኛም የምኞትና የፍላጎት የአንክሮ ቃል ይኾናል፤ (ግጥምና ሙሾ ስለጐንደር ጥፋት)፤ ቴዎድሮስ መጣ ዐይኑን አፍጦ፤ ወይ መሸሸጊያ ታናሽ ቁጥቋጦ፡፡ ተከተለኝ ብዬ ዙሬ ዙሬ ሳይ፤ ወይ ጥጋብ ወይ ኩራት ጐንደር ቀረ ወይ፡፡ ፫ኛም ያቤቱታ ቃል የጥሪ ተሰጦ ይኾናል፤ (ግጥም፣ የበለው እኅት ተማርካ በመተማ ሳለች)፤ ጐዣም አፋፉ ላይ የሚጣራው ማነው፤ ወንድሜ እንደኾነ ወይ በለው ወይ በለው፡፡ ምስጢሩ እንደላይኛው ነው፡፡ ፬ኛም  የጥያቄ ቃል ይኾናል፤ ኼደ ወይ፣ መጣ ወይ፡፡ 
‹‹መዐዛ ሰዋስው - የግጥም ስብከት›› በሚለው ክፍልም፣ ለአማርኛ ግእዝ ነው ዳኛ የሚል አስተሳሰብ የያዘ ለአማርኛ መሠረቱ ግእዝ ነው የሚል አቋም ያቀፈ ዐውደ ግጥም ይገኛል፡፡ ባለቅኔው ኪዳነ ወልድ እንዲህ ተቀኝተዋል፤ ሦስቱን አንጓ እነሆ፡፡ 
በዶሮ ሥጋ አምሳል ምሥጢሩ እንዲጥም 
ዐጭሬ ረዥሜ ይባላል ግጥም፤
ዐጭሬው ሰዋስው ረዥሜው ግስ
የሦስት ፊደል ሥጋ የርባ ቅምር ነፍስ
ለልጆች እንዲተርፍ ያዋቆች መብል
ያቡን ወጥ በሚሉት በቲማቲም ቃል
ሠርቶ ያቀረበው የግእዝ ወጥ ቤት
ላስነባቢው ምሳ ላንባቢው እራት፡፡ 
የሰዋስው ትምርት ሥጋውና ዐጥንቱ
ባጭሬው ተክቷል ረዥሜነቱ፡፡
ላንቀጹ ፍልሰታ ለርባታው ሑዳዴ
የተለቀመውን ጥሩ ፊደል ስንዴ
አስተውል ተመልከት ጸሐፊና አንባቢ 
ያማርኛ ገበዝ የግእዝ ዐቃቢ፡፡
የግእዝን ትምርት አባይን በጭልፋ 
ቀድቶ የሚጨርስ ማነው ባለተስፋ 
ቀድቶም ባይጨርሰው ከርሱ ለሚጠጣ 
ለሚሻገረውም እየተቀናጣ፡፡
ካዋቆች ራስ ቅል የተከፈለው 
ፋጋውና ሜዴው እንሆ ይኸው፡፡ 
ዐዞውም ስንፍና ተማሪ እንዳይነጥቅ
ዋነተኛው መምር ተግቶ ይጠብቅ፡፡ 
በቀለም ገበያም ጣፊው ብር ሲቀርጥ
ፊደሉ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ፡፡
(ሄ) ሐውልታቸው - መጽሐፋቸው
በኢትዮጵያ ሕዋ እንደተወርዋሪ ኮከብ ብቅ ብለው ካለፉት እሙራንና ማዕምራን (ታዋቂዎችና አዋቂዎች) መካከል በ19ኛው በ20ኛው ምእት ዓመት ውስጥ የኖሩት አለቃ ኪዳነ ወልድ ከፍሌ አንዱ ናቸው፡፡ ዘንድሮ ከተወለዱ 142ኛ ዓመት፣ ካረፉ ከአፀደ ሥጋ ከተለዩ 70 ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡
ሥራዎቻቸው በቤተክህትም ሆነ በቤተመንግሥት ይሁንታንና ይበልታን ያገኘ፣ እስከዘመናችን ድረስም በማጣቀሻነት በማስተማሪያነት፣ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ለመሆኑ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከመዠመርያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ድርሳኖች ውስጥ ሳይጠቀሱ ያለፉበት ጊዜ የለም፡፡ ለየድርሳናቱ (ቴሲስ ዲዘርቴሽን) ምልዐት ከኪዳነ ወልድ የጽሑፍ ጎተራ ያልዘገነ ያልቀመሰ፣ ያላጠጣመ አይኖርም፡፡ 
የግእዝ ቋንቋን ከሌሎች ሴማዊ ቋንቋዎች ጋራ እያገናዘቡ በመመርመር የፊሎሉጂ ጥናት በማድረግ ረገድ በፋና ወጊነት በአገሬው ሊጠቀሱ ቢችልም፣ በዘመናችን የሳቸውን ፈለግ ተከትሎ ንፅፅራዊ ጥናት ስለመቀጠሉ የተሰማ የተጻፈ ነገር አለመኖሩን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውና ግእዝና ዐረቢኛን ብቻ መሠረት ያደረገው የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ወደ ሌሎቹም ተዛማጅ ቋንቋዎች ይሸጋገር ይሆን?
አምና የግእዝና የሱርስጥ (ሶርያ) ቋንቋዎች ጥናት ጉባኤ ያካሄደው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲና የቅዱስ ፍራንቸስኮስ የጥናትና የጽሞና ምርምር ማዕከል፣ እንዲሁም ዐውደ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ጥረትን ከተግባር ጋር ያስቀጥሉት ይሆን? የሚታይ ይሆናል፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድ ይከተሉት በነበረው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ምክንያት የሥራዎቻቸውን ያህል ተገቢውን ቦታ አለማግኘታቸው ይነገራል፡፡ የሚገባቸውን ያህል ክብርም አልተሰጣቸውም፡፡ የመቃብራቸው ምልክትም እንደጠፋ ነው የሚወሳው፡፡ 
የባሕር ማዶ ቀደምት ጠቢባንን ለመዘከር የሚተጉት አገራዊ ተቋማትና ማኅበራት ለኢትዮጵያ ዐቢይ ቁም ነገርን ትተውና በሥራ አሳይተው ያለፉትን የሚዘክሩት መቼ ይሆን? (በርግጥ ባለፈው ግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. በአንድ የዐውደ ኢትዮጵያ ሀገራዊ የጥናት ጉባኤ 70ኛ ዓመታቸውን ያሰበ መሰናዶ ሳይዘነጋ)
አምና በኬንያ ናይሮቢ ስለአፍሪካ ቲኦሎጂ የመከረ አንድ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡ በጉባኤውም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ምሁራን ተገኝተው ነበር፡፡ 
በጉባኤው የተሳተፉ ኢትዮጵያዊ ምሁር እንዳወጉን፣ በጉባኤውም በመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ዘመናት (ከአንደኛው ምእት ዓመት ተነሥቶ) በሰሜን አፍሪቃ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር በነበረው ክርስቲያናዊ ግንኙነት በርካታ መጻሕፍት በግሪክ፣ በላቲን በዐረቢኛ ተዘጋጅተዋል፡፡ የሃይማኖት መግለጫዎችም ተቀነባብረዋል ተቀምረዋል፡፡ በዘመኑም የነበረውን የአፍሪካ ቲኦሎጂ ለማወቅ ምሁራኑ በተለይ ግሪክና ላቲንን ማጥናት መመርመር አለብን ብለው ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር የመጡ ጋናዊ ምሁር ጥሩ ብላችኋል፣ ግሪክ ላቲንን ማጥናት ይገባል፡፡ የተረሱ ሁለት ቋንቋዎች አሉ፡፡ የአፍሪካን ቲኦሎጂ ለማወቅ አንድንችል የሚያደርጉ ግእዝና አማርኛን ቋንቋዎች ማጥናት አለብን በማለት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸውና ከተተረጐመባቸው የመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች አንዱ ግእዝ ነበርና እውነትነት አላቸው፡፡
ከሰማንያ ዓመት በፊት ሊቁ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ስለሁለቱ ቋንቋዎች ግእዝና አማርኛ በቅኔያቸው እንዲህ ተንብየው ነበር፡፡
‹‹እናንተ እንጂ ናችኹ ያፍሪቃ ራስ ቅል
ባለዘውድ ቋንቋ ባለነጻ አክሊል
ግእዝ ዐማርኛም ኹለቱ ቋንቆች
ታላቅ ታናሽ አባይ ያፍሪቃ ወንዞች፤
ካፍሪቃ ዐልፈው ተርፈው በባሕር በየብስ
ገና ይሰፋሉ እንደ እግዜር መንፈስ
ስላማርኛና ስለግእዝ ክብር
ዋዜማ ተቁሟል በብዙ አህጉር፡፡››  

No comments:

Post a Comment