Saturday, June 13, 2015

ጣና ሐይቅ የዓለም ብዝኃ ሕይወት ቅርስ

4 June 2015 ተጻፈ በ 


ከግማሽ ምእት ዓመት በፊት በሰሜናዊት ኢትዮጵያ የነበሩ የመረብ ምላሽ ተማሪዎች በልጅ ናፍቆት ይዘምሩት ከነበረው መካከል አንዱ
‹‹ባሕረ ጻና ብሩር
 ዕንቋ ሽልማታ፣

ባሕረ አፍሪቃ ምሉእ ዕጣቃ ደረታ›› የሚለው ነው፡፡ ብርሃን የለበሰ ንጹሕ የጣና ባሕር ለብሔረ አግዓዚ (ለኢትዮጵያ) ዕንቋ ሽልማቷ ነው፡፡ የአፍሪካ ባሕሮችም እንደ ቅናቷ (መታጠቂያ) ሆነው ይከቡዋታል፤ ድንበርም ሆነውላታል ማለት እንደሆነ ‹‹የኢትዮጵያ ውበት›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ዶ/ር አባ ገብረ ኢየሱስ ኃይሉ ከ47 ዓመት በፊት ጽፈው ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ሐይቆች በስፋትም በታሪካዊነትም በቀዳሚነትም የሚጠቀሰው ለአፍሪካ መከበቢያ እንደሆነ የተነገረለት ጣና ሐይቅና አካባቢው ዘንድሮ ላይ ከወንዙ፣ ከመንደሩ፣ ከአገሩ ከአህጉሩ አልፎ የዓለም ቅርስ የብዝኃ ሕይወት መለያ ሆኖ መመዝገቡን ዓለም አቀፍ የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ በድረ ገጹ አስታውቋል፡፡
ሰኔና ሰኞ በገጠሙበት ዕለት በፈረንሳይ መዲና ፓሪስ ከሰኔ 1 ቀን እስከ ሰኔ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ጉባኤውን ያካሄደውና የብዝኃ ሕይወት ጉዳይን የሚመረምረው ዓለም አቀፉ ምክር ቤት ጣና ሐይቅን ጨምሮ በዓለም ዙርያ የሚገኙ 20 የብዝኃ ሕይወት ጥብቅ ቦታዎች የዓለም ቅርስ ሆነው መመዝገባቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ተቋሙ እስካሁን  በዓለም ዙሪያ ከመዘገባቸው 651 ቦታዎች 15ቱ ድንበር ተሻጋሪዎች ናቸው፡፡ የጣና ሐይቅ ብዝኃ ሕይወት ከጌድኦና ሸካ ጥብቅ ደን ብዝኃ ሕይወት ቀጥሎ በዩኔስኮ የተመዘገበ አራተኛው የኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ቅርስ ሆኗል፡፡
•የጣና ብዝኃ ሕይወት ሲገለጥ
የጣና ሐይቅ ብዝኃ ሕይወት ጥብቅ ስፍራ በሰሜናዊ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሲገኝ ታላቁን የኢትዮጵያ ሐይቅ ጣና ሐይቅን ያካትታል፡፡ በዩኒስኮ ድረ ገጽ እንደተጻፈው ጥብቁ ስፍራ አጠቃላይ ስፋቱ 695,885 ሔክታር ሲሆን ብዝኃ ሕይወት ተንጣሎ ይታይበታል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በአዕዋፋት መናኸሪያነት ከመታወቁም በተጨማሪ ለዓለም ግብርና ዘረ መል ብዙኃነትም ጠቀሜታ አለው፡፡
በአካባቢው ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ የተመሠረተው በእርሻ በዓሣ ዕርባታ፣ ከአገር ውስጥና ከውጪ ቱሪስቶች ከሚገኘው ገቢ ነው፡፡ አካባቢው ልዩና ብርቅዬ ባህላዊ ታሪካዊ፣ ጂኦሎጂካዊና ሥነ ውበታዊ እሴቶችን ከ13ኛው ምእት ዓመት ጀምሮ ከተመሠረቱ በርካታ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናትንም ይዟል፡፡
በጣና ሐይቅ ዙርያ ያሉት አብያተ ክርስቲያናት የያዟቸው ደኖች የተለያዩ የዛፍ ዓይነቶችንና የአበባ ዝርያዎች፣ የሕክምና ተክሎችን ያቀፉ ሲሆን ብዝኃ ሕይወትን በመጠበቅ ረገድ ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ ብዝኃ ሕይወቱ በጥብቅ ስፍራነት መመዝገቡ የአካባቢው ማኅበረሰቦች ባህላቸውን ዕውቀታቸውንና ክሂሎታቸውን የሚያከብሩበትና የሚያደንቁበት የሚንከባከቡበትም ዕድል የመፍጠር፣ ለዘላቂ የአኗኗር ዘዬ ከአካባቢው ጋር ተጣጥሞ እንዲኖር ለማስቻል እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
•በጣና ሐይቅ ጉያ
ጣና ሐይቅ በጥንታዊ ቋንቋ (ግእዝ) አገላለጽ ‹‹ጻና ሐይቅ›› ይባላል፡፡ የሐይቁ ቅርጽ ከሕዋ ላይ ሆነው ሲያዩት የሰውን ልብ ይመስላል፡፡ በሰፊው ሰሜናዊ ዳሩ ደምቢያን ስለሚከብ ‹‹ደምቢያ›› የሚሉትም አልታጡ፡፡ የዓባይ ምንጭ ብቻ ሳይሆን ከኢትዮጵያ ሐይቆች ሁሉ ይተልቃል፡፡ ከባሕር ወለል 1,788 ሜትር ከፍታ የሚገኘው ሐይቁ ከሰሜን እስከ ደቡብ ያለው የሐይቁ ርዝመት 85 ኪሎ ሜትር ሲቃረብ ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ ያለው ስፋቱም 66 ኪሎ ሜትር ተገምቷል፡፡
ለጣና ገባር የሆኑ ዥረቶች እስከ ስድሳ የሚደርሱ ሲሆን ቀዳሚ ተጠቃሾቹ ግልገል ዓባይ፣ ርብ እና ጉማራ ወንዞች ናቸው፡፡ ከነዚህ በተለይ ግልገል ዓባይ ወንዝ መጠኑ ከፍ ያለ ሲሆን ከጣና ሐይቅ በስተደቡብ 200 ኪሜ ርቀት ላይ ከግሽ ዓባይ የሚፈልቀው ዓባይ፣ የዋነኛው የዓባይ (ናይል) ወንዝ መሠረታዊው ምንጭ እንደሆነ ይወሳል፡፡ በዱሮው አጠራር በአቸፈርና በሜጫ አውራጃዎች መሐከል ሆኖ ወደ ባሕሩ (ሐይቁ) ይገባል፡፡ ዶ/ር አባ ገብረ ኢየሱስ እንደጻፉት፣ ‹‹ዓባይ ዳር የተባለውን ርእሰ ምድር ብንመለከትም ከውሀው ጋር ለባሕረ ጻና [ጣና ሐይቅ] ብዙ መሬትን ይገብራል፡፡
ይህም ማንኛውም ወንዝ ያለው የተፈጥሮ ተግባሩ ነው፡፡ ግብፅ ራሱም ከኒል ዓባይ ወንዝ ተወለደ ይባላል፡፡ ምክንያቱም ከውሀው ጋር ብዙ መሬት እየገፋ ስለ አመጣለትና የጨዋማ ባሕር ዳርም ወደ ኋላው ስላፈገፈገለት ነው፡፡ ትንሹ ዓባይ ከደቡብ ወደ ሰሜን እየመጣ የውሀና የመሬት ግብር የከፈለውን፤ ትልቁ ዓባይ ከሰሜን ወደ ደቡብ እያወጣ ውሀውን እያስፋፋ መሬቱን ይገፋልና ባሕረ ጻናን በሁለቱ ዓይነት ያስገብረዋል፡፡ የባሕረ ጻና ስፋት ካሁኑ ይበልጥ እንደነበረ ከባሕሩ ዳር እስከ አንድ መቶ ሜትር ርቀው የሚገኙት የመሬቱ ድርቅ ዓይነቶች ይመሰክራሉ፡፡››
•ገዳማቱ
በጣና ሐይቅ ከ13ኛው ምእት ዓመት ጀምሮ በየዘመኑ እንደተመሠረቱ የሚነገርላቸው በርካታ ደሴቶች ያሉ ሲሆን በየዘመኑ ከሚያጋጥመው የሐይቁ የውሀ ከፍታ መጠን መውረድ ጋር በተያያዘ ቁጥራቸው ተለያይቷል፡፡ ለአብነትም ከ400 ዓመታት በፊት ጎራ ብሎ የነበረው ፖርቱጋላዊው ሚሲዮናዊ ማኖኤሊ ደ አልሜዳ 21 ደሴቶችን ሲመዘግብ፣ በ18ኛው ምእት ዓመት የመጣው ጀምስ ብሩስ 45 ደሴቶች አሉ መባሉን ሲጠቅስ፣ የ20ኛው ምእት ዓመት ጂኦግራፈር 37 ደሴቶች እንዳሉ በነርሱም 19 ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት መኖራቸውን ጽፏል፡፡
በገዳማቱ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅርሶች፣ ጥንታውያን የ13ኛው ምእት ዓመት የብራና መጻሕፍት፣ ሥዕላት ወዘተ እንዲሁም የቀድሞ ነገሥታት አፅም ይገኛሉ፡፡
በሐይቁ ከሚገኙት ገዳማት መካከል ጣና ቂርቆስ፣ ዳጋ እስጢፋኖስ፣ ኮታ ማርያም፣ መሐል ዘጌ ጊዮርጊስ፣ ዑራ ኪዳነ ምሕረት፣ ክብራን ገብርኤል፣ እንጦስ ኢየሱስ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ገዳማት በ14ኛ ምእት ዓመት አቡነ መድኃኒነ እግዚእ ባመነኮሷቸው ‹‹ሰባቱ ከዋክብት›› ተብለው በሚጠሩት ቅዱሳን አባቶች የተመሠረቱ መሆናቸው ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡
በአፄ ይኩኖ አምላክ ዘመነ መንግሥት (በ13ኛው ምእት ዓመት) በአቡነ ሒሩት አምላክ እንደተመሠረተ የሚነገረው የዳጋ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን በመርከብ ቅርፅ የተሠራ ሲሆን፣ ምሳሌውም በጥፋት ውኃ ዘመን የሰው ዘር በኖኅ መርከብ አማካይነት መዳኑን  ለማመልከት እንደሆነ መምህራኑ ይናገራሉ፡፡

( http://ethiopianreporter.com/index.php/life-and-art/item/9993-)

No comments:

Post a Comment