Saturday, July 4, 2015

በዩኔስኮ የተመዘገበው ያልታወቀው ባለ79 ዓመቱ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰነድ - ተጻፈ በሔኖክ ያሬድ -05 July 2015

‹‹… ከእግዚአብሔር መንግሥት በቀር የፍጡር መንግሥት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ ሥራ የለውም፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው
መስሎት በተነሳበት ጊዜ ተጠቂው ወገን ለመንግሥታት ማኅበር የተበደለውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔር ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ለመንግሥት ማኅበርም ምስክር ሆነው ይመለከታሉ…›› 
ከ80 ፈሪ ዓመት፣ ማለትም ከ79 ዓመት በፊት ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም. የመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (1923 – 1967) ርእስ የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የፋሺስት ኢጣሊያን ወረራ አስመልክቶ በጄኔቭ የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ሸንጎ ላይ ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ኃይለ ቃል ነው፡፡ 
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን (1888 ዓ.ም.) ዓድዋ ላይ ድል የተመታው የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ በፋሺስቱ ቤኔቶ ሙሶሎኒ አማካይነት ኢትዮጵያን መውረሩና በተለይ በዓለም የተከለከለው የመርዝ ጋዝ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሠራዊት በ1928 ዓ.ም. መፈታቱ ይታወሳል፡፡ 
እርመኛ አርበኞች የአገሪቱን ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ መራር ተጋድሎ ማድረጋቸውም ባይዘነጋም የፋሺስት ወንጀለኞች በታኅሣሥ 1928 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት፣ በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዝ ያደረሱት እልቂት ይጠቀሳል፡፡ 
በስደት ወደ አውሮፓ የዘለቁት ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከክብር ተከታዮቻቸው ጋር ሆነው ዲፕሎማሲያዊ ተጋድሎ ማድረጋቸው በታሪክ ተመዝግቧል፡፡ አንዱና ቀዳሚዋ ኢትዮጵያ አባል ለሆነችበትና መቀመጫውን ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ላደረገው የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) የግፍ ወረራውን በመቃወም ለሥዩማኑ አቤት ማለት ነበር፡፡ 
በአንድ በኩል የኢጣሊያው አምባገነን ቤኒቶ ሙሶሎኒ ኢትዮጵያን በመጠቅለል በአፍሪካ የኢጣሊያ ግዛት መመሥረቱን አገሪቱንም መያዙን ሲያውጅ፣ አዲስ አበባንም ፋሺስቶች ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. ከመያዛቸው አስቀድሞ የተሰደዱት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሙሶሎኒን መግለጫ በመቃወም ለመንግሥታቱ ማኅበር አቤት ቢሉም ድጋፍ አላገኙም፡፡ አብዛኛዎቹ የሊግ ኦፍ ኔሽንስ አባል አገሮች ለኢጣሊያ ወረራ እውቅና ሰጥተው ነበርና፡፡ 
ይሁን እንጂ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በአገር ባህል ልብስ ተውበው፣ ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም. በጄኔቭ የምክር ቤቱ አዳራሽ በመገኘት ትንቢታዊና አስደናቂ ንግግር ያደረጉት በአማርኛ ቋንቋ ነበር፡፡ እንዲህም ብለው ነበር፡፡ 
‹‹ዛሬ የመንግሥታት ማኅበር ዋና ጉባዔ በፊቱ ያለው ጉዳይ ኢጣልያ በአጥቂነት የሠራችውን ለመጨረስ ብቻ አይደለም፡፡ በሙሉ የዓለምን መንግሥታት የሚነካ ጉዳይ መሆኑን አረጋግጬ አስታውቃለሁ፡፡ ይህም ጉዳይ ለዓለም ጸጥታ እንዲሆን መንግሥታት ለመረዳዳት የሚገባቸው ሴኩሪቲ ኰሌክቲፍ የተባለው የመንግሥታት ማኅበር ሕይወት፤ የዓለም መንግሥታት ለተዋዋሉት ውል መስጠት የሚገባቸው እምነት፤ ትንንሾቹም መንግሥታት አገራቸውና ነጻነታቸው እንዳይነካ የተቀበሉት ቃል ኪዳን የሚከበርበትና ዋጋው የሚገመትበት፤ የመንግሥቶች ትክክልነት የተመሠረተበት መሠረት፤ ይህን ለማድረግ ወይም ትንንሾች መንግሥቶች የኃይለኞች መንግሥቶች ተገዢ ለመሆን መቀበል ይገባቸው እንደሆነ ለመፍረድ ነው፡፡ 
‹‹በአጭር ቃል የተነካውና የተበደለው የዓለም ሕዝብ የሚገባ አንዋወር ነው እንጂ ኢትዮጵያ ብቻ አይደለችም፡፡ በአንድ ውል ላይ የተፈረሙ ፊርማዎች ዋጋቸውን የሚያገኙት የፈረሙት መንግሥቶች አንዱ በሌላው ላይ የግል ጥቅሙን በቀጥታና በፍጥነት ለማግኘት ለመፈጸምም እንዲችል እንዲረዱት ሲሆኑ ነውን?
‹‹በረቂቅ መንገድ መበላለጥ ዋናውን ነገር ሊለውጠው ወይም የክርክሩን መንገድ በሌላ በኩል ሊመራው አይገባም፡፡ ይህንንም ማመልከቻ ለመንግሥታት ማኅበር ዋና ጉባዔ የማቀርበው በእውነተኛነትና ከልቤ ነው፡፡ 
‹‹ሕዝቤ ዘሩ ሊጠፋ በደረሰበት የመንግሥታት ማኅበርም እርዳታ ከጥፋት ለማዳን በሚችልበት ጊዜ ማናቸውንም ሳላስቀርና፤ የመንግሥታት ማኅበር ማኅበርተኞች መንግሥቶች ሁሉ ያላቸው የትክክለኛነት ደንባቸው እንደሚያስገድደኝ፤ ሳላቆይና ሳላስቀር በተዘዋዋሪ ቃል ሳይሆን እውነቱን አውጥቼ እንድናገር ሊፈቀድልኝ የተገባ ነው፡፡ 
‹‹ከእግዚአብሔር መንግሥት በቀር የፍጡር መንግሥት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ ሥራ የለውም፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው መስሎት በተነሳሣበት ጊዜ፤ ተጠቂው ወገን ለመንግሥታት ማኅበር የተበደለውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔርና ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ለመንግሥታት ማኅበርም ምስክር ሆነው ይመለከታሉ፡፡››
በቁም ጽሕፈት የተጻፈው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንግግር (ዲስኩር) ከፈረንሣይኛ ትርጉሙ ጋራ ግራና ቀኝ ሆነው በሊጉ ቤተ መዛግብት ተጠብቆ ኖሮ በ1938 ዓ.ም. በጄኔቭ ወደ ሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ተዘዋውሮ ተቀምጧል፡፡ የመንግሥታቱ ድርጅት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከአምስት ዓመት በፊት በ2002 ዓ.ም. የዓለም ቅርስ አድርጎም መዝግቦታል፡፡ 
ወርልድ ዲጂታል ላይብረሪ (World Digital Library) በድረ ገጹ ያሰፈረውም፣ ‹‹The text is preserved in the archives of the League, which were transferred to the United Nations in 1946 and are housed at the UN office in Geneva. They were inscribed on the UNESCO Memory of the World register in 2010›› ይህንኑ ያንፀባርቃል፡፡ 
ኢትዮጵያ የንግግሩ ሰነድ መመዝገቡን ታውቃለች?
ኢትዮጵያ የዓይነተ ብዙ ቅርስ ባለቤት መሆኗ ይታወቃል፡፡ በጉያዋ የያዘቻቸውን ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ቅርሶች ትተን በዩኔስኮ የተመዘገቡት ብንቆጥር ዘጠኝ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ቅርሶች፣ አንድ የማይዳሰስ ቅርስ (የመስቀል በዓል) የብዝኃ ሕይወት አራት ቦታዎችና የሥነ ጽሑፍና የመዛግብት ቅርሶች መኖራቸው ከሚመለከታቸው አካላት በየጊዜው ሲነገረን ቆይቷል፡፡ 
በሥነ ጽሑፍ ዘርፍ የሚመዘገቡት ቅርሶች የሚመለከተው ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ 12 የኢትዮጵያ የጽሑፍ ቅርሶች መመዝገባቸው ከልዩ ልዩ ሰነዶች ባሻገር በቅጥር ግቢው የሰቀለው ሰሌዳ (ቢልቦርድ) ያመለክታል፡፡ 
ከአገሮች ሌላ ዓለም አቀፍ ድርጅቶችም መዝገቦቻቸውንና ልዩ ልዩ ሰነዶቻቸውንም አስመዝግበዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቀድሞው የመንግሥታቱ ማኅበር ሊግ ኦፍ ኔሽንስ ይገኝበታል፡፡ ጄኔቭ በሚገኘው ጽሕፈት ቤቱ እ.ኤ.አ. ከ1919-1946 (ከ1911 ዓ.ም. – 1938 ዓ.ም.) የተሰባሰቡ መዛግብት በዩኔስኮ ሲመዘገቡ አንዱ የተመዘገበው የ1928 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንግግርን የያዘው ሰነድ ነው፡፡ ይህ ባለ 20 ገጽ በአማርኛና በፈረንሳይኛ የተጻፈው የንጉሠ ነገሥቱ ንግግር ብሔራዊ ቤተ መዛግብት ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ እንደ 13ኛ ቅርስ ያልያዘው ምዝገባው በርሱ በኩል ባለመከናወኑ ነው ወይስ በሌላ ምክንያት?

1 comment: