መምህር ሰሎሞን ቶልቻ፣ በመንበረ ፓትርያርክ የቅርስ ጥበቃና የቤተ መጻሕፍት የሙዚየም መምሪያ ኃላፊ
ኢትዮጵያ ከምትታወቅባቸው ሀብቶች መካከል በኦርቶዶክሳዊቷ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚገኙት ጥንታውያን የብራና መጻሕፍትና ልዩ ልዩ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ከሃይማኖታዊ በዓላት መካከልም የልደትና የጥምቀት፣ የመስቀልና የጽዮን ማርያም እንዲሁም ሌሎች በቱሪስት መስህብነት፣ በአደባባይ በዓልነት ይታወቃሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት ሥር የተቋቋመው የቅርስ ጥበቃ፣ ሙዚየም (ቤተ መዘክር)፣ ቤተ መጻሕፍት መምርያ በቤተ ክርስቲያኒቱ ቅርስና ቱሪዝም ዙርያ እየሠራ ይገኛል፡፡ ስለ መምሪያው እንቀስቃሴ ሔኖክ ያሬድ ኃላፊውን መምህር ሰሎሞን ቶልቻን አነጋግሯል፡፡
ሪፖርተር፡- ቅርስና ቱሪዝምን የሚመለከተው ተቋማዊ አደረጃጀቱ ምን ይመስላል?
መምህር ሰሎሞን፡- በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ካሉት የተለያዩ መምርያዎች አንዱ ቱሪዝም መምሪያ ነው፡፡ አሁን ባለው አደረጃጀቱ ሰፋ ያለ አገልግሎት ይሰጥበታል፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት የቅርስ ቅርስ ጥበቃ መምሪያ ይባል የነበረው ተቋሙ የአገር ገጽታ የያዘ፣ የቤተ ክርስቲያኒቷን ማንነት የሚገልጽ፣ ህልውናዋን የሚያስጠብቅ ትውፊቷን ታሪኳን በሰፊው የያዘ መምርያ ነው፡፡ መምሪያው አገልግሎቱን የሚሰጥባቸው ልዩ ልዩ ክፍሎች አሉት፡፡ ሙዚየሙን ለመጎብኘት ለሚፈልጉ ጎብኚዎችም በነጠላና በማኅበር ተደራጅተው እንዲጎበኙና ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ተመራማሪዎች እንደፍላጎታቸው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባም ሆነ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በቤተ ክርስቲያኒቱ ሥር የተለያዩ ሙዚየሞች አሉ፡፡ በመንበረ ፓትርያርክ የሚገኘው ሙዚየም ከሌሎቹ በምን ይለያል?
መምህር ሰሎሞን፡- በአገራችን የዘመናዊ ሙዚየም ነገር የመጣው በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቢሆንም፣ በቤተ ክርስቲያናችን ግን ቅርስን በመጠበቅ ለእይታም በማብቃት ረገድ ሰፊ ልምድ አለ፡፡
በቤተክርስቲያናችን ዘመናዊ ሙዚየሞች ከመቋቋማቸው በፊት ከሺሕ ዓመታት በላይ ጥንታውያን ቅርሶች በየገዳማቱና አድባራቱ ዕቃ ቤት እና ይህንኑ ቅርስ ለመጠበቅ ታማኝ በነበሩት ሰዎች ዘንድ ይጠበቅ ነበር፡፡ አሁንም በተግባር ላይ አለ፡፡ ነገሥታቱም መሳፍንቱም በየአብያተ መንግሥቱ የጸሎት ቤት፣ የሥዕል ቤት እንዲሁም የጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ማንበቢያ ቤቶች እንደነበርዋቸውና እነዚህ ለቅርስ መጠበቅና ለትውልድ መተላለፍ ጉልህ ሚና ተጫዋተዋል፡፡ ታላላቅ ገዳሞች እንደ ሐይቅ እስጢፋኖስ፣ ደብረ ዳሞ፣ ጉንዳጉንዲ፣ የጣና ሐይቅ ደሴቶች፣ ደብረ ሊባኖስና ሌሎች ቅርሶች ተጠብቀው የሚገኙባቸው ናቸው፡፡
በአሁን ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በበላይነት ከምታስተዳድራቸው ሙዚየሞች መካከል አንዱና ዋነኛው የመንበረ ፓትርያርክ ቤተመጻሕፍት ወመዘክር (ሙዚየም) ነው፡፡ ይህ ሙዚየም በአምስተኛው ፓትርያርክ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ የአገልግሎት ዘመን ሐምሌ 6 ቀን 1996 ዓ.ም. ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ነው፡፡ ይህ መካነ ቅርስ በሌሎች አካባቢ ከሚገኙ ሙዚየሞች በሳይንሳዊ አደረጃጀቱ በታሪክ ገላጭነቱና ጥበቃው እጅግ የተለየና የሴኩሪቲ ካሜራ የተገጠመለት ነው፡፡ አገሪቷን ያሳያል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች›› የሚለውን ጥቅስ ከሚያሳየው ሥዕል ይነሳል፡፡ ሕገ ኦሪትን ጨምሮ የአገራችንና የቤተ ክርስቲያናችንን የሦስት ሺሕ ዓመታት የታሪክ ጉዞ ያሳያል፡፡ ከዘመነ አክሱም የቅዱስ ያሬድ ሥራዎች የዛጉዌ፣ የመካከለኛው ዘመን የወርቃማ ዘመንና የድቀት ዘመን ጉዞዎችም ይታዩበታል፡፡ ሌሎቹን አቆይተን የአዲስ አባባዎቹን የእንጦጦ፣ የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ፣ የጎፋ ገብርኤል የገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሙዚየሞችን ስናይ በተወሰነ ዘመን ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- የሙዚየሙ አደረጃጀት እንዴት ነው?
መምህር ሰሎሞን፡- ሙዚየሙ አራት ዋና ዋና ክፍሎች አሉት፡፡ ቀዳሚው የታሪክ ክፍል ነው፡፡ ይህ የሙዚየም ክፍል ከሕገ ልቦና ዘመን አንስቶ እስከ ሐዲስ ኪዳን ዘመን ያለውን የቤተ ክርስቲያን ታሪክ የያዘ ሲሆን ታሪኩም የቤተ ክርስቲያንን የአሣሣል ዘይቤ ተከትሎ በታሪክ ቅደም ተከተል የተደራጀና ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ በሥዕል የሚገለጥበት ክፍል ነው፡፡ ሌላው የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና የቅዱሳን ፓትርያርኮች ታሪክና ቅርስ ክፍል ሲሆን በዚህ ክፍል ውስጥ ኢትዮጵያ የራስዋን ሊቃነ ጳጳሳት መሾም ከጀመረችበት ከ1921 ዓ.ም. ጀምሮ ያሉ የብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ታሪክና ከግብፅ ቤተ ክርስቲያን ጋር የነበራትን ግንኙነት እንዲሁም የራስዋን ፓትርያርኮች መሾም ከጀመረችበት ከ1951 ዓ.ም. ጀምሮ የነበሩትን የፓትርያርኮች ታሪክና ቅርስ የሚተረክበትና የሚጎበኝበት ክፍል ነው፡፡
ጥንታውያን የቤተ ክርስቲያናችን የዜማ መሣሪያዎች የብራና መጻሕፍት፣ ዓረፍተ ዘመን የገታቸው የሊቃነ ጳጳሳት አልባሳት፣ የነገሥታት ዘውድ፣ ንዋያተ ቅዱሳት፣ የፓትርያርኮች ወንበርና የገበታ ሥዕላት የሚገኝበት ደግሞ ሌላኛው ክፍል ሲሆን ጥንታውያን የዜማ መሣሪያዎች አሠራርና መንፈሳዊ መልዕክት፣ የጥንታውያን የብራና መጻሕፍት አዘገጃጀትና ይዘት፣ የጥንታውያን ቅዱሳት ሥዕላት አሣሣልና መንፈሳዊ መልዕክት በተለየ መልኩ በስፋት ይነገርበታል፡፡ ቤተክርስቲያችን ከሌሎች አገሮች ጋር ቀደም ብላ የውጭ ግንኙነቷን ስታደርግ የቆየች ቢሆንም ይህ ክፍል ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቤተክርስቲያናችን ከሌሎች መሰል አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያደረገችውን የውጭ ግንኙነት የሚያሳይ ክፍል ነው፡፡ ክፍሉ ውስጥ አባቶቻችን በተለያየ ዘመን ከእህት አብያተ ክርስትያናትና ከሌሎች መሰል አብያተክርስቲያናት ጋር ያደረጉት ግንኙነት የተካተተ ሲሆን የቀድሞው አምስተኛው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ያደረጉት የውጭ ግንኙነት ትልቁን ድርሻ ይይዛል፡፡
በስተመጨረሻም የአምስቱ እህት አብያተ ክርስቲያናት ፓትርያርኮች ፎቶግራፍና በኢየሩሳሌም ያሉ የኢትዮጵያ ገዳማት ታሪክ የሚብራራበት ክፍል ሲሆን፣ ጎብኚዎች በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭም የሚገኙትን የቤተ ክርስቲያኑቱን ሀብት እንዲንከባከቡ ታሪካቸውንና ሃይማኖታቸውን እንዲጠብቁ ከፍተኛ ትምህርት እንዲያገኙ የሚያደርግ ክፍል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የመጻሕፍት ስብስብስ?
መምህር ሰሎሞን፡- በመምርያው ሥር ከሚገኙ ክፍሎች መካከል አንዱ ቤተ መጻሕፍት ነው፡፡ ይህ ቤተ መጻሕፍት ከሙዚየሙ ጋር አብሮ የተሠራ ሲሆን ምዕመናን የቤተ ክርስቲያናቸውን ታሪክ እንዲያውቁ የሚያደርግና በተለያዩ ቋንቋ የተጻፉ መጻሕፍት ማለትም የታሪክ፣ የባህል፣ የቋንቋ፣ የእምነት፣ የሥነ ጥበብ እና የመሳሰሉት መጻሕፍት ይገኙበታል፡፡ መጻሕፍቱ ከብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ እንዲሁም ከግለሰቦችና ከተለያዩ ድርጅቶች በስጦታና ግዢ የተሰበሰቡ መንፈሳውያን መጻሕፍት የተደራጀ ክፍል ነው፡፡
በዚህ ክፍል ውስጥ መንፈሳውያን መጻሕፍት ብቻ ሳይሆኑ የተለያዩ የታሪክ የሥነ ማኅበረሰብ፣ ሥነ ልቡና፣ ፍልስፍናና የቋንቋ መጻሕፍት የተካተቱበት ሲሆን ለጥናትና ምርምር የሚረዱ በማይክሮ ፊልም የተቀረጹ የብራናዎች ሶፍት ኮፒ ማንበቢያ፣ እንዲሁም የዲጂታል ላይብረሪ በዚህ ክፍል ውስጥ ይገኛል፡፡ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገር የሚመጡ ለሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪ መመረቂያ ድርሳን የሚሠሩ ተማሪዎች በከፍተኛ ደረጃ ይጠቀሙበታል፡፡ የብራና መጻሕፍት በዲጂታል ተቀርፀው ለአንባቢያንና ለተመራማሪዎች ዝግጁ ሆነዋል፡፡ በዶክመንቴሽን ክፍላችን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በብስራተ ወንጌል ራዲዮ የተሠራጩ ትምህርቶችና መዝሙሮች የሸክላ ቅጂዎችም አሉ፡፡
በመምሪያው ሥር ከሚገኙ ዐበይት ክፍሎች መካከል አንዱ የቁም ጽሑፍ ክፍል ሲሆን በዚህ ክፍል ውስጥ የዕድሜ ባለጸጋ በሆኑት አባቶች ብራና ፍቀው ቀለም በጥብጠው ብዕር ቀርጸው በማዘጋጀት በብዛት በሰው እጅና በሁሉም ገዳማትና አብያተክርስቲያናት የማይገኙ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት በማዘጋጀት ትውፊቱ እንዳይጠፋ ትኩረት የሚሰጥበት ክፍል ነው፡፡ የቁም ጽሕፈት ጸሐፊዎች የሙዚየሙ አንድ አካል ሆነው ብራና ላይ ሲጽፉ ለጎብኚዎች ይታያል፡፡
በዚህ ክፍል ውስጥ ጽሑፉም ብቻ ሳይሆን የአጻጻፉም ስልት ትልቅ የቤተክርስቲያን ሀብት እንደመሆኑ መጠን ይህንንም ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ተጨማሪ የቁም ጸሐፊዎችን በመመደብ የበለጠ እንዲደራጅ መምሪያው ትልቅ ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- የቅርሶች መረጃ ቋትስ ምን ይመስላል?
መምህር ሰሎሞን፡- ቅርሶችን ደረጃውን በጠበቀ በዲጂታል የመረጃ አያያዝ ዘዴ በመመዝገብ የቅርስ ምዝገባ ከማድረጉም በተጨማሪም ካታሎግና የቅርስ ምዝገባ የመረጃ ቋት ያዘጋጃል፡፡ እንዲሁም አስተማሪ ቋሚና ተንቀሳቃሽ ዐውደ ርዕይ በማዘጋጀት ለምዕመናን ያቀርባል፡፡ ጥንታውያን የብራና መጻሕፍት ለትውልድ ይተላለፉ ዘንድ ለዚሁ በተዘጋጀ መሣሪያ ወደ ሶፍት ኮፒ በመገልበጥ በጥንቃቄ ለአንባብያን እንዲደርሱ የሚደረግበት ክፍል ሲሆን ክፍሉ በተሻለ ባለሙያና መሣሪያ ከሌሎቹ ክፍሎች ልዩ ያደርገዋል፡፡
ይህ የመልቲ ሚዲያና ዲጂታላይዜሽን ክፍል በልዩ ልዩ መንገድ መምሪያው ያሰባሰባቸውን የምስል፣ የድምፅና የተንቀሳቃሽ ምስል ክምችት የያዘና አስፈላጊውን ትረካና የመግለጫ ሥራ በማከናወን እንዲሁም ዘመኑ በሚፈቅደው የቴክኖሎጂ ሥልጣኔና የመረጃ ልውውጥ ጥበብ መሠረት በማድረግ ቅርሶችን እያሰባሰበ ይገኛል፡፡
ሪፖርተር፡- የጥምቀት በዓል የዩኔስኮን (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት) መስፈርት በማሟላት ከሁሉ በፊት በዓለም ቅርስነት ለመመዝገብ የሚያስችለው ዕድል ኖሮት ሳለ እስካሁን ትኩረት አላገኘም ይባላል፡-
መምህር ሰሎሞን፡- ኢትዮጵያዊ ባህል፣ ኢትዮጵያዊ ታሪክ ስናይ ይኸ ይቅደም፣ ይኸ ይከተል የምንለው የለም፡፡ ሁሉም ቅርሶች እንዲመዘገቡልን እንደ ኢትዮጵያ ደስ ነው የሚለን፡፡ እኔ በግሌ ግን ጥምቀት በዓል ያልተመዘገበ ማን ይመዘገባል ነው የምለው፡፡ ምክንያቱም የአደባባይ በዓላችን ነው፡፡ ብዙ በዓላት አሉን፤ ጥምቀት የሚለይበት ከሃይማኖታዊ መሠረትነቱ ባሻገር የአደባባይ በዓል መሆኑ ነው፡፡ ሕፃን፣ አዋቂ፣ ሽማግሌ ደካማው ብርቱው የሚታይበት ሃይማኖታዊና ባህላዊ መገለጫዎቹ ለየት ያለ ነው፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያስተሳስሩ፣ የኢትዮጵያዊነት ወዝ ያላቸው፣ ጠቀሜታቸው የጎላና እኛነታችንን የሚገልጹ ብዙ ባህሎች አሉበት፡፡ በሃይማኖታዊነቱ የጌታ መጠመቅ ለአኛ አርአያ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ መጠመቁን የምናይበት ትልቁ በዓላችን ነው፡፡ ለክርስትና ሕይወት የጥምቀት በዓል መሠረታዊ በዓል ነው፡፡ በዩኔስኮ የማስመዝገቡን ጉዳይ ቤተ ክርስቲያኒቱ እንደተቋም የሚመለከተውን አካል ጠይቃለች፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጥምቀት በዓል በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ተጠይቋል፡፡
በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ የሚያስችሉ መስፈርቶች በባለሙያዎች እየተጠኑ ቢሆንም፣ ጥሩ ደረጃ ላይ ቢገኝም፣ ግፊቱ ግን ያስፈልጋል፡፡ የሕዝቡም ጥያቄ ነው፡፡ በትክክል ሊመዘገብና ጥበቃ ሊደረግለት የሚገባው የማንነታችን መገለጫ ነው፡፡ ክብረ በዓሉ በአገራችን ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት የዓለም ክፍሎች ሁሉ ታቦታት ወጥተው በደማቅ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሁሉ ታቦት አለ፡፡ መላው ዓለም በየአደባባዩ የሚያየው በዓል በመሆኑ ለማስመዝገብ ጥረት እያደረግን ነው፡፡
No comments:
Post a Comment