Sunday, February 28, 2016

ከጳጉሜን 6 በኋላ ፌብሪዋሪ 29!ከጳጉሜን 6 በኋላ ፌብሪዋሪ 29! - ሠግረ ዕለት- (leap day)- ሠግረ ዓመት (leap year)
የዛሬዋ ፌብሪዋሪ 29! ከአራት ዓመት በኋላ ከች አለች! የጎርጎርዮሳዊው ቀመር የዘንድሮ ዓመት 366 ቀኖችን እንዲይዝ ታደርጋለች፡፡
እኛ ባመቱ መካተቻ (366ኛ) የዕለት ሠግር ስናደርግ እነሱ በዓመቱ ሁለተኛ ወር ማጠቃለያ (60ኛ) ላይ ያደርጓታል፡፡

Saturday, February 27, 2016

የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን የሚገልጠው መዘክር

 20 የካቲት 2008 በሔኖክ ያሬድ
በኢትዮጵያ ‹‹ከ80 በላይ ብሔር ብሔረሰቦች›› ይኖራሉ እየተባለ በተለይ ከሩብ ምእት ዓመት ወዲህ ከመንግሥት ለውጥ በኋላ ሲነገር ይሰማል፡፡ በአገሪቱ ያሉት ብሔረሰቦች ቁጥር በርግጥ ስንት ነው የሚለውን ለመወሰን በተለይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ባህሎች አካዴሚና በፌዴሬሽን ምክር ቤት አማካይነት እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑ ከተነገረ ቆይቷል፡፡
የ1966ቱን የኢትዮጵያ አብዮት ተከትሎ የተመሠረተው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) ብሔረሰቦችን በተመለከተ ካከናወናቸው ተግባራት አንዱ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩትን መመሥረቱና የተለያዩ ጥናቶች ማድረጉ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሠፓአኮ) /1972 - 1976/ በቀጣይነትም በኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ (ኢሠፓ) /1977 - 1983/ ሥር የብሔረሰቦች ጉዳይን በሚመለከተው መምርያ ሥር ይመራ የነበረው ኢንስቲትዩቱ ብሔረሰቦች ብዛታቸውን፣ ዓይነታቸውንና አሰፋፈራቸውን አጥንቶ መሰነዱና ለሚመለከተው አካል ማቅረቡ ይታወቃል፡፡
በዘመኑ ለአንባብያን ያልቀረበው የጥናት ውጤት መሰንበቻውን በወቅቱ ከነበሩት የዩኒቨርሲቲ ምሁራን አጥኚዎች መካከል አንዱ ዶ/ር ፍሥሐ አስፋው ‹‹የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን የሚገልጥ ጥናታዊ መዘክር - ብዛት፣ ምንነት፣ ማንነትና አሰፋፈር›› በሚል ርእስ አሳትመው ለአንባቢያን አድርሰዋል፡፡
ዶ/ር ፍሥሐ በመግቢያቸው ላይ እንደገለጹት፣ የዚህ ‹‹የብሔረሰቦች ማወቂያ›› በመጽሐፍ መልክ አሳትሞ ለሕዝብ እንዲደርስ የተደረገበት ዓላማው የአሁኑ ትውልድ ስለ ኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የሚያነበውና የሚሰማው ግለሰቦች ወይም የተወሰኑ ቡድኖች ከራሳቸው የግል አመለካከትና ከሚያገኙት የፖለቲካ ተረፌታ በመነሳት ከሚጽፉትና ከሚናገሩት ስለሆነ ይሄን በሐቅና በጥንቃቄ የተጠና የመስክ ጥናት በመመልከት ሙሉና እውነተኛ መረጃ በማግኘት ስለ ሀገሩ ሕዝቦች እውነቱን እንዲያውቅ ለማድረግ ነው፡፡
በተጨማሪም ለመጪውም ትውልድ የታሪክ መዛግብት እንዲሆንና ኢትዮጵያዊ ነኝ ሲል ምን ዓይነት ኢትዮጵያዊ እንደሆነና ታሪኩም ሆነ ባህሉም በአንድ፣ በሁለት ወይም በሦስት ብሔረሰቦች ብቻ የተገነባ አለመሆኑን እንዲያውቅ ለማድረግም መጻፉን አዘጋጁ ገልጸዋል፡፡
መጽሐፉ የኢትዮጵያን ብሔረሰቦች ሥርጭት በጥቅል መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ በሦስት ረድፎች ከፍሎታል፡፡
አንደኛው ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው፣ ሰፋፊ አካባቢ የያዙ፣ በኢኮኖሚ የዳበሩና በተመጣጣኝ የባህል ዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ፣ ከሰሜን እስከ ደቡብ ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ባለው ደጋማ መሀል አገር የሚኖሩ ብሔረሰቦችን አማክሏል፡፡
ሁለተኛው እነዚህን ባለብዙ ሕዝብ ብሔረሰቦች እያጐራበቱና እያዋሰኑ፣ በደቡብ ምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ እንደዚሁም በሰሜን ምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ጠረፎች ዙሪያ የሚኖሩ፣ በኢኮኖሚ ኋላቀር የሆኑ ገና በዝቅተኛ የባህል ዕድገት ደረጃ ላይ የሚገኙ፣ የሕዝባቸው ብዛት ከጥቂቶች በቀር በጣም አነስተኛ የሆነ አናሳ ብሔረሰቦች ያላቸው ብሔረሰቦች እንደሚኖሩ አመላክቷል፡፡
ሦስተኛው በኢኮኖሚና በባህል ዕድገታቸው ከእነዚህ በአንደኛው ረድፍ ከተጠቀሱት ብሔረሰቦች የሚነጻጸሩ፣ ብዙዎቹ መለስተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው በመጀመሪያዎቹ ብሔረሰቦች በከፊል በመከበብ፣ ወይም በሙሉ በመታቀፍ፣ በአንዳንድ አካባቢ ደግሞ በጠረፍና በመሀል ሀገር በሰፈሩት ብሔረሰቦች መካከል የሚገኙ ብሔረሰቦች እንዳሉ ጠቅሷል፡፡
ከ574 ወረዳዎች የተሰበሰቡ መረጃዎችን በያዘው መጽሐፍ የመጀመሪያ ክፍል የ75 ብሔረሰቦች ምንነት፣ ማንነትና አሰፋፈር በአጭሩ ተገልጽዋል፡፡ በአባሪነት በሰፈረው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ስም ዝርዝር መግቢያ ላይ ኢንስቲትዩቱ ካሰባሰበው መረጃዎች አንፃር የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ዝርዝር 89 ይደርሳል፡፡ ይሁን እንጂ አኀዙ የመጨረሻ እንደማይሆንና ቁጥሩ ሊጨምርም ሆነ ሊቀንስ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ የሁሉም ብሔረሰቦች የስም ዝርዝር የተጻፈ ሲሆን፣ ትግርኛ ተናጋሪ ኤርትራና ትግራይን ‹‹ትግራይ ትግርኝ›› በሚል አስቀምጦታል፡፡
የብሔረሰቦቹ ቁጥር ይፋ አኃዝ ሳያገኝ በመውጣትና በመውረድ ላይ መገኘቱ  የተለያዩ ምክንያቶች ሲኖሩ ዋናው የብሔረሰቦች ስያሜ አለመጣራት ነው፡፡ ከጥቂት ብሔረሰቦች በቀር ሁሉም ብሔረሰቦች እያንዳንዳቸው አያሌ መጠሪያ አላቸው፡፡ አንድ ብሔረሰብ ራሱ የሚቀበለውና የሚያምንበት አንድ ስም ሲኖረው ሌሎች የሰጡት ስያሜ አለው፡፡ የቋንቋና የስነ ሰብ ምሁራን ያወጡለት ሌላ መጠሪያ ይኖረዋል፡፡ ስለሆነም እንደዚህ ያለው ድርብርብ ስምና መጠሪያ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችን ቁጥር ሊያበዛው ችሏል፡፡ አንዳንድ ብሔረሰብ በታሪክ፣ በባህል፣ በቋንቋ ተመሳሳይ ሲሆኑ በስያሜ ይለያያሉ ይላል ጥናታዊው ድርሳን፡፡

Wednesday, February 24, 2016

‹‹አትርሱት አንርሳው …››

ራስን ካንገት ላይ ቆራርጦ እየጣለ
በችንካር ቸንክሮ ሰው እየገደለ
ሰውን ከነቤቱ አብሮ እያቃጠለ
ማነው እንደ ፋሽስት በሰው ግፍ የዋለ?
ሥጋችንን ገድለው ሊቀብሩት ከጀሉ
በዚህ ያልነበሩ ሐሰት እንዳይሉ
እሊህ አስክሬኖች ይመሰክራሉ፡፡
ይህን ታላቅ ስቃይ መከራና ግፍ
ሲያስታውስ ይኖራል የታሪክ መጽሐፍ
አትርሱት አንርሳው ያስታውሰው ዘራችን
ኢጣሊያ መሆኗን መርዛም ጠላታችን፡፡
እላንት አእጽምቶች ዕድለኞች ናችሁ
በኃይለ ሥላሴ ትንሣኤ አገኛችሁ፡፡
ከ79 ዓመት በፊት (ሰማንያ ፈሪ) በፋሺስት ኢጣሊያ ጭፍራ ማርሻል ሮዶልፎ ግራዚያኒ አማካይነት በአዲስ አበባ ከተማ ለሦስት ቀናት በዘለቀው ጭፍጨፋ ሰማዕት ለሆኑት 30 ሺሕ ኢትዮጵያውያን በቆመው ሐውልት ግርጌ የሰፈረ የወል ቤት ግጥም ነው፡፡
ቅዳሜ የካቲት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. የሰማዕታቱ ዕለት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲዘከር በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አማካይነት በ1934 ዓ.ም. በካቴድራሉ አፀድ ውስጥ በተተከለው የሰማዕታቱ አፅሞች ማረፊያ አርበኞች ተሰባስበው በጸሎትና በትውስታ አስበውታል፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ 14ኛ ዓመት የዘውድ በዓላቸውን ሐሙስ ጥቅምት 23 ቀን 1937 ዓ.ም. ሲያከብሩ በተመረቀውና ለአርበኞችም የተጋድሎ ሜዳሊያ ባበረከቱበት አዲሱ ሐውልት ግርጌ በግእዝ ቋንቋ የተጻፈው ጽሑፍ ዘመነ ፍዳውን የሚያስታውስ ነው፡፡
‹‹ዝንቱ ውእቱ ምዕራፈ አዕጽምቲሆሙ ለብዙኃን ኢትዮጵያውያን እለ ተቀትሉ በግፍዕ በእደዊሆሙ በሕዝበ ኢጣሊያ ፋሽስታውያን አመ ፲ወ፪ ለየካቲት በ፲ወ፱፻፳ወ፱ ዓ.ም …›› ይህ የአፅሞች ማረፊያ በኢጣሊያ ፋሽስታውያን እጅ በግፍ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. የተገደሉ የብዙኃን ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ ነው፤ በሚል የሚንደረደረው የሐውልቱ ጽሑፍ አገዳደላቸው በድንጋይ በመወገር፣ በዱላ በመቀጥቀጥ፣ በአካፋ፣ በዶማ በመብረቀ ሐፂን/የብረት መብረቅ (መትረየስ)፣ በየቤታቸው ውስጥ በእሳት በመቃጠል፣ ወዘተ እንደሆነ ይዘረዝራል፡፡ የግፍ አገዳደሉ በተፈጸመ በአራተኛው ዓመት ከብሪታኒያ በድል አድራጊነት የተመለሱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የነፃነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ካቆሙ በኋላ በግፍ የተገደሉትን አፅሞች ከየቦታው እንዲሰበሰቡ ሹማምንቱን በማዘዝ ለዝክረ ነገር እንዲሆንም በቅዱስ ስፍራም መታሰቢያውን አቆሙላቸው፡፡
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ከ1848 እስከ 1966›› በተሰኘውና በ1989 ዓ.ም. በታተመው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የኢጣሊያ ፋሺዝም ጽልመታዊ ገጽታ ቁልጭ ብሎ የወጣው በየካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. ነው፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም የተባሉ ሁለት ወጣቶች በግራዚያኒ ላይ ቦምብ ጥለው ካቆሰሉት በኋላ አዲስ አበባ ላይ መዓት ወረደባት፡፡ ‹‹ጥቁር ሸሚዝ›› እየተባሉ የሚታወቁት የፋሽስት ደቀመዛሙርት መንግሥት አይዟችሁ እያላቸው አዲስ አበባን ቄራ አደረጓት፡፡ የሰው ልጅ ጭንቅላት እንደ ዶሮ እየተቀነጠሰ ወደቀ፡፡ ቤቶች ከነነዋሪዎቻቸው ጋዩ፡፡ እርጉዝ ሴቶች በሳንጃ ተወጉ፡፡ የጭፍጨፋው ተቀዳሚ ዒላማ የተማሩ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ በተለይም የጥቁር አንበሳ አባላት ከራስ እምሩ ጋር እጃቸውን ከሰጡ በኋላ በከተማይቱ ይገኙ ስለነበር በወረንጦ እየተለቀሙ ተረሸኑ፡፡ ይህ የምሁራን ጭፍጭፋ አንድ ትውልድ እንዳለ ያጠፋ በመሆኑም ባገሪቱ የፖለቲካና ምሁራዊ ታሪክ ላይ የማይሽር ቁስል ጥሎ አለፈ፡፡
የዓይን እማኙ ‹‹ሊቀ ጠበብት እውነቱና የካቲት 12›› የተሰኘ ጽሑፍ የጻፉት ተመስገን ገብሬም እንዲህ ጽፈዋል፡- ‹‹ከሦስት ቀን የከተማ ጥፋት በኋላ ከሆለታ የመጡ የፋሽስት አውሬዎች በሚመለሱበት ካሚዮን በኋላው በኩል አቶ አርአያን እግራቸውን ጠርቅመው አሰሯቸው፡፡ ካሚዮኑ ሳይጐትታቸው ‹እኔ ወደ ሰማይ እንድገባ ሰማይ ተከፍቶ ይጠብቀኛል፡፡ ኢየሱስንም በዚያ አየዋለሁ፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ ደስ ይለኛል!› የሚለውን የሚሲዮን መዝሙር ዘመሩ፡፡ ፋሽስቶቹም የተሻለውን መዝሙር ብትሰማ ይሻልሃል አሏቸውና ዱኪ ዱኪ የሚለውን መዝሙራቸውን ዘመሩ፡፡ ካሚዮኑም ሞተሩን አስነስቶ ሲነዳ ታስረው ቁመው ነበርና ያን ጊዜ ዘግናኝ አወዳደቅ አቶ አርአያ ወደቁ፡፡ ካምዮኑም እየፈጠነ ጐተታቸው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ሆለታ አርባ ኪሎ ሜትር ይሆናል፡፡ ካምዮኑ ከዚያ ሲደርስ ያ ከካሚዮኑ ጋር የታሰረው እግራቸው ብቻ እንደተንጠለጠለ ነበርና የካሚዮኑ ነጂ ከካሚዮኑ ፈታና ለውሾች ወረወረው፡፡ እኔንም ያለሁበትን ቤት ሰብረው ከዚያ ቤት ያለነውን አውጥተው ከየመንደሩም ሕዝቡን አጠራቅመው ኑረዋል፡፡ ከዚያም መሐል ጨመሩን፡፡
‹‹ስምንት መትረየስ በዙሪያችን ጠምደዋል፡፡ በዚያም ቦታ ቁጥራቸው በብዙ የሆኑ ሐበሾችን አስቀድመው ገለዋቸዋል፡፡ ሬሣቸውም ተቆላልፎ በፊታችን ነበረ፡፡ እኛንም በዚያ ሊገድሉን ተዘጋጁ፡፡ ለመትረየስም ተኩስ እንድንመች ያንዳችንን እጅ ካንዱ ጋር አያይዘው አሰሩን፡፡ አሥረውን ወደ መተኰሱ ሳይመለሱ አንድ ታላቅ ሹም መጣ፡፡ የርሱም ፖለቲካ ልዩ ነበረ፡፡ ፋሽስቶች የሚያደርጉትን የሰላማዊ ሕዝብ መግደል፤ ሕፃናቶችን ከአባትና እናታቸው ጋራ በቤት ዘግቶ ማቃጠል መልካም ብሎ ቢወድ እንኳን እኒያ ቦምብ በቤተ መንግሥቱ ስብሰባ የወረወሩት ሐበሾች ሳይታወቁ እንዲቀሩ አይወድም ነበርና ስለዚህ ካሚዮኖች ይዞ እየዞረ ፋሽስቶች የሚገድሉትን እያስጣለ ወደ እስር ቤት ለምርመራ ይወስድ ኑረዋል፡፡ እኛንም እንዲተኮስብን ታሰረን ከቆምንበት ከቅዱሰ ጊዮርጊስ ጠበል አጠገብ ካለው ሸለቆ እስራታችንን አስፈትቶ በአምስተ ረድፍ ወደላይኛው መንገድ ለመድረስ ስንሄድ በአካፋ ራሳቸውን የተፈለጡ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፡፡ ምራቄ ደረቀ፡፡ በካሚዮኑ ወደ እስር ቤት አስወሰደን፡፡ ለጊዜው እስር ቤት ያደረጉት ማዘጋጃ ቤትን ነበር፡፡››
ስድስት ኪሎ በሚገኘው የያኔው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ያሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በወቅቱ የነበረውን የፋሽስት ኢጣሊያን ጭፍጨፋ የታዘበው ሀንጋሪያዊው ሐኪም ዶ/ር ላዲስላስ ሳቫ ዓይኑ ያየውንና የታዘበውን በማስታወሻው መግለጹን በጳውሎስ ኞኞ ‹‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት›› መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተመልክቷል፡- ‹‹…ከዚህ በኋላ በግቢውና በአካባቢው ወዲያውኑ ጅምላ ጭፍጨፋ ተጀመረ፡፡ … በገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ግቢ ውስጥ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን አንድም በሕይወት የተረፈ ሰው አልነበረም፡፡ ቦታው ላይ የተካሄደው የጅምላ ጭፍጨፋ የተሰበሰቡት ሰዎች ዕድሜያቸው የገፋ፣ ዓይነ ስውራን፣ አካል ጉዳተኞች፣ የኔብጤዎችና ሕፃናትን የያዙ ድሃ እናቶች ስለነበሩ በዚህ ቦታ የተፈጸመው ሰቆቃ ትርጉም የሌለው፣ የሚሰቀጥጥና የሚያሳፍር ነበር፡፡››
የሰማዕታቱ ቀን በወቅቱ የነበሩ እናት አርበኞች፣ የመዲናይቱ ነዋሪዎች በተገኙበት ሲከበር የአበባ ጉንጉን ያስቀመጡት የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ዶ/ር ታቦር ገብረመድኅንና የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ናቸው፡፡
‹‹የአካፋው ሚካኤል›› እየተባለ የሚታወቀውን የሰማዕታት ዕለት ከቀድሞው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተጎራበተው መንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያንም ሰማዕታቱ ካህናትና ምዕመናን፣ ሊቃውንት በተገኙበት በጸሎትና በዝማሬ ታስበዋል፡፡Friday, February 19, 2016

ስብሐት ሲሔድ

በሔኖክ ያሬድ
‹‹ተረት ተረት
‹‹የላም በረት››
‹‹አንዲት ሴትዮ ነበረች››
‹‹እሺ!››
‹‹ስትኖር ስትኖር ታመመችና ሞተች፤ ተቀበረች፤
ይህ የሁላችንም የሕይወት ታሪክ ነው፤››
ደራሲ ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ›› በተሰኘው ልብ ወለዱ ላይ በጽሕፈት ዓለም ውስጥ በነበረበት ጊዜ የከተበው ነበር፡፡
‹‹አንዲት ሴትዮ ነበረች›› አለና የእርሷን ሕልፈት ሲያረዳ የቋጨውም ‹‹የሁላችንም የሕይወት ታሪክ ነው፤›› በማለት ነው፡፡ ከትናንት በስቲያ ሕልፈተ ሕይወቱን ተከትሎ ከአጸደ ሥጋ ተለይቶ ግብአተ መሬቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የተፈጸመው ደራሲው ስብሐት፣ በስመ ጥምቀቱ ‹‹ስብሐት ለአብ›› ኖሮ ኖሮ ታሞ ቢያልፍም፣ ቢቀበርም፣ የብርዕ ትሩፋቱን በተለያዩ መልኮች አስተላልፏል፡፡ ጽልመት ውስጥ የነበሩት ብርሃን ከትቦባቸው ወጥተዋል፡፡ አንዳንዶቹም ከዕድር፣ ከአነዋር የወጡ አወዛጋቢ ሆነዋል፡፡
አምስት ስድስት ሰባትትኩሳትሌቱም አይነጋልኝ፣ ሰባተኛው መልአክ፣ እግረ መንገድ፣ እነሆ ጀግና፣ የፍቅር ሻማዎች፣ ዛዚ (ትርጉም) የተሰኙትን ደረሰ፤ ተረጐመ፤ አሳተመ፡፡ በቀለም አበባ ይዘከርና፡፡
ከሰባ ስድስት ዓመት በፊት የፋሺስት ኢጣሊያ ሠራዊት አዲስ አበባን ወርሮ በያዘበት ዕለት ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ዓድዋ ርባ ገረድ በሚባለው ቦታ የተወለደው ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር፣ የመዠመርያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኰንን ሲከታተል፣ በሥነ ትምህርት (የማስተማር ሙያ) የመዠመርያ ዲግሪውን ከዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ (አዲስ አበባ) አግኝቷል፡፡ ቢኤ ዲግሪው ስንቅ ሆኖት ካዛንቺስ ቶታል አካባቢ በሚገኘው አሰፋ ወሰን ትምህርት ቤት ለአራት ዓመታት (1953-56) የእንግሊዝኛ መምህር ነበር፡፡ ከማስተማሩም ተሻግሮ በትምህርት ሚኒስቴር ባልደረባ ሆኖ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል ባልደረባ ሆኖ አገልግሏል፡፡ በሰባት ዓመት ዕድሜው በዕረኝነት የተጀመረው የሥራ ልምዱ ከትምህርትና መምህርነት በኋላ የቀጠለው እስከ ኅልፈቱ የዘለቀበት ጋዜጠኝነቱ ነው፡፡
ከ44 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ጀግኖች ማኅበር የእንግሊዝኛው መጽሔት አዘጋጅነት የተዠመረው ጋዜጠኛነቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ተወዳጅ የነበረችውና፣ በሀገር ፍቅር ቴአትር ሥር ትታተም የነበረችው መነን መጽሔት፣ በይቀጥላልም በኢትዮጵያን ሚረር በአዲስ ሪፖርተር አዘጋጅና ጸሐፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡
በ1960ዎቹ በነበረችው ቁም ነገር መጽሔት፣ በኋላም በየካቲት፣ የአማርኛና እንግሊዝኛ መጽሔቶች፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ‹‹እግረ መንገድ›› (እሑድ) እና ‹‹አንድ ሺሕ አንድ ሌሊት›› (ዓርብ)›› ዐምዶቹ፣ እፎይታ፣ አዲስ አድማስ የብዕር ትሩፋቶቹን ለአንባቢያን አድርሷል፡፡ ስብሐት ከተረኮቹ አንዱ የሆነው ‹‹ሞትና አጋፋሪ እንደሻው›› የብዙዎችን ቀልብ የያዘ፣ ለበዓሉ ግርማ ድርሰትም መነሻ የኾነ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ይጽፍበት ከነበረው ቁም ነገር መጽሔት ያፈናቀለው ይኸው የአጋፋሪ እንደሻው ተረክ ነው፡፡
የስብሐትን ምልዐተ ታሪክ እስከ ስድሳ አምስት ዓመት ዕድሜው ድረስ ያለውን ‹‹ማስታወሻ›› በሚል ርእስ ለትውልድ ያስተላለፈው ደራሲና ጋዜጠኛው ዘነበ ወላ ገለታው ይድረሰውና የስብሐትን ጣጣ እንዲህ ከትቦታል፡፡
‹‹ከቁምነገር መጽሔት እንዴተ ተሰናበትክ?››
‹‹በአንድ ቀን ቁራጭ ወረቀት ከሳንሱር ጽሕፈት ቤት አካባቢ ተጻፈልኝ፡፡ በዚያን ጊዜ የምጽፈው በአጋፋሪ እንደሻው ላይ ነበር፡፡ የደረሰኝ ማስጠንቀቂያ ‹የወዛደሩን ልዕልና የሚያሳይ ካልሆነ ቀልድ ክልክል ነው› ይላል፡፡››
ከትግርኛና አማርኛ ሌላ በእንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ የሚጽፈው፣ ገጣሚም የኾነው ደራሲው ስብሐት፣ ከድርሰቶቹ መካከል ‹‹ሌቱም አይነጋልኝ›› በፈረንሣይኛ ሲተረጐም፣ አጫጭር ጽሑፎቹ የተካተቱበት ‹‹ዘ ሲድ›› የተሰኘ መጽሐፍም በእንግሊዝኛ ታትሞለታል፡፡
የካቲት 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ከቀኑ 10 ሰዓት የስብሐት ወዳጅ ዘመዶች፣ አድናቂዎች በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሽኝት ሊያደርጉለት ተሰብስበዋል፡፡ በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ መሪነት የተካሔደው ጸሎተ ፍትሐት በስመ ጥምቀቱ ‹‹ስብሐት ለአብ›› ለተሰኘው ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ጸሎት እያደረሱ ነው፡፡ ‹‹ከመ መሬት ንሕነ…›› እያሉ በግእዙ ያደርሱታል፡፡
‹‹አቤቱ እኛ አፈር እንደሆንን አስብ፡፡ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነው፤ እንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል፤ ነፋስ በነፈሰበት ጊዜ ያልፋልና፡፡ ስፍራውንም ደግሞ አያውቀውምና፡፡››
ከካቴድራሉ አጸድ ውጪ ከቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ፊት ለፊት በሚገኘው አዳራሽ ሥር በሚገኘው ፉካም ቀብሩ ከ12 ሰዓት በኋላ ተፈጸመ፡፡ ስብሐትም አለፈ፤ ስብሐትም ሔደ፡፡
ቀብሩ ላይ የተገኘው ደራሲው ዘነበ ወላ ከ11 ዓመት በፊት በመጋቢት ወር ያሳተመውና ‹‹ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ማስታወሻ›› ብሎ የጠራው ታሪከ ስብሐት፣ በክፍል አንድ ‹‹ስብሐት ለአብ›› ንኡስ ክፍሉ የተከፈተው ‹‹ሞትን እንቅደመው›› በማለት ነው፡፡
ዘነበ እንዲህ ጻፈ፡፡
ከዕለታት አንድ ቀን [ስብሐት] ‹‹ዘነበ›› [ብሎ ጠራው]
‹‹አቤት ጋሼ?››
‹‹ሞትን እንቅደመው?››
‹‹እሺ! ግን እንዴት?››
‹‹ከማውቀው የማስታውሰውን ሁሉ ልንገርህ!››
‹‹ማለፊያ!››
‹‹የሚጣፈውንም፣ የማይጣፈውንም ነው የምነግርህ››
‹‹እየያዝኩ ነው››
ዘነበና ስብሐት ወጋቸውን ቀጠሉ፤ ወጉም ተጠራቅሞ ባለ345 ገጽ መጽሐፍ ወጣው፡፡ በመጋቢት 1993 ብርሃን ያየው የ‹‹ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ማስታወሻ›› መጽሐፍ በቅብብሎሽ እዚህ ደረሰ፤ ወደፊትም ለትውልደ ትውልድ ይቀጥላል፡፡ ይፈስሳል፡፡ የተጻፈለት ደራሲው ስብሐት ግን የመጋቢት 13ኛ ወር በሆነችው በየካቲት ተከተተ፡፡ ባሕረሐሳቡ እንደሚለው ዐውዱ ተፈጸመ፡፡
ከመንበረ ጸባዖት ዐውደ ምሕረት ቆሞ ጸሎተ ፍትሐቱን ይከታተል የነበረው የማስታወሻው ደራሲ ዘነበ፣ ከ1993ቱ 65 ዓመተ ስብሐት (ዓ.ስ.) እስከ 2004 ዓ.ም. 76 ዓ.ስ. እስከ ግብአተ ሕንፃ ድረስ የነበረውን የስብሐት ታሪክ አንቀጽ ከነጓዙ ይጽፈው ይሆን? ከሚያውቀው፣ ከሚያስታውሰው፣ ከሚጣፈውም፣ ከማይጣፈውም አወጣጥቶ ያመጣልን፣ ያዘንብልን ይሆን?

የኪራዩ ቁማር

 
29 Jan, 2016

በአሁኑ ወቅት የቤት ኪራይ ከምንም ነገር በላይ የብዙዎች ዋነኛ የኑሮ አጀንዳ ነው፡፡ ከዝቅተኛ ደረጃ እስከ ላይ ድረስ የኪራይ ዋጋ ለተከራዮች ጉዳያቸው ብቻም ሳይሆን ራስ ምታታቸውም ጭምር ነው ቢባል ስህተት አይሆንም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ በየጊዜው የዋጋ መጨመር፣ ቤት ልቀቁ መባል፣ የአከራዮች ቅድመ ሁኔታና የደላሎች ሚና ነው፡፡
በተቃራኒው በማከራየት ሒደት ዋነኛ ተዋናይ ለሆኑት ደላሎች ደግሞ የቤት ኪራይ ራስ ምታታቸው ሳይሆን ሎተሪያቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ላለው ምክንያታዊ ያልሆነ የቤት ኪራይ የገበያ ዋጋ ብዙዎች ተጠያቂ የሚያደርጉት ደላሎችን ነው፡፡ አንዳንዶች ደግሞ ለቤት ኪራይ ብቻ ሳይሆን ደላሎች የሌሉበት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ በአጠቃላይ ለኑሮ መወደድ የደላሎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ይደመድማሉ፡፡ ‹‹ደላሎች የሌሉበት እንቅስቃሴ ጠፍቷል፡፡ ምግብ መግዛትና ታክሲ መሳፈርም እንኳ በደላላ እየሆነ ነው፡፡ እነሱ የሚጨምሩት ምንም ዓይነት እሴት ግን የለም፤›› በማለት አስተያየት የሰጡም አሉ፡፡
እንደተባለው በብዙ መልኩ በተለያዩ እንቅስቃሴዎች የደላሎች ተፅዕኖ ከፍተኛ መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡ እዚህ ላይ የኮንዶሚኒየም ቤት ኪራይ የደላሎች ወሳኝ የሥራ መድረክ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ ከመደለል ባሻገር የባለቤቶች እንደራሴ ሆነው የሚንቀሳቀሱ ደላሎችም ጥቂት አይደሉም፡፡ እነዚህ ደላሎች ገበያውን ዓይተው የጓደኞቻቸውን ዕርምጃ እንደሚከተሉ፣ ዋጋ በመጨመር መሪ እንደሚሆኑም ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
ለስድስት ዓመታት ገደማ ገርጂ ሰንሻይን አካባቢ ከሚገኘው ኮንዶሚኒየም ሳይት ተከራይቶ ኖሯል፡፡ በመጀመርያ ሲከራይ የገባው ስቱዲዮ ሲሆን፣ አሁን የሚኖረው ባለ አንድ መኝታ ኮንዶሚኒየም ውስጥ ነው፡፡ እሱ እንደሚለው ደላሎች ለባለቤቶች ዋጋ ያወጣሉ፣ በየጊዜውም እየደወሉ የገበያው ዋጋ መጨመሩን በመንገር ጭማሪ እንዲያደርጉ ያሳስባሉ፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን ከወራት በፊት ያስገቡትን ተከራይ የተሻለ ዋጋ የሚከፍል በማምጣት ያስወጣሉ፡፡ ይህን ሐሳቡን ሙሉ በሙሉ ብዙዎች ይጋሩታል፡፡
እሱን ያከራየው ደላላ እንዳከራየው በጥቂት ወራት ውስጥ ማረሚያ ቤት በመግባቱ እዚያው ሳይት ላይ የሚኖሩ ሌሎች የሚያውቃቸው ሰዎች ያስገቧቸው ደላሎች ያደረሱባቸው ዓይነት ጫና አልደረሰበትም፡፡ በርግጥ ይህ የሆነው ያከራየው ደላላ ለሁለት ዓመታት ሳይቱ ላይ ባለመኖሩ ብቻም ሳይሆን አከራዩ መልካም ሰው በመሆኗ ጭምር እንደሆነ ያምናል፡፡ ከረዥም ጊዜ በኋላ እዚያው አካባቢ ሲገናኙ ሰላም ብሎ አልፎ  ተከራዩ እዚያው ያስገባው ቤት መሆኑን አረጋግጦ ወዲያው ለባለቤቱ ደውሎ በመንገር ለማስወጣት የሚንቀሳቀስ ደላላ ሁሉ አለ፤›› በማለት ደላሎች ዋጋ ለመጨመር የማያደርጉት ሙከራ እንደሌለ ይገልጻል፡፡
ምንም እንኳን የመጀመርያውን ዕርምጃ የሚወስዱት ደላሎች ቢሆኑም የኮንዶሚኒየም ባለቤቱም ኪራይ፣ የቤቱን ዕዳ የሚከፍልበት ኑሮውን የሚኖርበትም በመሆኑ መጨመሩን እንደማይጠላውና ከደላሎቹ ጋር እንደሚተባበር ይናገራል፡፡ አንዳንድ አከራዮች በተለያየ ምክንያት የሦስት ወይም የስድስት ወር ቅድሚያ የሚጠይቁ ቢሆንም እንደዚህ የወራት ቅድሚያ መጠየቅ ከተወሰነ ጊዜ ወዲህ የተለመደ አሠራር እየሆነ የመጣው በደላሎች ምክንያት እንደሆነም ያስረዳል፡፡ እሱ እንደሚለው ሌሎች እንደሚገልጹትም በዚህ የደላሎች ኮሚሽን የሚሰላው በተፈጸመው የወራት ክፍያ መሠረት ነው፡፡

ብዙ ባይሆኑም ጥቂት ኮንዶሚኒየም ሳይቶች ላይ የሚገኙ ኮሚቴዎችና ማኅበራት የቤት ኪራይ ሥርዓትን ፈር ለማስያዝ፣ የሚባለውን ያልተገባ የደላሎች ሚና ለመቀነስ ተንቀሳቅሰዋል፡፡ የኮሜት (ሳሪስ አቦ) ኮንዶሚኒየም ኅብረት ሥራ ማኅበር  በዚህ ረገድ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት አስተዳደር ኃላፊ አቶ እዮብ ኑሬ እንደገለጸው በሳይቱ 16 ብሎኮች ሲኖሩ 80 በመቶ የሚሆኑት ቤቶች የተከራዩ ሲሆኑ፣ ቀሪው 20 በመቶ የሚሆነው ባለቤቶች የሚኖሩባቸው ናቸው፡፡
በሳይቱ ደላሎች የማከራየት ሚና የላቸውም፡፡ ቤት ፈላጊ መከራየት የሚችለው ከመኅበሩ ጽሕፈት ቤት ተመዝግቦ ነው፡፡ ቤት ፈላጊዎች የሚፈልጉን ቤት ዓይነት ይናገራሉ፡፡ መታወቂያ የመሰሉ ማስረጃዎችን አሳይተው ስልካቸውን እንዲተው ይደረጋል፡፡ ተራቸው ሲደርስ ይደወልላቸዋል፡፡ መተዳደሪያ ደንብ ተሰጥቷቸው ሲስማሙ ውል ፈጽመው እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ እዚያው ተከራይ የሆነ ሌላ ቤት ሲፈልግም እንዲመዘገብ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡ ከአሠራር ውጭ የቤት ባለቤቶች በፈለጉት ጊዜ የፈለጉትን ሰው የማስገባት መብት የላቸውም፡፡ እህትንና ወንድምን ማስገባት የመሰሉ ፍላጎች ሲኖሩ ኬዙ በልዩ ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህም ቢሆን ግን ማኅበሩ የመታወቂያ ካርድን በመመልከትና በሌላም መንገድ እውነት እህት ወይም ወንድም መሆናቸውን እንደሚያረጋግጥ አቶ እዮብ ይናገራል፡፡
ይህ አሠራር የተዘረጋው ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ በማኅበሩ ጽሕፈት ቤት የቤት ባለቤቶች ፋይል በተደራጀ መልኩ ተቀምጦ ይገኛል፡፡ ማኅበሩ ለሥራ ማስኬጃና ለጽሕፈት ቤቱ ማስተዳደሪያ ይሆን ዘንድ በኪራይ ከአከራይም ከተከራይም አምስት በመቶ አምስት በመቶ ኮሚሽን የሚወስድ መሆኑን የሚናገረው አቶ እዮብ ደላሎች ግን ከሁለቱም ወገን አሥር በመቶ አሥር በመቶ ይወስዱ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ‹‹የምንቀበለው እያንዳንዱ ክፍያ በሕጋዊ ደረሰኝ የሚፈጸም ነው፡፡ በየወሩም ኦዲት ይደረጋል፡፡ ማኅበሩ በቦርድ የሚተዳደር ሲሆን፣ የቦርድ አባላት በየሁለት ዓመት የሚመረጡት ማንነታቸው ታውቆ ነው፤›› የሚለው አቶ እዮብ ማኅበሩ ሥራውን በግልጽ እንደሚሠራ ያስረዳል፡፡ ለምሳሌ ተራ ለደረሳቸው ሰዎች ስልክ የተደወለበት ሰዓት ይመዘገባል፡፡ ይህ አልተደወለልኝም ወይም ሌላ ነገር በማለት የሚፈጠርን ችግር ይፈታል፡፡
ከነዋሪዎች ለመረዳት እንደሞከርነው ከሌሎች ጋር ሲነፃፀር የቤት ኪራይ ዋጋ ጥሩ ሊባል የሚችል ነው፡፡ በግቢው ዋጋ ስቱዲዮ 22 ካሬ 2,000 ብር፣ ባለ አንድ መኝታ 36 ካሬ 3,000 ብርና ባለሁለት 48 ካሬ 4,000 ብር ይከራያል፡፡ የማኅበሩ ጽሕፈት ቤት አከራዮች የግቢውን ዋጋ መሠረት እንዲያደርጉ አስተያየት ከመስጠት ውጭ ዋጋ የማውጣት መብት ሙሉ በሙሉ የባለቤቱ ነው፡፡ ቢሆንም ግን የማኅበሩ አሠራር ባንድም ይሁን በሌላ መንገድ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ እንዳይኖርና ወጥ ባልሆነ አሠራር ተከራዮች ላይ ሊፈጠር የሚችል ጫናን አስቀርቷል፡፡ አሠራሩ በብዙ መልኩ ለአከራይም ለተከራይም ጠቅሟል፡፡ በእርግጥ በተለያየ አጋጣሚ ባለቤቶች መብታችን ተነካ የሚል ቅሬታ ማንሳታቸው አልቀረም፡፡
በጀሞ፣ ጎፋና ጎተራ ኮንዶሚኒየም ሳይቶች ባለቤት በሆኑ አከራዮች እንደተገለጸልን በየጊዜው በደላሎች እየተደወለ ዋጋ እየጨመረ መሆኑ ይነገራቸዋል፡፡ ተከራይ እንደሚያመጡና በተሻለ ዋጋ እንደሚያከራዩ ቃል የሚገቡ ደላሎችም አሉ፡፡
በጀሞ ሳይት ባለ አንድ መኝታ ቤት የምታከራየው ባለቤት በቅርቡ ያጋጠማትን ነግራናለች፡፡ እዚያው ሳይት የምትኖረው ሌላ የራሷ ቤት ውስጥ ነው፡፡ አጠገቧ ያለን የሌላ ሰው ስቱዲዮም ኃላፊነት ወስዳ የምታከራየው እሷ ነች፡፡ ቀደም ሲል የነበሩት ተከራዮች ወጡና ደላላ አዲስ ተከራይ አመጣ፡፡ አዲሱ ተከራይ ለስቱዲዮ እንዲከፍል የተደረገው 2,500 ብር ነበር፡፡ እሷ እዚያ ሳይት ላይ የሚገኘውን ባለ አንድ መኝታ የምታከራየው በ2,100 ስለነበር በመገረም ደላላውን እንዴት ነው ነገሩ? ስትል ጠየቀችው፡፡ የደላላው መልስ ባለ አንድ የሚከራየው እንደዚያ እንዳልሆነ ስለዚህም 3,200 ብር የሚከፍል ተከራይ እንደሚያመጣ ነገራት፡፡ በቀጥታ ለተከራዮቿ የተነገራትን በመግለጽ ዋጋ እንደምትጨምር አሳወቀቻቸው፡፡ ኪራዩን ከ2,100 ወደ 2,800 ብር ከፍ አደረገችው፡፡ ይህን አጋጣሚ በመጥቀስ የቱን ያህልም የተከራይን ሁኔታ ላገናዝብ ቢባል ደላሎች የሚያቀርቡት ዋጋ የአከራዩን ልብ እንደሚያማልል ትናገራለች፡፡
በጎፋ ኮንዶሚኒየም ደላላ የሆነው አቶ ደሳለኝ ዘውዴ ደግሞ ምንም እንኳ የተወሰኑ ደላሎች ዋጋ በማስጨመር ተከራዮች እንዲወጡ፣ አከራዮችም በየጊዜው እንዲጨምሩ የሚያደርጉ ቢሆንም የቤት ኪራይ እንዲጨመር ማድረግ በዋነኝነት የአከራዮች ፍላጎት ነው በማለት ይከራከራል፡፡ እሱ እንደሚለው በሳይቱ ደላሎች ተከራይ ያመጣሉ የኮንዶሚኒየም ማኅበሩ ውል ያዋውላል፡፡ ተከራይ ለተዋዋለበት ለማኅበሩ፤ የደላላውን ደግሞ ለደላላው ኮሚሽን ይከፍላል፡፡ ተከራዩ ለሁሉቱም መክፈሉ ተገቢ ነው ብሎ እንደማያምን ግን ይህ ነው የሚባል አሠራር እስከሌለ እነሱ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ ይናገራል፡፡
‹‹የቤት ኪራይን በተለይም ኮንዶሚኒየም እንዲጨምር ያደረገው የደላላ ሥራ ብቻ አይደለም፤ አንዳንድ ጊዜ ባለቤቶች የሚያስቀምጡት ዋጋ ለእኛም ለመናገር እንኳ ይከብደናል፤›› ይላል አቶ ደሳለኝ፡፡ የቤት ኪራይ ዋጋ እንዲጨምር የባለቤቶች ሚናም ከፍተኛ መሆንን በሚመለከት ጉለሌ ክፍለ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የመድኃኒዓለም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ አንተነህም የደላላውን አቶ ደሳለኝን ሐሳብ ይጋራሉ፡፡
የተጋነነ ዋጋ ማስቀመጥ፣ በመጀመርያ የሦስት ወይም የስድስት ወር ከተቀበሉ በኋላ ቅድመ ሁኔታ እያስቀመጡ በየጊዜ ተከራይን ማስወጣት በቤት ባለቤቶች በኩል ምን ያህል ዋጋ የመጨመር ፍላጎት እንዳለ እንደሚያሳይ አቶ ደሳለኝ ያምናል፡፡ በደላላዎች በኩል ደላሎች የሚፈልጉት የዕለት ገንዘብ ማግኘት ስለሆነ ዋጋ አከራይ የሚችለው ሆኖ የድርሻውን አግኝተው ቢወጡ እንደሚመርጡ ይናገራል፡፡ ‹‹ሰው እያለቀሰ የማገኘው ገንዘብ ለእኔም ሰላም አይሰጠኝም፡፡ መንግሥት በካሬ ሜትር ተምኖ የሆነ ዓይነት ግልጽ አሠራር ቢቀመጥ ለተከራዩም ለእኛም ጥሩ ይሆናል፤›› በማለት ወጥ የሆነ አሠራር እንዲኖር እንደሚፈልግ፤ ደላሎችም ዕውቅና አግኝተው መስመር ውስጥ ይገባሉ የሚል እምነት እንዳለው ይናገራል፡፡  
በመድኃኒዓለም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ሳይትም ደላሎች በማከራየትም ይሁን በሽያጭ በሳይቱ መንቀሳቀስ አይችሉም፡፡ ይህ የሆነው 2006 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ባለቤቶች ተሰብስበው ውሳኔ ላይ በመድረሳቸው ነው፡፡ ኪራይ በደላላ ሳይሆን በምዝገባ ነው፡፡ ኪራይ ሲሆን ማኅበሩ ከአንድ ወር ኪራይ አሥር በመቶ ኮሚሽን ይወስዳል፡፡ ከሽያጭ ደግሞ አንድ በመቶ ይወስዳል፡፡ በደላላ ግን ኪራይ ሲሆን አሥር በመቶ ከሁለቱም ወገን ከሽያጭ ደግሞ ሁለት በመቶ ኮሚሽን ይከፈላል፡፡
የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታደሰ እንደሚያስታውሱት በፊት በሳይቱ ነዋሪ ሆነው የሚደልሉም ብዙ ስለነበሩ ችግሮች ነበሩ፡፡ ውል ላይ የባለቤቶችን ሳይሆን የራሳቸውን ስልክ ቁጥር በማስቀመጥ የባለቤቶች እንደራሴ ሆነው እንዳሻቸው ተከራይ የሚያውሰጡና የሚያስገቡ፣ ዋጋ የሚጨምሩ ደላሎች ነበሩ፡፡ በደላሎች ከመስመር የወጣ ዕርምጃ ወደ ክስ የተሄደባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ፡፡ በእነዚህና በሌሎች ሁኔታዎች ነው በግቢው ቤት የሚከራየው በደላላ ሳይሆን በምዝገባ እንዲሆን ውሳኔ ላይ የተደረሰው፡፡
ባለቤቶች በየጊዜው ዋጋ መጨመራቸውን ለማኅበሩ እንደሚያሳውቁ፤ በሌላ በኩል ተከራዮችም ዋጋ ተጨመረብን ቅሬታ እንደሚያቀርቡ የሚናገሩት አቶ ታደሰ ለባለቤቶች የግቢውን ዋጋ መሠረት በማድረግ ዋጋቸውን ምክንያታዊ እንዲያደርጉ ጥረት ሲያደርጉ ባለቤቶች ምን አገባችሁ እንደሚሏቸው ይገልጻሉ፡፡ ስለዚህ እሳቸውም እንደ ደላላው አቶ ደሳለኝ ወጥ የሆነ አሠራር ቢመጣ መልካም መሆኑንና ለማስፈጸምም ዝግጁ መሆናቸውን ይገልጻሉ፡፡
ካነጋገርናቸው ብዙዎቹ ዋጋ በካሬ ሜትር የሚተመንበት ወጥ አሠራር ቢኖር እንደሚመርጡ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የቤት ባለቤቶች መብትን በመጋፋት ወይም ደላሎችን ከሥራ ውጪ በማድረግ ሳይሆን አግባብ ያልሆነ አሠራርን የሚያስቀርና የዋጋ ጭማሪን ምክንያታዊ እንዲሆን የሚያደርግ ወጥ አሠራር መዘርጋትን ነው የብዙዎች ችግር ለሆነው የቤት ኪራይ ዋጋ ውድነት መፍትሔ የሚሉት፡፡

Thursday, February 18, 2016

‹‹ነፃ መሆኔን ያወቅኩት ሰዎች ነፃ ነሽ ሲሉኝ ነው››
በብዙዎች የምትታወቀው ኢቢኤስ ቲቪ ላይ በምታቀርበውና ጆርዳና ኪችን በሚሰኘው የምግብ ዝግጅት ፕሮግራሟ ነው፡፡ የአርባ ስድስት ዓመቷ ወ/ሮ ጆርዳና ከበዶም ኢትዮጵያ ውስጥ ትወለድ እንጂ ያደገችው ውጭ አገር ነው፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነች፡፡ የምግብ ዝግጅት ፕሮግራሟን መሠረት በማድረግ ከምሕረት አስቻለው ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች፡፡
ሪፖርተር፡- ያደግሽው የት ነው?
ጆርዳና፡- ያደግኩትም የተማርኩትም ጣሊያን አገር ውስጥ ነው፡፡ እዚያ ላድግ የቻልኩት ልጆች ሳለን ቤተሰቦቼ ለኑሮ ወደዚያ በመሄዳቸውና እዚያው በመቅረታቸው ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን ካጠናቀቅኩ በኋላ ግን እኔ ወደ አገሬ ተመልሻለሁ፡፡ ከመጣሁ እንኳ አሥራ ስምንት ዓመት ሆኖኛል፡፡
ሪፖርተር፡- በቲቪ የምግብ ዝግጅት ፕሮግራምሽ ላይ ከምታሳያቸው ነፃ መሆንን ከሚያንፀባርቁ የተለያዩ ሁኔታዎች በመነሣት ብዙዎች ውጭ አገር መኖርሽን ይገምታሉ?
ጆርዳና፡- አዎ ነፃ ሰው ነኝ፤ ነገር ግን በመጀመርያ ደረጃ ነፃ መሆን ተፈጥሮዬ ነው፡፡ አስተዳደጌ ቤተሰቦቼም በርግጥ ለዚህ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ነፃ መሆኔ ለኔ ኖርማል የተፈጥሮዬ ነገር ነው፡፡ ነፃ መሆኔን ያወቅኩት ሰዎች ነፃ ነሽ ሲሉኝ ነው፡፡ ነፃ መሆን ለኔ ሌሎችን ሳያስቀይሙ የሚፈልጉትን ነገር ማድረግ መቻል ነው፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ግን እብደት ይሆናል፡፡ ስለዚህ ነፃ መሆኔ የተፈጥሮዬና የአስተዳደጌ እንጂ ውጭ የመኖሬ ውጤት ብቻ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲ ሳለሽ ያጠናሽው ምንድን ነው?
ጆርዳና፡- የተማርኩት እንግሊዝ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ያጠናሁት ማርኬቲንግ ነው፡፡ የምግብ ነክ  ሥራ ግን በፍላጎትና ከቤተሰብ ጋር የተያያዘ እንጂ በትምህርት ያገኘሁት አይደለም፡፡ እናቴ ምግብ የማዘጋጀት ከፍተኛ ፍላጎትም ችሎታም ያላት አብሳይ ናት፡፡ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሳለሁም  ፍላጎቱ ስለነበረኝ የተለያዩ ሬስቶራንቶች እሠራ ነበር፡፡ ምግብ የማዘጋጀት ችሎታዬ ከፍቅርና ከልምድ የመጣ እንጂ ትምህርት ቤት ሄጄ አይደለም፡፡ የተለያዩ ሬስቶራንቶች ውስጥ ከተለያዩ ሼፎች ጋር ሠርቻለሁ፡፡ በትምህርት ላገኝ የምችለውን ነገር በእነዚህ አጋጣሚዎች ማግኘት ችያለሁ፡፡ ሬስቶራንቶች ውስጥ መሥራትም ብቻ ሳይሆን ከቤተሰቦቼ ጋር ከፍተን ሠርቻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ከረዥም ዓመታት የጣሊያን ቆይታ በኋላ እንዴት ወደ ኢትዮጵያ ተመለሽ?
ጆርዳና፡- የመጣሁት በአጋጣሚ ለስድስት ወር እረፍት ነበር፡፡ ልጅ እያለሁ የማውቀውን የዛሬውን ባለቤቴን በዚህ ወቅት አገኘሁት፡፡ እዚህ የፈረንሳይ ሬስቶራንት ከፈተ፤ ሁለታችንም አብረን መሥራት ጀመርን፡፡ የሀበሻ ምግብ ከዚያም ኬተሪንጉን እያልን እያልን በኢትዮጵያ ፍቅር እዚህ ቀረሁ፡፡ ይህ ውሳኔ በወቅቱ ለእኔ ከባድ አልነበረም፤ ምክንያቱም ብቻዬን ነኝ ውሳኔውም የእኔ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- የቴሌቪዥን የምግብ ዝግጅት ፕሮግራም መሥራት ያሰብሽው መቼ ነበር?
ጆርዳና፡- የዛሬ አሥር ዓመት ሐሳቡ ነበረኝ፡፡ ምን መቅረብ አለበት? ሕዝቡ ምን ይፈልጋል? እንዴትስ ይቀበለዋል? የሚለውን ሳስብበት ነው የቆየሁት፡፡ ከምግብ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ የሚያስፈልጋቸው በሽታዎች አሉ፡፡ አመጋገብና ጤናንም ከግንዛቤ ከትቻለሁ፡፡  በመጨረሻ ነፃ ሆኜ መሥራት የምችልበትን ሁኔታ ኢቢኤስ ስላመቻቸልኝ፣ በምፈልገው መንገድ እንድሠራ ሰፊ እድል ስለሰጡኝ አሳቤን አሁን ተግባራዊ ላደርገው ችያለሁ፡፡ እንደዚሁ ጊዜና ሁኔታዎችን የሚጠብቁ በርካታ በወረቀት አስፍሬ ያስቀመጥኳቸው የሥራ ሐሳቦች አሉኝ፡፡
ሪፖርተር፡- አንድን ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ አሥር ዓመት መጠበቅ ረዥም አይደለም?
ጆርዳና፡- ረዥም ነው፡፡ ግን እኔ ቅድመ ሁኔታዎች እየተቀመጡልኝ መሥራት የምወድ ሰው ስላልሆንኩኝ በምፈልገው መልኩ ለመሥራት ጊዜ መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ ሁኔታዎች ከተቀመጡ ሁሌም እኔ ይሄን አድርጊ ያንን እየተባልኩ አሻንጉሊት እሆናለሁ፡፡ ይህን ደግሞ አልፈቅድም፡፡ ፕሮፖዛሌን ኢቢኤሶች አዩት፣ ወደዱት በምፈልገው መልኩ በነፃነት እንድሠራ ሁኔታዎችን አመቻቹልኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ቀደም ባሉት ጊዚያት ምግብ ማብሰል የሴቶች ኃላፊነት ፍላጎቱም የሴቶች ተደርጎ ይታይ ነበር፡፡ አሁን ግን ወንዶችም ምግብ የማብሰል ፍላጎት እያሳዩ የመጡበት ሁኔታ አለ እዚህ ላይ ምን አስተያየት አለሽ?
ጆርዳና፡- መሠረታዊው ነገር የማብሰል ፍላጎት መኖሩ ነው፡፡ ምግብ የማብሰል ፍላጎት ያለው ሰው ያበስላል፡፡ ሴት ወንድ የሚለውን ነገር ያመጣው ባህል ነው፡፡ ሆዱን የሚወድ፣ ጥሩ ምግብ የሚወድና የሚያስደስተው ሴትም ወንድም ያበስላል፡፡ እውነት ነው ለውጦች እየታዩ ነው፡፡ ወንዶች ማብሰል ጀምረዋል፡፡ ለምሳሌ ሴቷ ደህና ገቢ የሚያስገኝ ሥራ ካላትና የወንዱ እስከዚህም ከሆነ ወንዱ ቁጭ ብሎ እያበሰለ ልጆች የሚያሳድግበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ይህ ደስ የሚያሰኝ ለውጥ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያየ መልኩ አስተያየታቸውን የሚገልጹልሽ እነማን ናቸው?
ጆርዳና፡- የመጀመርያዎቹ ልጆች ናቸው፡፡ ትልልቅ ሴቶችም አስተያየት ይሰጡኛል፤ ወንዶች ግን ይበዛሉ፡፡ ከሁሉም የሚያስደስተኝ ግን የልጆች አስተያየት ነበር፡፡ ምክንያቱም ልጆች ነፃ መንፈስ ያላቸው በመሆናቸው ነው፡፡ አድገው ከዓመታት በኋላ ጆርዳና እንዲህ ትል ነበር፣ እንደዚያ ማለታቸውን ሳስበው እደሰታለሁ፡፡ ምንም እንኳ የእኔን የምግብ ፕሮግራም ተመልክተው አስተያየት ሰጡ ማለት ወንዶች ምግብ ማብሰል ጀመሩ ማለት ባይሆንም ፍላጎት እያደረባቸው ለውጥም እየታየ የመሆኑ ምልክት ነው፡፡ ስለዚህም ምግብ ለማብሰል ወደ ማዕድ ቤት መግባት ይሞክራሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የምግብ ዝግጅት የሙሉ ጊዜ ሥራሽ ነው?
ጆርዳና፡- አዎ የሙሉ ጊዜ ሥራዬ ነው፡፡ አዳዲስ ሬስቶራንቶች ሲከፈቱ አማክራለሁ፡፡ ሠርጎችና ሌሎች ዝግጅቶች ላይ ምግብ አዘጋጃለሁ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያልኩ የምሠራቸው ሥራዎች በአጠቃላይ በምግብ ዝግጅት ዙርያ ያሉ ናቸው፡፡ የኢቢኤሱ የምግብ ዝግጅት ፕሮግራም ግን ከሁሉም በላይ ጊዜዬን ይወስዳል፡፡ በመሀል ክፍተት ሳገኝ ግን ሌሎቹን ሥራዎች እሠራለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ስለ አመጋገባችን አስተያየት አለሽ?
ጆርዳና፡- ይህ ምግብ ምን ይዘት አለው? ምን የለውም ብሎ የመጠየቅ ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ ዛሬንና የዛሬ አሥራ ስምንት ዓመት የነበረውን ሁኔታ ስናነፃፅር አሁን ብዙ ለውጥ አለ፡፡ ስለዚህ ከምግብ ጋር በተያያዘ ሰው የተለያየ ነገርን ማወቅ የሚፈልግበት ጊዜ መጥቷል፡፡ ዓመት በዓል ካልሆነ በቀር ዛሬ ሰው በደንብ የተቁላላ ወጥ መብላት አይፈልግም፡፡ ቀለል ያለ ብዙ ያልተጠበሰ ምግብ ምርጫው እየሆነ መጥቷል፡፡ ለምሳሌ በምግብ ዝግጅት ላይ የሚያተኩር ጋዜጣ የመጀመር ሐሳብ አለኝ፡፡ ሐሳቤ በወረቀት ላይ ሰፍሮ ተቀምጧል፡፡ እንደ ማኅበረሰብ ይህ ዓይነቱን ጋዜጣ የምንፈልግበት ደረጃ ላይ ስንደርስ ሐሳቤ ተግባራዊ ይሆናል፡፡ ሕዝቡ ስለአመጋገብ ጆሮውን መክፈቱን መረጃ መፈለጉን በሚመረቱ ምርቶች፣ እላያቸው ላይ በሚለጠፉ መረጃዎች ማወቅ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- የምግብ አዘገጃጀታችንን በሚመለከት የምትይው ይኖራል?
ጆርዳና፡- ዘይት ይበዛል፡፡ አትክልቱ ምንነታቸው እስኪለወጥ ድረስ ይጠበሳሉ፡፡ ይህ በሒደት የሚቀየር ነው፡፡ የምግቦችን የንጥረ ነገር ይዘት መመልከት ደግሞ ሌላ ትኩረት ልናደርግበት የሚገባ ነገር ነው፡፡ ካርቦሀይድሬት ፕሮቲንና አትክልት ያስፈልገናል፡፡ አቅም በፈቀደ በተቻለ እነዚህን ማመጣጠንና ጤናችንን መጠበቅ ይኖርብናል፡፡ እንደ ጎመን፣ ሰላጣ ያሉ ነገሮች ብዙ ውድ አይደሉም፡፡ እኔ በነሱ ብኖር ደስተኛ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- በቅርብ ልትሠሪ የምታስቢው ነገር ካለ?
ጆርዳና፡- ያለኝን የቲቪ የምግብ ዝግጅት ፕሮግራም ማጠናከር ነው፡፡ ሠርቼ አልጠግብም፣ አይደክመኝም፡፡ አሁን በሳምንት ሁለት ጊዜ ነው የምሠራው፣ የሚታየው ግን አራት ጊዜ ነው፡፡ ጥያቄውም ስፖንሰሩም ካለ በቀን የመሥራት አቅም አለኝ፡፡

Sunday, February 14, 2016

የቀለሙ ቀንድ - ኪዳነ ወልድ

29 June 2014 ተጻፈ በ 


(አ) ፊት በር
ካፍሪቃ ወንዞች ወርቅና አልማዝ - እንደሚያስገኘው እንደ ዓባይ ወንዝ
ተርፎን እንዲፈስ ትምርቱ ንግድ - በዚህ ሰዋስው ጥርጊያ መንገድ
ይልቅ ኑ እንውጣ ወደ ገበያ - ገበያችንም ኢትዮጵያ፡፡

መደብሮቿ የተዘጉቱ - ባራቱ ማዕዘን እንዲከፈቱ
ልጆቿን በሙቀት እያሳደገ - መንገዶቿንም እያስጠረገ
እግዜር ያቆማት ከማኽል ቦታ - በውጭ አገር ሰው እንዳትፈታ፡፡
ያፍሪቃ ደንደስ ሻኛና ጫንቃ - ጦቢያው እንጂ ናት ምሥራቅ አፍሪቃ
የሰማይ ምደር የምድር ሰማይ - የተከበበች በነጭ አባይ 
ዐይኗም ሲመስል በገነት ዐይን - ነጩ አባይ መደብ ጥቁሩ ብሌን
ባስተያየትም ሲመረመሩ - ማየት አይችልም ነጭ አለ ጥቁሩ፡፡ 
ነጩ ሲፈተሽ ውስጠ ጥቁር - ጥቁሩም ሲፈተሽ ውስጥ ነጭ ዘር፤
ሕብረ ሰማይ ነው ጥቁሩ አባይማ - በቂጥኛም አፍ የማይታማ፡፡ 
ነጭና ጥቁር የዓለም ዐይን - ኹሉም ተገልጦ የሚከድን፤
መክደኛውም ሞት ወዝ ከንባይ ነው፤ ያዳም ሌባ ጣት የሰፋችው፡፡
ይህ በሰምና ወርቅ መንገድ የቀረበው የቅኔ ገበታ ከሰማንያ ዓመታት በፊት ታላቁ ኢትዮጵያ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከደረሱት ሰፊ የቅኔ አዝመራ የተቀነጨበ ነው፡፡ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በሚባለው የግእዝ ቋንቋ ሰዋስውና ግስ፣ የግእዝ አማርኛ መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ውስጥ የተገኘው ሰማዊና ወርቃዊው ቅኔያቸው የግእዝን ትምህርት በአባይ ወንዝ የመሰሉበት ኢትዮጵያም የአፍሪቃ አውራ፣ የአፍሪቃ ቀንድ መሆኗን ያጠየቁበት ነው፡፡ በግእዝ ኢትዮጵያ የዕውቀት መደብሮች ውስጥ የሚገኙትን መክሊቶች በግእዝ ሰዋስው መሰላልነት መሠረትነት እናውጣቸው፣ እንጠቀምባቸው የሚል ሴማ አለው፡፡ 
በኢትዮጵያ የቋንቋዎች ሕዋ፣ በሥነ ጽሑፍ ገበታ፣ በአንድምታ ትርጓሜ እልፍኝ ውስጥ ላቅ ያለ ስፍራ የሚሰጣቸው ሊቁ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በአፀደ ሥጋ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን፣ ዓለምንም ከተለዩ ሰኔ 24 ቀን 2006 ዓ.ም. ልክ 70 ዓመት፣ 70 ክረምት፣ 70 መፀው፣ 70 በጋ፣ 70 ፀደይ ይሞላቸዋል፡፡ 
በቀለም - አበባ ይዘከሩና እኚህን ታላቅ የጥበብ ሰው እንዘክራለን፡፡
(ቡ) አለቃ ኪዳነ ወልድ ማን ናቸው?
ከሰባ ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ሰኔ 24 ቀን ስላረፉት አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ዜና ዕረፍት፣ በወቅቱ በሳምንታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ደቀ መዝሙራቸው አለቃ ደስታ ተክለ ወልድ ከታሪካቸው ጋራ ሐምሌ 1 ቀን 1936 ዓ.ም. ጽፈውት ተገኝቷል፡፡ በጋዜጣውና በመጽሐፈ ሰዋስው ላይ የሰፈረውን ዜና ሕይወታቸውን አዛምደን ለማቅረብ ወደድን፡፡  
አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ በ1862 ዓ.ም. የተወለዱት በይፋት ወረዳ [ሰሜን ሸዋ] ነው፡፡ በጎንደር ባለቃ ዘዮሐንስ ዘንድ የዳዊት ትርጓሜ ተምረው ከጨረሱ በኋላ በ1891 ዓ.ም. በዘመነ ሉቃስ ከጎንደር ተነሥተው በአክሱም በኩል ምፅዋ ኼደዋል፡፡ ከምፅዋም በመስከረም 1892 ዓ.ም. በግብፅ አስቄጥስ ገዳም በመግባት ለስምንት ወራት ቆይተዋል፡፡ በሚያዝያ ወርም ለ20 ዓመታት ወደኖሩባት ኢየሩሳሌም ተጉዘዋል፡፡ በኢየሩሳሌም ቆይታቸው ካገኟቸው መምህር ክፍለ ጊዮርጊስ የብሉይንና የሐዲስን፣ የሊቃውንትንና የመጻሕፍተ መነኮሳትን፣ የፍትሕ ነገሥትን ትርጓሜ ለዐሥር ዓመት ተማሩ፡፡ አቡሻህርና መርሐ ዕውርም [ባሕረ ሐሳብ] ዐወቁ፡፡ መምህራቸው ካረፉ በኋላ በኢየሩሳሌም የዓመታት ቆይታቸው የግእዝ ቋንቋ ቤተኛ የሆኑትን ዕብራይስጥ፣ (የእሥራኤል ቋንቋ)፣ ሱርስት (የሶርያ ቋንቋ) እና ዐረብኛ አጠኑ፡፡ የብሉያትንም ትርጓሜ ከዕብራይስጥ አጥብቀው አጥልቀው መረመሩ፣ በዕብራይስጥና በጽርእ (ግሪክ) በግእዝ መጻሕፍት መካከል እንዴት ያለ ልዩነት እንዳለ ተረዱ፡፡ ከዚህም በዃላ ጃንሆይ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ዐልጋ ወራሽ ልዑል ራስ ተፈሪ መኰንን ይባሉ በነበረ ጊዜ የግእዝን መጻሕፍት እያስተረጎሙ ሲያስጥፉ ሕዝቅኤልን መጥተው እንዲተረጉሙላቸው ስላስጠሯቸው በ1912 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መጡ፡፡ የሕዝቅኤልንም ንባብ በዕብራይስጥ ዐርመው አጥርተው አብርተው፣ ትርጓሜውንም ከዕብራይስጥና ከሮማይስጥ አውጥተው፣ ዐልፎ ዐልፎም ማስረጃ ሥዕል አግብተው በ1916 ዓ.ም. አሳትመው ለግርማዊነታቸው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አስረከቡ፡፡ በ1926 ዓመተ ምሕረትም መዝገበ ፊደል አውጥተው ከየት መጣውን ከነማስረጃው ጥፈው ሌላም ታናሽ ፊደል ከዕብራይስጥና ካረብኛ ጋራ አቆራኝተው አሳትመዋል፡፡ 
በድሬዳዋም ኅሊና ያልደረሰበትን የግእዝ ቋንቋ እየመረመሩ ሲጥፉ 22 ዓመት ተቀመጡ፡፡ ጠላት ኢትዮጵያን በወረረ ጊዜ ጣሊያን ለቅጣት ነው እንጂ፣ ኢትዮጵያን አይገዛም፣ ጃንሆይም ሲኼዱ እንዳየናቸው ተመልሰው እናያቸዋለን እያሉ ሳይፈሩ ሳያፍሩ በግልፅ ስለሰበኩ በ1929 ዓ.ም. ኹለት ወር አሰራቸው፡፡ ዳግመኛም በ1933 ዓ.ም. አንድ ወር ካሰራቸው በዃላ እንግሊዞች ፈቷቸው፡፡ የታሰሩበት በጨለማ ውስጥ ነበርና በፊተኛው እስራት ግራ ዐይናቸው በኹለተኛው ቀኝ ዐይናቸው ታወረ፡፡ 
ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ዐይንኽን አሳክምኻለኹ ስላሏቸው በ1936 ዓ.ም. ኅዳር 15 ቀን አዲስ አበባ መጥተው ተቀምጠው ሳሉ የስኳር በሽታ ነበረባቸውና 15 ቀን ከታመሙ በኋላ በራስ ደስታ ሆስፒታል በተወለዱ በ73 ዓመታቸው ሰኔ 24 ቀን ከማታው በ12 ሰዓት ተኩል ዐርፈው ሬሳቸው በክቡር አባ ሐና ርዳታ ካዲስበባ በካሚዮን ተጉዞ በ11 ሰዓት ተኩል ደብረ ሊባኖስ ተቀበሩ፡፡ ሐሳባቸው ኹሉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በማንኛውም ነገር ራሷን እንድትችል ነበር፡፡ 
(ጊ) ሥራዎቻቸው
አራት ዐይናው ኪዳነ ወልድ ከቋንቋና ከመዝገበ ቃላት፣ ከሃይማኖትም ጋራ የተያያዙ ታላላቅ መጻሕፍት አዘጋጅተዋል፡፡ በሕይወት እያሉ የታተሙላቸው መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሦስት ናቸው፡፡ እነርሱም የመዠመርያው፣ ‹‹መጽሐፈ ሕዝቅኤል ከትርጓሜው ጋራ ንባቡ በግእዝ ትርጓሜው ባማርኛ ከኪዳነ ወልድ ክፍሌ ተጽፎ ታተመ፡፡ ፲፱፻፲፮ (1916)›› ኹለተኛው፣ ‹‹አበገዳ ፊደልና ፊደላዋሪያ የልጆች አፍ መፍቻ››፣ ሦስተኛው ‹‹መዝገበ ፊደላት ሴማውያት››ኹለቱም በድሬዳዋ ከተማ በቅዱስ አልዓዛር ማተሚያ ቤት በ1926 ዓ.ም. የታተሙት ናቸው፡፡
የአለቃ ኪዳነ ወልድን ስም በግዘፍ ከሚያስነሡት ሥራዎቻቸው ዋነኛው ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› ነው፡፡ ይህ በአንዳንዶች አገላለጽ ኢንሳይክሎፔዲያ መሰል መጽሐፍ የኅትመት ብርሃን ያየው ሊቁ ባረፉ በ12 ዓመት፣ በ1948 ዓ.ም. በደቀ መዝሙራቸው (ተማሪያቸው) አለቃ ደስታ ተክለወልድ ዘብሔረ ወግዳ አማካይነት ነው፡፡
መጽሐፈ ሰዋስውን በቅድሚያ ማዘጋጀት የጀመሩት መምህራቸው ክፍለ ጊዮርጊስ ናቸው፡፡ ያንኮበሩ ሊቅ መምህር ክፍሌ ወልደ አባ ተክሌ አለቃ ደስታ እንደጻፉት፣ ትምርት ከጥፈት ያስተባበሩ፣ በትምህርታቸውም የተደነቁና የታወቁ የውጭ አገር ባህል ቋንቋና ፊደል ያጠኑ ነበር፡፡ በምፅዋ ደሴት ግሱን የጨረሱት ለማረምና ለማሳተም ዕረፍትና ጊዜ አላገኙም፡፡ ተከረን ወደ ሮማ፣ ከሮማ ወደ የሩሳሌም ሲሉ ብዙ ጊዜ ዐለፈ፡፡ ኋላም በጊዜ ሞት 10 ዓመት ሙሉ ከርሳቸው ጋራ በኢየሩሳሌም ለነበረው ለሀገራቸው ልጅ ለተማሪያቸው (ኪዳነ ወልድ) እንዲህ ብለውታል፤ ‹‹ልጄ ሆይ ይህነን ግስ ማሳተም ብትፈልግ እንደገና ጥቂት ዕብራይስጥ ተምረኽ ማፍረስና ማደስ አለብኽ፤ በመዠመሪያው አበገደን ጥፈኽ የፊደሉን ተራ በዚያው አስኪደው፡፡ አንባቦችም እንዳይቸገሩ ከፊደል ቀጥለኽ ዐጭር ሰዋስው አግባበት፣ የጎደለውና የጠበበው ኹሉ መልቶ ሰፍቶ ሊጣፍ ፈቃዴ ነው፤ ከሌላው ንግድ ይልቅ ይህን አንድ መክሊት ለማብዛትና ለማበርከት ትጋ ዘር ኹን፣ ዘር ያድርግኽ ካላጣው ዕድሜ አይንፈግኽ ለሀገርኽ ያብቃኽ ብለው ተሰናበቱት፡፡››
አለቃ ኪዳነ ወልድ ‹‹ዐደራ ጥብቅ ሰማይ ሩቅ›› ነውና ከመምህራቸው የተቀበሉትን ዐደራ ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንዲሉ 22 ዓመት ሙሉ ሠርተው አጠናቀቁት፡፡ ሒደቱን አለቃ ደስታ ባጭሩ እንዲህ ይገልጹታል፡፡ ‹‹ሕዝቅኤልንም ንባቡን ከምሉ ትርጓሜው ጋራ [1916 ዓ.ም.] አሳትመው ካስረከቡ በዃላ በቅድስት አገር [ኢየሩሳሌም] የወጠኑትን ይህን ብርሃናዊ መጽሐፍ  [መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ] እንደገና በድሬዳዋ ማዘጋጀት ዠመሩ፡፡ በሥራ ውለው ማታ ነፋስ በመቀበል ጊዜ አንድ ሐሳብ ቢያገኙ በማስታወሻ ለመጻፍ ከውጭ ወደ ቤት ይመለሳሉ፡፡ በምሳ ወይም በራት ጊዜ አንድ ትርጓሜ ቢታሰባቸው ምግቡን ትተው ብድግ ይላሉ፡፡ ሌሊትም ተኝተው ሳሉ አንድ ምስጢር ቢገጥማቸው ከመኝታቸው ተነሥተው መብራት አብርተው ይጽፋሉ፡፡
‹‹ያን ጊዜም ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ ያዘዙላቸውን ቀለብና ድርጎ እያደራጁ በዕለት መፍቅድ ይረዷቸው የነበሩ የክቡር ብላታ አሸኔ ኪዳነ ማርያም ባለቤት ክብርት ወይዘሮ በላይነሽ ጎበና [የራስ ጎበና ዳጨው ልጅ] ናቸው፡፡ 
የአለቃ ኪዳነ ወልድ ሌላኛው መጽሐፍ ‹‹ግእዝ መሠረተ ትምህርት›› ነው፡፡ ለዚህ መጽሐፍ መዘጋጀት መንሥኤ የሆነው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላለቃ ኪዳነ ወልድ መፍቅድኽን  [ቀለብህን] እየሰጠኹ በምትፈልገው ነገር ኹሉ እረዳኻለሁ (እጦርኸለኹ)፣ ስላገራችንም ጥቅም ብዙ ዘመን የደከሙበትን የግእዝ ሰዋስውና ግስ አሳትምልኻለኹ ብለው ተስፋ ስለሰጧቸው በ1936 ዓ.ም. ኅዳር 26 ቀን ወዳዲሳበባ መምጣታቸው ነበር፡፡ ቀበና በተቀመጡ ጊዜ ሦስት ሰዎች የግእዝ ቋንቋ መማር እንፈቅዳለን ቢሏቸው የስምና የአንቀጽ ርባታ በቃል በጽፈት ማታ ማታ ማስተማር ዠመሩ፡፡ ይህንንም ከ60 ዓመት በፊት አለቃ ደስታ ሰብስበውና ጽፈው በ1946 ዓ.ም. በአዲስ አበባ የኅትመት ብርሃን እንዲያይ አደረጉት፡፡ 
ሌላው የሊቁ ሥራ በ1980ዎቹ በሀገረ ጀርመን በቁም ጽሕፈት ለኅትመት የበቃው የነገረ መለኮት (ቲኦሎጂ) መጽሐፍ የኾነው ‹‹ሃይማኖት አበው ዘቀደምት ወዘደኃርት›› ነውና፡፡ ሊቄ ኪዳነ ወልድ፣ መጸሐፉን በግእዝና ባማርኛ ንባብና በኹለት ዐይነት ግጥም አድርገው አዘጋጅተውና ጽፈው ያጠናቀቁት በ1934 ዓ.ም. ነበር፡፡ 
አለቃ እስካሁን ያልታተሙ መጻሕፍት እንዳሏቸውም ይነገራል፡፡ አንዱ ‹‹የዕብራይስጥ ግስ በግእዝ ፊደል ተጽፎ በግእዝ ቋንቋ የተተረጐመው›› ነው፡፡ ማን ይኾን ባለተራው ባለዐደራ የሚያሳትመው፣ ከኅትመት ብርሃንስ ጋራ የሚያገናኘው? 
(ዳ) ቅንጫቢ
ሊቁ ከጻፏቸው መጻሕፍት ለማሳያ፣ አንድም ለአንክሮ ለተዝክሮ ይኾን ዘንድ ባጭሩ እንጽፋለን፡፡ 
1.የመጽሐፈ ሕዝቅኤል ትርጓሜ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ መጻሕፍት አንዱ ‹‹ትንቢተ ሕዝቅኤል›› ነው፡፡ በ1916 ዓ.ም. ንባቡ በግእዝ ትርጓሜ በአማርኛ አድርገው አዘጋጅተውታል፡፡ አተረጓጐሙ አንድምታ ነው፡፡ ከነጠላ ትርጉም ያልፋል፡፡ ምዕራፍ 27 ቁጥር 17 እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹ይሁዳና እስራኤል ምድር ነጋዴዎችሽ ነበሩ፤ የሚኒትን ስንዴ ጣፋጭም እንጐቻ ማር ዘይትም በለስንም ስለአንቺ ሸቀጥ ይነግዱ ነበር፡፡››
ሊቁ ግእዝና አማርኛውን ከአንድምታው ጋር ጂኦግራፊያዊ ተዘምዶውንም ከኢትዮጵያ ጋር አያይዘው እንዲህ አቀረቡት፡፡ 
‹‹ይሁዳ ወምድረ እስራኤል እሙንቱ ሠየጥኪ፡፡ ይሁዳ ሠማሪያ አሥሩ ነገድ፣ ሁለቱ ነገድ የሚገዙና የሚሸጡ ነጋዶችሽ ነበሩ፡፡
‹‹ወረሰዩ ማዕረብተኪ በሥርናየ ሚኒት ወበሰምዕ ወመዓር ወቅብዕ ወርጢን፡፡ 
ሚኒት ከሸዋ እንደ ቡልጋ፣ ከትግሬ እንደ እንደርታ ያለች የስንዴ አገር ናት፡፡ ርስትነቷ የደቂቀ አሞን ነበረ፡፡ ገለዓዳዊ ዮፍታሔ በጦርነት ወስዷታል፡፡ ንግድሽን ከሚኒት በሚወጣ ስንዴ በሰምና በማር በዘይትና በበለሳን አደረጉት፡፡ በለሳን ጥሩ ሽቱ ነው፤ በኢያሪሆ ይበቅላል፤ ኢያሪሆ ማለት ሠናየ መዓዛ ዘመዓዛሁ ሠናይ ማለት ነው፡፡ ቦ ርጢን በቁሙ መድኃኒት ማለት ነው፡፡ በምድረ እስራኤል የማይበቅል እንጨት የለምና፡፡
2.‹‹አበገደ - ፊደልና ፊደላዋሪያ የልጆች አፍ መፍቻ››
በአበገደ ፊደል ገበታ የተዘጋጀው መማሪያ መጽሐፍ፣ ከፊደል ገበታው በተጨማሪ ንባብና ሥርዓተ ነጥብ፣ ከግእዝ ጋራ የሚዛመዱት የሱርስትና የዕብራይስጥ የዐረብም ፊደል ከነስሙና ከነቁጥሩ ይዟል፡፡ ፊደላቱ ዲቃሎቻቸውም ሳይቀሩ፣ ድምፀ ልሳኑ የሚነገርበትን ባምስት ጾታ በጉሮሮና በትናጋ፣ በምላስና በከንፈር በጥርስ የሚነገሩትን ያሳያል፡፡ 
‹‹የፊደላዋሪያ መቅድም›› በሚለው ክፍል ተማሮች ከፊደል ጋራ በግጥም ቃል የተመላለሱበት ተውኔታዊ ምልልስም ይገኝበታል፡፡
ከ80 ዓመት በፊት በታተመችው መጽሐፍ ብዙ ቋንቋዎችን መማር ልዩ ልዩ ጥበባትን መቅሰም እንደሚያስፈልግ ታሳስባለች፡፡ ጵጵስናን ከግብፅ መፈለግ የለብንም፤ የራሳችንን ሊቃውንት ጳጳሳት አድርገን መሾም አለብንም ትላለች፡፡ የኪዳነ ወልድ ድምፅ፡፡
(ተማሪ)   ‹‹ሃይማኖት ያስለውጥ እየመሰለን
            እጅግ አንወደውም ቋንቋን መማሩን
            ከሃይማኖት ኹሉ የኛ ሃይማኖት
            ትበልጣለችና በውነተኛነት፡፡
(ፊደል) ‹‹የልጅ ነገር ወትሮ ሁለት ቅንጣት ፍሬ
       አንዱ ፍጹም ብስል አንዱ ፍጹም ጥሬ፤
        አባቴ ታናሽ ነው ሃይማኖቴ ክፉ
        የሚል የለምና በዚህ አትስነፉ፡፡ 
       ቋንቋና እጅ ሥራ ካልጨመራችኹ
       ንግድና መኪና ካላቆማችኹ
       ባንድ ክፍል ትምርት በድጓ በቅኔ
       አይገኙምና ብዕልና ሥልጣኔ
      ይልቅስ ተማሩ ኹሉን በያይነቱ
     ቶሎ እንዲለቃችኹ ስንፍናው ንዴቱ፡፡
     … አንድ ዐረግ ቢስቡ ዱር ይሰበስቡ
     የተባለውን ቃል ስለ ቋንቋ ዐስቡ፡፡ 
    በዚህ ላይ መምሩ ያገር ልጅ ሲኾን
    መሰወር አይችሉም ጥበብና ኪን፤
    ያገር ልጅ የማር እጅ የሚሉት ተረት 
    ከመምር ከጳጳስ አለው መስማማት፡፡
   ንጉሥና ጳጳስ ግራና ቀኝ ዐይን 
  አንድ ዐይነት ሊኾኑ አይገባምን?
  ንጉሥ እያላችኹ ጳጳስ መበደር
  ይኸ ነው የዘጋው የትምርቱን በር፡፡
  መበደሩ ቀርቶ ክህነትና አቡን
  ሊቀ ጵጵስናው በጃችኹ ቢኾን፤
  ኢትዮጵያችሁ እንደ ፀሐይ ሙቃ
  ታንዣብቡ ነበር አፍሪቃ ላፍሪቃ፤
  ወደ እስያም ክፍል እንዳፄ ካሌብ
   ትሻገሩ ነበር በወንጌል መርከብ፡፡››
3.‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ መመዝገበ ቃላት ሐዲስ››
ባለታሪካዊው የ922 ገጹ የግእዝ - አማርኛ መጽሐፍ በ19ኛው ምእት ዓመት አጋማሽ ተዠምሮ በ20ኛው ምእት አጋማሽ የኅትመት ብርሃን ያየ መጽሐፍ ነው፡፡ በዝግጅትና በኅትመት ጉዞው ሦስት ትውልዶችን አሳልፏል፡፡ ከመዝገበ ቃላቱ የኹለት ቃላት አፈታት እነሆ፡፡
ወንጌል፤ (ላት፡፡ ጽርዕ (ግሪክ) ሄዋንጌሊዎን፡፡ ዐረብ ኢንጂል)፣ በቁሙ፤ ብሥራት፣ ምሥራች፤ ሐዲስ ዜና መልካም ወሬ፣ ደስ የሚያሰኝ ስብከት፤ አምላካዊ ሰማያዊ ነገር፤ ምሥጢረ ሥላሴ፣ ምሥጢረ ሥጋዌ፡፡
-፤መጽሐፍ የመጽሐፍ ስም፤ የሐዲስ ኪዳን መጽሐፍ አራት ክፍል ያለው፣ አራት ሰዎች የጣፉት፤ ፍችው ያው ብሥራት ነው፡፡
ወይ፤ (ዐረብ ዋእ፣ ወይ፡፡ ሱርስት (የሶርያ) ዋይ፡፡ ዕብራይስጥ ኦይ)፤ ንኡስ አገባብ፡፡ በቁሙ፤ ወዮ ወየው፤ ዋይ ውይ፤ አወይ የልቅሶ የሐዘን፣ የቁጣ፣ የንዴት፣ የብስጭት ቃል ነው፡፡ ወይ ሊተ፣ ወይ ልየ፣ ወይ ለከ እያለ እንደ አሌ በለ ይዘምታል፡፡ አሌንና ለይን ተመልክት የዚህ ጎሮች ናቸው፡፡
ወይ፤ (ዐማርኛ)፤ በቁሙ፤ (ዋዌ አው) የማማረጥ ቃል፤ አውን እይ፡፡ (ግጥም፤ ሐፄ ቴ፡ ባሏን የሰቀሉባት)፣ ወይ አልተቀደሰ የባረኩት ሰው፤ ንጉሥ መስቀልዎን ቢተዉት ምነው፡፡ ፪ኛም የምኞትና የፍላጎት የአንክሮ ቃል ይኾናል፤ (ግጥምና ሙሾ ስለጐንደር ጥፋት)፤ ቴዎድሮስ መጣ ዐይኑን አፍጦ፤ ወይ መሸሸጊያ ታናሽ ቁጥቋጦ፡፡ ተከተለኝ ብዬ ዙሬ ዙሬ ሳይ፤ ወይ ጥጋብ ወይ ኩራት ጐንደር ቀረ ወይ፡፡ ፫ኛም ያቤቱታ ቃል የጥሪ ተሰጦ ይኾናል፤ (ግጥም፣ የበለው እኅት ተማርካ በመተማ ሳለች)፤ ጐዣም አፋፉ ላይ የሚጣራው ማነው፤ ወንድሜ እንደኾነ ወይ በለው ወይ በለው፡፡ ምስጢሩ እንደላይኛው ነው፡፡ ፬ኛም  የጥያቄ ቃል ይኾናል፤ ኼደ ወይ፣ መጣ ወይ፡፡ 
‹‹መዐዛ ሰዋስው - የግጥም ስብከት›› በሚለው ክፍልም፣ ለአማርኛ ግእዝ ነው ዳኛ የሚል አስተሳሰብ የያዘ ለአማርኛ መሠረቱ ግእዝ ነው የሚል አቋም ያቀፈ ዐውደ ግጥም ይገኛል፡፡ ባለቅኔው ኪዳነ ወልድ እንዲህ ተቀኝተዋል፤ ሦስቱን አንጓ እነሆ፡፡ 
በዶሮ ሥጋ አምሳል ምሥጢሩ እንዲጥም 
ዐጭሬ ረዥሜ ይባላል ግጥም፤
ዐጭሬው ሰዋስው ረዥሜው ግስ
የሦስት ፊደል ሥጋ የርባ ቅምር ነፍስ
ለልጆች እንዲተርፍ ያዋቆች መብል
ያቡን ወጥ በሚሉት በቲማቲም ቃል
ሠርቶ ያቀረበው የግእዝ ወጥ ቤት
ላስነባቢው ምሳ ላንባቢው እራት፡፡ 
የሰዋስው ትምርት ሥጋውና ዐጥንቱ
ባጭሬው ተክቷል ረዥሜነቱ፡፡
ላንቀጹ ፍልሰታ ለርባታው ሑዳዴ
የተለቀመውን ጥሩ ፊደል ስንዴ
አስተውል ተመልከት ጸሐፊና አንባቢ 
ያማርኛ ገበዝ የግእዝ ዐቃቢ፡፡
የግእዝን ትምርት አባይን በጭልፋ 
ቀድቶ የሚጨርስ ማነው ባለተስፋ 
ቀድቶም ባይጨርሰው ከርሱ ለሚጠጣ 
ለሚሻገረውም እየተቀናጣ፡፡
ካዋቆች ራስ ቅል የተከፈለው 
ፋጋውና ሜዴው እንሆ ይኸው፡፡ 
ዐዞውም ስንፍና ተማሪ እንዳይነጥቅ
ዋነተኛው መምር ተግቶ ይጠብቅ፡፡ 
በቀለም ገበያም ጣፊው ብር ሲቀርጥ
ፊደሉ እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ፡፡
(ሄ) ሐውልታቸው - መጽሐፋቸው
በኢትዮጵያ ሕዋ እንደተወርዋሪ ኮከብ ብቅ ብለው ካለፉት እሙራንና ማዕምራን (ታዋቂዎችና አዋቂዎች) መካከል በ19ኛው በ20ኛው ምእት ዓመት ውስጥ የኖሩት አለቃ ኪዳነ ወልድ ከፍሌ አንዱ ናቸው፡፡ ዘንድሮ ከተወለዱ 142ኛ ዓመት፣ ካረፉ ከአፀደ ሥጋ ከተለዩ 70 ዓመት ሞልቷቸዋል፡፡
ሥራዎቻቸው በቤተክህትም ሆነ በቤተመንግሥት ይሁንታንና ይበልታን ያገኘ፣ እስከዘመናችን ድረስም በማጣቀሻነት በማስተማሪያነት፣ ዘርፈ ብዙ አገልግሎት እየሰጠ ለመሆኑ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ከመዠመርያ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ድርሳኖች ውስጥ ሳይጠቀሱ ያለፉበት ጊዜ የለም፡፡ ለየድርሳናቱ (ቴሲስ ዲዘርቴሽን) ምልዐት ከኪዳነ ወልድ የጽሑፍ ጎተራ ያልዘገነ ያልቀመሰ፣ ያላጠጣመ አይኖርም፡፡ 
የግእዝ ቋንቋን ከሌሎች ሴማዊ ቋንቋዎች ጋራ እያገናዘቡ በመመርመር የፊሎሉጂ ጥናት በማድረግ ረገድ በፋና ወጊነት በአገሬው ሊጠቀሱ ቢችልም፣ በዘመናችን የሳቸውን ፈለግ ተከትሎ ንፅፅራዊ ጥናት ስለመቀጠሉ የተሰማ የተጻፈ ነገር አለመኖሩን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተጀመረውና ግእዝና ዐረቢኛን ብቻ መሠረት ያደረገው የፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ወደ ሌሎቹም ተዛማጅ ቋንቋዎች ይሸጋገር ይሆን?
አምና የግእዝና የሱርስጥ (ሶርያ) ቋንቋዎች ጥናት ጉባኤ ያካሄደው የኢትዮጵያ ካቶሊክ ዩኒቨርሲቲና የቅዱስ ፍራንቸስኮስ የጥናትና የጽሞና ምርምር ማዕከል፣ እንዲሁም ዐውደ ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ጥረትን ከተግባር ጋር ያስቀጥሉት ይሆን? የሚታይ ይሆናል፡፡
አለቃ ኪዳነ ወልድ ይከተሉት በነበረው ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ምክንያት የሥራዎቻቸውን ያህል ተገቢውን ቦታ አለማግኘታቸው ይነገራል፡፡ የሚገባቸውን ያህል ክብርም አልተሰጣቸውም፡፡ የመቃብራቸው ምልክትም እንደጠፋ ነው የሚወሳው፡፡ 
የባሕር ማዶ ቀደምት ጠቢባንን ለመዘከር የሚተጉት አገራዊ ተቋማትና ማኅበራት ለኢትዮጵያ ዐቢይ ቁም ነገርን ትተውና በሥራ አሳይተው ያለፉትን የሚዘክሩት መቼ ይሆን? (በርግጥ ባለፈው ግንቦት 25 ቀን 2006 ዓ.ም. በአንድ የዐውደ ኢትዮጵያ ሀገራዊ የጥናት ጉባኤ 70ኛ ዓመታቸውን ያሰበ መሰናዶ ሳይዘነጋ)
አምና በኬንያ ናይሮቢ ስለአፍሪካ ቲኦሎጂ የመከረ አንድ ጉባኤ ተካሂዶ ነበር፡፡ በጉባኤውም ኢትዮጵያን ጨምሮ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የመጡ ምሁራን ተገኝተው ነበር፡፡ 
በጉባኤው የተሳተፉ ኢትዮጵያዊ ምሁር እንዳወጉን፣ በጉባኤውም በመጀመሪያዎቹ የክርስቲያን ዘመናት (ከአንደኛው ምእት ዓመት ተነሥቶ) በሰሜን አፍሪቃ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጋር በነበረው ክርስቲያናዊ ግንኙነት በርካታ መጻሕፍት በግሪክ፣ በላቲን በዐረቢኛ ተዘጋጅተዋል፡፡ የሃይማኖት መግለጫዎችም ተቀነባብረዋል ተቀምረዋል፡፡ በዘመኑም የነበረውን የአፍሪካ ቲኦሎጂ ለማወቅ ምሁራኑ በተለይ ግሪክና ላቲንን ማጥናት መመርመር አለብን ብለው ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ነበር ከምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር የመጡ ጋናዊ ምሁር ጥሩ ብላችኋል፣ ግሪክ ላቲንን ማጥናት ይገባል፡፡ የተረሱ ሁለት ቋንቋዎች አሉ፡፡ የአፍሪካን ቲኦሎጂ ለማወቅ አንድንችል የሚያደርጉ ግእዝና አማርኛን ቋንቋዎች ማጥናት አለብን በማለት አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸውና ከተተረጐመባቸው የመጀመሪያዎቹ ቋንቋዎች አንዱ ግእዝ ነበርና እውነትነት አላቸው፡፡
ከሰማንያ ዓመት በፊት ሊቁ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ስለሁለቱ ቋንቋዎች ግእዝና አማርኛ በቅኔያቸው እንዲህ ተንብየው ነበር፡፡
‹‹እናንተ እንጂ ናችኹ ያፍሪቃ ራስ ቅል
ባለዘውድ ቋንቋ ባለነጻ አክሊል
ግእዝ ዐማርኛም ኹለቱ ቋንቆች
ታላቅ ታናሽ አባይ ያፍሪቃ ወንዞች፤
ካፍሪቃ ዐልፈው ተርፈው በባሕር በየብስ
ገና ይሰፋሉ እንደ እግዜር መንፈስ
ስላማርኛና ስለግእዝ ክብር
ዋዜማ ተቁሟል በብዙ አህጉር፡፡››