22 July 2015 (15/11/07) ተጻፈ በሔኖክ ያሬድ (ረፖርተር)
ከዓዲግራት ከተማ ወደ ዛላምበሳ በሚወስደው አውራ ጎዳና በስተቀኝ በኩል ገባ ብሎ አንድ ጥንታዊ መንደር አለ፡፡
የተንጣለለ አካባቢ ነው፡፡ በርካቶች ኖረውበታል፡፡ አካባቢው ‹‹ገናሕቲ››፣ ‹‹በዓቲ›› በመባል ለዘመናት
ሲጠራበት
ኖሯል፡፡ በአካባቢው ተወልደው ያደጉት የ107 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋ አቶ ካሕሳይ ባህታ ‹‹ገናሕቲ›› ለሚባል
መጽሔት እንዳወጉት፣ ‹‹በዓቲ›› ዋሻ ማለት እንደሆነ ‹‹ገናሕቲ›› ደግሞ መንገድ ቀያሽ፣ መካሪና አቅጣጫ ቀያሽ
ማለት እንደሆነ ነግረውታል፡፡ በእነዚህ ሁለት መንደሮችና ጎልዓ ከሚባለው ቦታ የተወሰነ ቦታ በመውሰድ አንድ
ዩኒቨርሲቲ ተመሥርቶበታል፡፡ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በ2003 ዓ.ም. ካቋቋማቸው 10 ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ የሆነው
ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ወደ አራተኛ ዓመቱ እያመራ ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም. በ960 ተማሪዎች ሥራውን ጀምሮ
የመጀመርያዎቹን ምሩቃን አምና ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡ ዘንድሮም በታሪኩ ለሁለተኛ ጊዜ 1027
ተማሪዎችን ባለፈው ቅዳሜ ሐምሌ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ያስመረቃቸው ተማሪዎች በስሩ ካሉት አራት ኮሌጆችና 16
ክፍለ ትምህርቶች የተገኙ ናቸው፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተመሠረተበት በዓቲ (ዋሻ) አቶ ካሕሳይ እንደተናገሩት፣ ድሮ ልጆች
ሆነው ዝናብ ሲዘንብባቸው፣ እረኞችም ከነከብታቸው የሚጠለሉበት ቦታ ነበር፡፡ ዩኒቨርሲቲው ከተመሠረተ በኋላ
የኢትዮጵያ ልጆች ከአራቱም አቅጣጫዎች ተሰብስበው ተጠልለውበታል፡፡ ዕውቀትና ሥልጣኔ ይማሩበታል፡፡ ‹‹ስም ይመርሆ
ለግብር›› (ስም ሥራን ይመራል) ማለት ይኼ ነው በማለት ይገልጹታል፡፡ በትግራይ ክልል ምሥራቃዊ ዞን ውስጥ
የሚገኘው ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በቅድመ ምረቃና ድኅረ ምረቃ ፕሮግራሞች 11,000 መደበኛ በተከታታይና በክረምት
ፕሮግራሞች 3,000 ተማሪዎች በድምሩ 14,300 ተማሪዎች አሉት፡፡ ‹‹ጠንክሮ መሥራት መለያችን ነው›› የሚል መሪ
ቃል ያለው ዩኒቨርሲቲው ዓርማ ላይ በክልሉ ታዋቂ ሰብል የሆነው በለስ ፍሬ ይታይበታል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ካለው
የመማር ማስተማር ተግባር በተያያዥነት በምርምር ላይም የተሰማራ ሲሆን፣ በተለይ የበለስ ጥናት ተቋምንም
አደራጅቷል፡፡ የዩኒቨርሲቲውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የአካዴሚክ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል
ፕሬዚዳንቱን ዶ/ር ዓለም መብራህቱን ሔኖክ ያሬድ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ካቋቋማችኋቸው የትምህርት ክፍሎች በተጨማሪ የበለስ ተቋም እንዳላችሁ ይነገራል፡፡ ለምን ተቋቋመ?
ዶ/ር ዓለም፡- በለስ እኛ ባለንበት የምሥራቅ ትግራይ ዞን በአብዛኛው
ዓጋመ በሚባለው አካባቢ በጣም የሚታወቅ የፍራፍሬ ዓይነት ነው፡፡ በእንግሊዝኛ ካክተስ በአማርኛ ቁልቋል ይባላል፡፡
በሌላ አካባቢ ከሚታወቀው በላይ በጣም ጣፋጭ ፍሬ ሲሆን ሰዎች በብዙ መልኩ ይጠቀሙበታል፡፡ ከሦስት እስከ አራት
ወራት የኅብረተሰቡን ምግብ ፍላጎት የሚሸፍንና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ሲሆን፣ በበጋ ወራት ለከብቶችም ጭምር ምግብነት
ያለው በተለይ ውኃ የመያዝ ከፍተኛ አቅም ያለው ስለሆነ በድርቅ ጊዜም እንኳ ከብቶች እርሱን በልተው ሳይቸገሩ
መቆየት የሚያስችል ትልቅ ባለውለታ ፍሬ ነው፡፡ በለስ በዓጋመ፣ በክልተ ኣውላዕሎ፣ በደቡባዊ ትግራይ ጨምሮ ከፍተኛ
ትርጉም ያለው ነው፡፡ ስለዚህ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ በበለስ ዋና ምንጭ በሚባለው የኢሮብ አካባቢ እንደመገኘቱ መጠን
በዚህ ባለውለታ ተክል ላይ ምርምር መሥራት ይገባል፡፡ አሁን ከሚሰጠው ጠቀሜታ በበለጠ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ
የኅብረተሰቡን ችግር በሚፈታ መልኩ ለማብቃት እንዲቻል የበለስ ተቋም አቋቁመናል፡፡
በለስ በዘመናዊ መልክ ከተያዘ ተጠቃሚነቱን በእጅጉ ማስረዘም ይቻላል፡፡ ሁለተኛ አገራችን እየተከተለችው ካለው
ወደ ማኑፋክቸሪንግ (ኢንዱስትራላይዜሽን) ከመሄድ አኳያ በተለይ በአግሮ ኢንዱስትሪ አካባቢ በለስ በርካታ ጥቅሞች
ሊሰጥ እንደሚችል ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በሜክሲኮ፣ በቺሊ፣ በጣሊያን በለስ የታወቀ ቢሆንም ደረጃው እኛ ካለን በለስ
በእጅጉ ያነሰ ግን በውድ ዋጋ የሚሸጥበት ሁኔታ አለ፡፡ ወደዚያም መግባት እንፈልጋለን፡፡ ለምግብነት እየሰጠ ካለው
በተጨማሪ ለወይንም በጭማቂ መልክም እንዲሁም በኢንዱስትሪ በኩል ለመድኃኒት፣ ለሳሙና፣ ለሻምፖ ለተለያዩ በርካታ
ነገሮች ለማዋል እንፈልጋለን፡፡ አሁን ፍሬው ብቻ ነው የሚበላው፡፡ ነገር ግን ገሉም ጭምር ሊበላ እንደሚገባ
የሚያሳዩ ጥናቶች አሉ፡፡ የሚበላበትም አካባቢም አለ፡፡ ስለዚህ ይህን ሀብትና ትልቅ ባለውለታ ፍሬ በእጅጉ ትኩረት
ተሰጥቶበት ለኅብረተሰቡ ጠቀሜታ በተገቢው መልክ እንዲያመጣ ተቋሙን አቋቁመን እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የታየ ነገር አለ?
ዶ/ር ዓለም፡- ከተቋቋመበት ከአንድ ዓመት ወዲህ ከተለያዩ ተቋማት
ጋር ግንኙነት መሥርተናል፡፡ ‹‹ሄልቤታስ›› ከሚባል አንድ ግብረ ሠናይ ድርጅት፣ ዩኒዶ ከሚባል ኦስትሪያ በሚገኝ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አንድ አካል ጋር የጋራ ስምምነት አለን፡፡ በአገር ውስጥ ከጥቃቅንና አነስተኛ
ማኅበራት፣ ከዓዲግራት ከተማ አስተዳደር ለአግሮ ኢንዱስትሪው የሚውል ሕንፃ አዘጋጅቶ ለሚደረገው ሽግግር በጋራ
እየሠራን ነው፡፡ ተቋሙ ከዚያ በላይ የበለስ በርካታ ዝርያዎች የተለያየ ጣዕምና ቀለም ያላቸው አሉና ለቀጣይ ሰፊ
ተቋም ሆኖ በርካታ ሥራ እየሠራ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ዩኒቨርሲቲው ዓርማ ላይ የሚታየው በለስ ነው?
ዶ/ር ዓለም፡- የዩኒቨርሲቲው ዓርማ በለስ ፍሬው ነው፡፡ እንደ ሉል
(ግሎብ) ክብ ነገር ስለሆነ እርሱ ራሱ በለስ ነው፡፡ እዚህ አካባቢ ከእሱ የሚበልጥ በውለታም በጣፋጭነትም ከጥቅም
አኳያ የተለየ ነገር ማግኘት ይከብዳል፡፡
ሪፖርተር፡- በቋንቋና በባህል ላይ ያተኮራችሁበት ነገር አለ?
ዶ/ር ዓለም፡- አገራችን ኢትዮጵያ የበርካታ ባህል፣ ቋንቋ፣ ሥልጣኔ
መነሻ ናት፡፡ እነዚህ ባህሎችና ትውፊቶች ቋንቋን መሠረት አድርገው የሚገለጹ ናቸው፡፡ የትግራይ አካባቢም
የሃይማኖቶች ሁሉ መጀመሪያ፣ የሥልጣኔዎችም ከሓና ከአክሱም ጀምሮ ይታወቃል፡፡ በዋናነት ደግሞ መነበይቲ [በዓዲግራት
ዛላምበሳ መስመር የሚገኝ] የንግሥት ማክዳ (ሳባ) የቅድመ የሓ የቅድመ አክሱም ቤተ መንግሥት እንደነበረ የካናዳ
ፕሮፌሰሮች ከኢትዮጵያውያን ምሁራን ጋር ሆነው እየሠሩት ያለው ጥናት ያመለክታል፡፡ በመነበይቲ የተገኘው የንግሥት
ማክዳ ቤተ መንግሥት የኢትዮጵያን ታሪክ በአንድ ዕርምጃ ወደፊት የሚወስድ ነው፡፡ ስለዚህ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ
በአርኪዮሎጂ በኩል እየሠራ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ቋንቋ የአንድ ሕዝብ የማንነት መገለጫ በመሆኑ በግእዝና
በትግርኛ በሌሎች ቋንቋዎች በቀደምት ኢትዮጵያውያን የተሠሩ በርካታ የጽሑፍ ሀብቶች አሉ፡፡ ትኩረት ተሰጥቶት
በዘመናዊ መልኩ ማጥናት ለአገር ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ያሉትን ሊቃውንት በግእዝና በትግርኛ ስላለው
ሀብት በዩኒቨርሲቲያችን እንዲመክሩ ጥናትም እንዲያቀርቡ አድርገናል፡፡
ሪፖርተር፡- በክፍለ ትምህርት ደረጃ በቋንቋ ላይ ምን እየሠራችሁ ነው?
ዶ/ር ዓለም፡- በአካባቢያችን ዋና መገለጫ ቋንቋ ትግርኛ ነው፡፡ ብዙ
ሥራዎችም አሉት፡፡ ዘንድሮ የትግርኛ ትምህርት ክፍልን አቋቁመናል፡፡ ሲምፖዝየሙን ያዘጋጀው አዲሱ የትምህርት ክፍል
ነው፡፡ ለቋንቋው ትኩረት ሰጥተን ባህሉንም ጭምር የምናጠናበት ይሆናል፡፡ ልጆቻችን ቁሳዊና መንፈሳዊ ባህላቸውን
እንዲያውቁ ከከተሜነት መስፋፋት አንፃር የአካባቢው መገለጫዎች የሆኑት ቁሶች እንዳይረሱ ለማድረግም ዓይነተኛ ተግባር
ይሆናል፡፡ ትምህርት ክፍሉ በአሁኑ ጊዜ 40 የሚጠጉ የመጀመሪያ ዓመት የትግርኛ ተማሪዎች አሉን፡፡ እነርሱን
እየኮተኮትን የበለጠ ሥራ ለመሥራት አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ምሥራቅ ትግራይ በተፈጥሮአዊ፣ በባህላዊና በሃይማኖታዊ ቅርሶች ይታወቃል፡፡ የውጭ አገር ተመራማሪዎችንም ቀልብ ይዞ በጥናት ላይ ተሰማርተውበታል፡፡ እናንተስ እምን ድረስ እየሄዳችሁ ነው?
ዶ/ር ዓለም፡- በዚህ በኩል እንደ አገር ብዙ ሥራ እየሠራን ነው
ብለን አናምንም፡፡ አገራችን በተለይ አሁን ካለው የሰላምና የልማት ገጽታ ሲታይ ከዘርፉ በእጅጉ ተጠቃሚ መሆን
ትችላለች፡፡ እኔ እንደግለሰብም የተወሰነ ሥራ ከሠራን አውሮፓውያን ሌላ መዳረሻ ይኖራቸዋል ብዬ አላምንም፡፡
የተወሰኑ ሥራዎች ከሠራን በትግራይ ያሉት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት እንደ ጉንዳጉንዶ፣ ደብረ ዳሞ፣ አክሱም ጽዮን፣
ነጋሽ፣ ገርዓልታ ትልቅ የቱሪስት መስህብ መሆን የሚችሉ ናቸው፡፡ ዳሉልም ከአካባቢያችን በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኝ
ነው፡፡ በድሮ ጊዜ የዓጋመ አውራጃ አንድ ወረዳ ነበር፡፡ አገራችንን በትልቁ ሊያስተዋውቁ የሚችሉ ሥራዎች አሉን፡፡
መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎችን በከፍተኛ በጀት እያቋቋመ ያለው በየኅብረተሰቡ ያሉት ነገሮች እንዲታዩ እንዲጠኑ ለማድረግ
ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲዎች ተግባር ምርምር ማካሄድ ለኅብረተሰቡ አገልግሎት መስጠት ስለሆነ መንግሥትን ወክለን ይህንኑ
ኃላፊነት ወስደን ሥራዎችን እየሠራን ነው፡፡ በተለይ የአርኪዮሎጂ ትምህርት ክፍል ከፍተናል፡፡ አዳዲስ በርካታ
ነገሮች እያገኘን ነው፡፡ ከሚመለከታቸው የውጭ አካላትም ጋር ግንኙነቶች ፈጥረን ምርምሮች እየተደረጉ ነው፡፡ በሌላ
በኩል የመስቀል ዓመታዊ ክብረ በዓል አለን፡፡ በመጪው መስከረም ከምንጊዜውም በተሻለ ዓለም አቀፍ መልክ ይዞ
የተለያዩ ተመራማሪዎች ጥናት የሚያቀርቡበት መድረክ በማዘጋጀት ላይ ነን፡፡ በዋናነት በምሥራቅ ትግራይ ባሉት
አርኪዮሎጂ ግኝቶች መሠረት አድርጎ ሌሎችን በሚጨምር መልኩ ለማካሄድ ጥረት እያደረግን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የልህቀት ጉዳይ እንዴት ነው የምታዩት?
ዶ/ር ዓለም፡- የልህቀት ጉዳይ እንደመናገር ቀላል ጉዳይ አይደለም፡፡
የትምህርት ተቋሞቻችን ቢያንስ በአካባቢያቸው ባለው የተሻለ ሀብት ሌሎች ከሚሠሩት በበለጠ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ያሉት ዩኒቨርሲቲዎች የተለያየ የልህቀት ማዕከል ቢኖራቸው ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ የትምህርት ክፍሎቻችን የልህቀት ማዕከል እንዲሆኑ ፍላጎት አለን፡፡ የመንግሥትን
ፖሊሲ መሠረት አድርገን የ70/30 ጉዳይ የአርኪዮሎጂ የቱሪዝም፣ የቋንቋዎች ሥራ እንደተጠበቁ ሆነው እየሠራን
እንገኛለን፡፡ ሠላሳውም የሠላሳ ድርሻ ይሠራል፡፡ በምሕንድስና በጤናው አካባቢ የበለጠ የልህቀት ማዕከል ለመሆን
እየሠራን ነው፡፡ በምሕንድስናው በአካባቢያችን በርካታ ሀብቶች አሉ፡፡ አንዱ የተለየ የድንጋይ ዓይነት በስፋት መኖሩ
ከአገራችን አልፎ ለአውሮፓ የምንተርፍበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከተጠቀምን በርካታ ሀብት
የሚገኝበት ዕድል ይኖራል፡፡ በዓዲግራት የመድኃኒት ፋብሪካ አለ፤ እኛም የኬሚካል ኢንጂነሪንግ አለን፡፡ በፋርማሲ
በኩልም ከጣሊያን ሳሌርኑ ዩኒቨርሲቲ ጋር ግንኙነት ፈጥረናል፡፡ እያሰፋን የምንሄድበት ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት
በሚያስቀምጠው አቅጣጫ ጥሩ ሥራ ሠርተን የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ የኅብረተሰብን ችግር የሚፈቱ የምርምር
ሥራዎች እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሁለት ዓይነት መሪ ቃል መጠቀማችሁ ለምንድነው?
ዶ/ር ዓለም፡- ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሁለት ዓይነት መሪ ቃል አለው፡፡
በየዓመቱ ገላጭ የሆኑ ቃላትን እንጠቀማለን፡፡ ከአራት ዓመት በፊት ስንጀምር ‹‹ነባር ዩኒቨርሲቲዎች ከደረሱበት
ጀምረን ወደፊት እንቀጥላለን›› ነበር፡፡ የሁልጊዜ መለያችን መሪ ቃል ግን ‹‹ጠንክሮ መሥራት መለያችን ነው››
ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ይኸ አካባቢ በታታሪነት፣ ሥራን በመፍጠር፣ ወደ ቢዝነስ ዓለም በመግባት ይታወቃል፡፡
በኢትዮጵያ ደረጃ በሌሎች አካባቢዎች እንዳሉት የሚጠቀስ ነው፡፡ ስለዚህ ዩኒቨርሲቲውም የሕዝቡ አንድ አካል ስለሆነ
‹‹ጠንክሮ መሥራት መለያችን ነው›› የሚለውን መሪ ቃል ይዘን በአጭር ጊዜ ውስጥ አራት ዓመት ሳንሞላ ወደ
11,000 የሚጠጋ መደበኛ ተማሪ መቀበል ችለናል፡፡ በአገር ደረጃም እውቅና ያገኘንበትና ቁጥር ብቻ ሳይሆን
በጥራትም እየሠራን ነው፡፡
No comments:
Post a Comment