Friday, July 3, 2015

‹‹የዝናብ ኮቴ ተሰማ››




‹‹የዝናብ ኮቴ ተሰማ››
(ደምፀ እገሪሁ ለዝናም)
በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ መሠረት ዛሬ ሰኔ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. የክረምት ወቅት ገብቷል፡፡ ትናንት ሰኔ 25 ቀን የሸኘነው የፀደይ (በልግ) ወቅት ነበር፡፡ ወቅቱ ዝናብ የዝናብ ወራት ነው፡፡ በፀደይና በመፀው መካከል ያለ ክፍለ ዓመት ሲሆን እስከ መስከረም 25 ድረስ ይቈያል፡፡
‹‹ሰማዩን በደመናት ይሸፍናል፤ ለምድርም ዝናብን (ክረምትን) ያዘጋጃል፤ሣር በተራሮች ላይ ያበቅላል፤ ለምለሙን ለሰው ልጆች ጥቅም፡፡››
‹‹ዘይገለብቦ ለሰማይ በደመና፤ወያስተዴሉ ክረምተ ለምድር፤ ዘያበቍል ሣዕረ ውስተ አድባር፡፡›› (መዝሙር 146፡8)፡፡
በኢዮብ እንደተጻፈውም (37፡5-6)፣ ‹‹እግዚአብሔር በድምፁ ድንቅኛ ያንጐደጒዳል፤እኛም የማናስተውለውን ታላቅ ነገር ያደርጋል፡፡ በረዶውንና ውሽንፍሩን ብርቱንም ዝናብ በምድር ላይ ውደቁ ይላል፡፡››



 (ማመሳከሪያ፡- መክ 3፤11፡፡‹‹ነገሩን ሁሉ በጊዜው ውብ አድርጎ ሠራው››፤ኢዮብ 36፡ 29፡፡ ‹‹የደመናትን ንብርብር፣ ከድንኳኑንም የሚሰማውን ነጐድጓድ ማን ሊያስተውል ይችላል?››፤ መዝ 147፡6፡፡ ‹‹በረዶውን እንደ ፍርፋሪ ያወርዳል፤ በበረዶውስ ፊት ማን ይቆማል፡?›› አሞጽ 9፡6፡፡ አዳራሹን በሰማይ የሠራ፣ ጠፈሩንም በምድር ላይ የመሠረተ፣ የባሕርንም ውሃ ጠርቶ በምድረ ፊት ላይ የሚያፈስሰው እርሱ ነው፤ ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡)
ልበ እግዚአብሔር ዳዊት እንዳለውም (73፡16-17)፣ ‹‹አንተ ፀሐይንና ጨረቃን አዘጋጀህ፤ አንተ የምድር ዳርቻን ሁሉ ሠራህ፤ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ፡፡››
በክረምት ውስጥ የምንቈየው ለ96 ቀኖች ነው፡፡ ዘንድሮ ጳጉሜን ስድስት በመሆኗ የአንድ ቀን ጭማሪ አለ፡፡ ክፍለ ዓመቱ ክረምት እስከ መስከረም 25፣ 2008 ዓ.ም. በሚኖረው ቆይታ ዘጠኝ ንኡሳን ክፍሎችን ያስተናግዳል፡፡ ለአሁን ግን እስከ ዓመቱ (2007) መካተቻ ጳጉሜን 6 ድረስ ያሉትን እንዘረዝራለን፡፡
(ሀ) ከሰኔ26- ሐምሌ18 -‹‹ዘር፣ ደመና››
(ሁ) ከሐምሌ19- ነሐሴ9 -‹‹መብረቅ፣ ነጐድጓድ፣ ባሕር፣ አፍላግ (ወንዞች)፣ ጠል››
(ሂ) ከነሐሴ10- 27 - ‹‹ዕጒለ ቋዓት (የቁራ ጫጩት)፣ ደስያት (ደሴቶች)፣ዐይነ ኵሉ (የሁሉም ዓይን)››
(ሃ) ከነሐሴ 28- ጳጉሜን 5 ወይም 6- ‹‹ጎህ (ወጋገን)፣ ነግህ (ንጋት)፣ ጽባሕ (ጠዋት)፣ ብርሃን፣ መዓልት (ቀን)፣ ልደት››
ፀደዩን እንዳስፈጸመን ክረምቱንም በሰላም አስፈጽሞ ለመፀዉ ያብቃን፡፡ ደኅና ያክርመን፡፡
ሰላም ወሰናይ፡፡፡፡
ምንጭ፡- በአራቱ ወቅቶች ላይ የተመሠረተው የአለቃ ያሬድ ፈንታ ወልደ ዮሐንስ ‹‹መጽሐፈ ግጻዌ ሐዲስ ዘተሰናአወ በአርባዕቱ ክፍላተ አዝማን›› (1997)
የአለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› (1948)
-    ኖክ መደብር

No comments:

Post a Comment