Friday, February 12, 2016

የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ዳግም ተከላ- የፋሺስት ሰለባው አቡነ ሚካኤል ሐውልትም ወደ አደባባዩ እንዲመለስ ፓትርያርኩ ጠየቁ

‹‹እግዚአብሔር ይፍታችሁ፣ እግዚአብሔር ይፍታችሁ ልጆቼ፣ ለጠላታችሁ ለፋሽስት አትገዙ ልጆቼ፣… እንኳን እናንተ መሬቷም እንዳትገዛ ገዝቻለሁ፣… እመብርሃን ብቻዬን ነኝ ትእዛዝሽ ተቆራኘኝ፣… ምሳሌን የቃል ኪዳኔ ምንጭ አርጊያት፣… አንደበቴን የእውነት ብርሃን አርጊያት፣… ልጆቼ በመንፈስ ጀምራችሁ በሥጋ እንዳታልቁ፣ ለሀገራችሁ በመልካም ፍሬ ፈንታ አሜከላ እንዳትሆኗት፣… ለጠላታችሁ፣… አትገዙ፣… እንኳን እናንተ መሬቷም እንዳትገዛ ገዝቻለሁ፣… ልጆቼ እግዚአብሔር ይፍታችሁ፤››
ከስምንት አሠርታት በፊት በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ጊዜ አራዳ ጊዮርጊስ አካባቢ በፋሺስቶች የጥይት አረር ሰማዕትነት የተቀበሉት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከመገደላቸው በፊት የተናገሩትን፣ ያስተላለፉትን ቃለ ግዝት በዚያው አደባባይ ላይ ከ80 ዓመት በኋላ ያስተጋባው አርቲስት አብራር አብዶ ነበር፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት በባቡር መስመር ዝርጋታ ሳቢያ ተነስቶ የነበረው የሰማዕቱ አርበኛ ጳጳስ - ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ጥር 29 ቀን 2008 ዓ.ም. በቀደመ ስፍራው ተተክሎ ከመገለጡ በፊት ነበር አብራር አብዶ የጸሐፌ ተውኔትና ባለቅኔ ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹ጴጥሮስ ያቺን ሰዓት›› ተውኔት አንዱን ቃለ ተውኔት የተወነው፡፡
ሐውልቱ ከጊዜያዊው መቆያ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም በዕለቱ ረፋድ ላይ ተነስቶ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጎዳና፣ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በኩል በታላቅ አጀብ በጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ሰልፈኞች፣ በካህናቱ ዝማሬና በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን፣ በፌደራል ፖሊስ ማርሽ ባንድ ታጅቦ ከጥንተ መንበሩ ከደረሰ በኋላ አቡነ ጴጥሮስ ያኔ ሰማዕትነት በተቀበሉበት 5 ሰዓት ተሩብ ላይ በመድረስ የማቆሙና የመግለጡ ተግባር ተከናውኗል፡፡ በነቂስ የወጣውም ኅብረተሰብ ወንዱ በሆታ ሴቱ በዕልልታ ደስታውን ገልጿል፡፡
በአደባባዩ ከተገኙት መካከል የዘጠና ዓመቷ አረጋዊት እማሆይ አበበች ኃይሌ አንዷ ናቸው፡፡ ከ80 ዓመት በፊት አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕትነት ሲከፍሉ ተመልክተዋል፡፡ በ10 ዓመታቸው ከሚኖሩበት ጣሊያን ሰፈር (ደጃች ነሲቡ ሰፈር) በእናታቸው ኋላ ተከትለው ሄደው የተደረገውን ሁሉ ተመልክተዋል፡፡ እንዲህም አስታውሰዋል፡-
‹‹የድሮ ጭቃ ሹሞች እንዲህ ያለ ቦታ ተሰብሰቡ እያሉ ጥሩምባ ያስነፉ ነበር፡፡ አቡነ ጴጥሮስ እንደሚገደሉ ሲለፈፍና እናቴም በተጠሩበት ሰዓት ሲወጡ እኔ ከኋላቸው እየተከተልኩ ሄድኩ ታናናሾቼም አሉ፡፡ እርሻ ሚኒስቴር ሆኜ እሳቸው [አቡነ ጴጥሮስ] በተገደሉበት ቦታ ጠጋ እንዳልኩ እናቴ አልፈው ሄዱ፡፡ ጥይቱ ሲንጣጣ ተሰማ እሩምታው ካለቀ በኋላ ሸሽቼ እያለከለክሁ ገባሁ፡፡››
እማሆይ አበበች ‹‹ዕድሜ ሰጥቶኝ በዓይኔ ለማየት አበቃኝ›› እንደሚሉት  ከ70 ዓመት በፊት ሐምሌ 1938 ዓ.ም. አዲሱ ሐውልት ሲመረቅ ተመልክተዋል፡፡ ከ80 ዓመት በኋላም ሐውልቱ ዳግም ሲተከል እማኝ ሆነዋል፡፡ ከሦስት ዓመት በፊት የሆነውን ከአሁን ጋር አዛምደውም ያስታውሳሉ፡፡
‹‹ሐውልቱ ከተነሳ በኋላ ሄድኩ፤ አልተሸበርኩም፡፡ ተመልሶ እንደሚቆም ሙሉ ለሙሉ እምነቱ ነበረኝ፡፡ በፍጹም አላዘንኩም ሲነሳ፡፡ አንስተው ሳይመልሱት ይቀራል የሚል ጥርጣሬ አልገባኝም፡፡ ምክንያቱም ቅርስ ነው፣ ሐውልት ማለት ትልቅ ነገር ነው፡፡››
እማሆይ ለእንግዶች በተዘጋጀው ዳስ ውስጥ በአዘጋጅ ኮሚቴው አማካይነት እንዲቀመጡ ቢደረግም ‹‹እንግዶች አሉብን›› በሚል እንዲነሱና ከአደባባዩ አንዱ ጥግ እንዲቆሙ መደረጋቸው ከቁብም አልቆጠሩትም፡፡ ‹‹ቅር አላለኝም፤ ደስታዬ ሐውልቱ ተተክሎ ማየቴ ነው፤›› ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከንቲባ ድሪባ ኩማን ጨምሮ ከፍተኛ ሹማምንት በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርና የሐውልቱ አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዮናስ ደስታ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ የሐውልቱ ተከላ በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችና የቴክኒክ ኮሚቴ ተከናውኗል፡፡ በራስ አቅም ቅርሶችን መጠበቅ እንደሚቻል ተምረንበታልም ብለዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ለሊቀ ጳጳሱ የሰማዕትነት ክብር መስጠቷንና በንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አማካይነት ሰማዕነትን በተቀበሉበት ቦታ ለሀገርና ለነጻነት የከፈሉትን የሕይወት ዋጋ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በየትውልድ ዘመኑ እንዲዘክሩትና እንዲማሩበት የመታሰቢያ ሐውልት ማቆማቸውን ያስታወሱት የክብር እንግዳው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ለባቡር መንገድ ሥራ ሲባል ከሦስት ዓመት በፊት ከቦታው ተነሥቶ የነበረውን ሐውልት በክብርና በታላቅ ሥነ ሥርዓት መመለሱ መንግሥትን ያስመሰግነዋል ብለዋል፡፡
ቅዱስ ፓትርያርኩ አያይዘውም፣ እንደ ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በተመሳሳይ ሁኔታ በጎሬ ከተማ በ1929 ዓ.ም. በፋሽስት ኢጣሊያን በግፍ የተገደሉት ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤልም ለሀገር ክብርና ነጻነት የከፈሉትን የሕይወት ዋጋ ትውልዱ ሁሉ እንዲዘክረውና እንዲማርበት በቅዱስ ሲኖዶስ አማካይነት የተዘጋጀው ሐውልታቸው ሰማዕትነትን በተቀበሉበት ቦታ በጎሬ ከተማ በክብር እንዲመለስና እንዲቆም ለሚመለከተውና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ሰማዕቱ ብፁዕ አቡነ ሚካኤል በ1921 ዓ.ም. ከነአቡነ ጴጥሮስ ጋር ሲጰጵሱ መቀመጫቸው ኢሉባቡር ጎሬ ሆኖ ‹‹ጳጳስ ዘምዕራብ ኢትዮጵያ›› በመባል ነበር፡፡
ከሰማንያ ዓመት በፊት በሐምሌ ወር ሰማዕት የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ የኢጣሊያ ፋሺስት በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነትን ባነሣ ጊዜ ከጦሩ ባለመለየት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሔደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሰላሌ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡
አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች በሰሜናዊ ምዕራብና በደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺስት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፣ ሕዝቡም ሆነ አገሪቱ ለፋሺስት ኢጣሊያ እንዲገዙ እንዲቀሰቅሱ ቢያዛቸውም፣ ‹‹እምቢ ለአገሬና ለሃይማኖቴ›› ብለው ሕዝቡ ለፋሺስት  ኢጣሊያ እንዳይገዛ በማውገዛቸው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. መቀበላቸው ይታወቃል፡፡ ከድል በኋላ ‹‹በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስለመታሰቢያ የቆመ ሐውልት›› የሚል ጽሑፍ ያለበት በጥይት በተደበደቡበት ቦታ (በቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ባሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ፋኩልቲ አጥር ጥግ) ሰማዕት በሆኑ በአምስተኛው ዓመት ሐምሌ 22 ቀን 1933 ዓ.ም. አነስተኛ ትክል ድንጋይ ቆሞላቸዋል፡፡ እንዲሁም ሐምሌ 16 ቀን 1938 ዓ.ም. ግዙፍ ሐውልት እንደቆመላቸው ይታወቃል።
በፋሺስት ኢጣሊያ ከ80 ዓመታት በፊት ሰማዕት የሆኑት አቡነ ጴጥሮስ የተቀበሩበት ቦታ በአዲስ አበባ በስተደቡብ በለቡ አካባቢ ከአምስት ዓመት በፊት መገኘቱን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ማስታወቋ ይታወሳል፡፡ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የፉሪ ምስካበ ቅዱሳን አቡነ ተክለ ሃይማኖትና መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን በወቅቱ ለሪፖርተር እንዳስታወቀችው፣ አቡነ ጴጥሮስ ሰማዕት ከሆኑ በኋላ የተቀበሩት ፋሺስቶች በመኖርያነትና በእስር ቤትነት ይጠቀሙበት በነበረው ‹‹ሙኒሳ ጉብታ›› ላይ ነው፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ኃይል በሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ሰማዕቱን ገድሎ አስክሬናቸውን አደባባይ ላይ ጥሎ ከዋለ በኋላ፣ ቀብራቸው በምስጢር መፈጸሙን መዛግብት እንደሚያስረዱ ያስታወሰችው ቤተ ክርስቲያኗ፣ የእኚህ ታላቅ አባት ቀብር በምስጢር የተፈጸመበት ቦታ ለማግኘት የተለያዩ ምሁራን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ የታሪክ ሰነዶችን ሲመረምሩ ቢቆዩም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ “ከአዲስ አበባ በስተደቡብ በምስጢር ቀበሯቸው” ከሚል ጠቅላላ ፍንጭ ያለፈ ምንም ዓይነት የተረጋገጠ ማስረጃ ሳይገኝ ቆይቶ ነበር ፡፡
ከአራዳ ጊዮርጊስ በታች የቆመው  የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሁለተኛው ሐውልታቸው ሲሆን፣ የመጀመሪያው ሐውልት የኢትዮጵያ ጳጳሳት የአለባበስ ትውፊትን ያልተከተለ በመሆኑ ተነቅሎ በመናገሻ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አፀድ እንዲገባ መደረጉ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ የራሷን አራት ጳጳሳት በ1921 ዓ.ም. በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመን ስታስሾም አንዱ አቡነ ጴጥሮስ ነበሩ፡፡ በ1875 ዓ.ም. በሰላሌ ፍቼ የተወለዱት አቡነ ጴጥሮስ፣ ‹‹ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ” ተብለው፣ ‹‹ራሱ በሽሎ መለስ፣ እግሩ አቦክ ፈረንሳዊ ወሰን ድረስ (ጅቡቲ)›› 21 አካባቢዎችን ያስተዳድሩ ነበር፡፡
አቡነ ጴጥሮስ ገጸ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው፣ በትምህርት ዝግጅታቸውም እንደ ጥንታዊው የቤተ ክርስቲያኗ ሥርዓተ ትምህርት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በተወለዱበት አካባቢ አጠናቀዋል፡፡ የቅኔ ትምህርታቸውን ለማስፋፋት ዋሸራ (ጎጃም) በመዝለቅ በመምህርነት ተመርቀዋል፡፡ ዜማን በጎንደር፣ ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ (ብሉያት፣ ሐዲሳትና ሊቃውንት) ትምህርቶችን በብቃት አስሒደውታል፡፡
በ1900 ዓ.ም. በአማራ ሳይንት (ወሎ)  ምስካበ ቅዱሳን ገዳም ወንበር ዘርግተው ለዘጠኝ ዓመት ቅኔና መጻሕፍትን ካስተማሩ በኋላ በ1909 ዓ.ም. ሥርዓተ ምንኩስናን በደብረ ሊባኖስ ገዳም ፈጽመዋል፡፡ በወላይታና በዝዋይ ገዳማት በ1919 ዓ.ም. አዲስ አበባ በመምጣት ስድስት ኪሎ በሚገኘው የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መምህርና የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንስሐ አባት ነበሩ፡፡
በሔኖክ ያሬድ ዘሪፖርተር (የካቲት 2 ቀን 2008 ዓ.ም. )

No comments:

Post a Comment