Saturday, March 14, 2015

በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደረሰ ሰደድ እሳት የአንድ ባለሙያ ሕይወት አጠፋ

ሪፖርተር 15 March 2015 ተጻፈ በ 

በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደረሰ ሰደድ እሳት የአንድ ባለሙያ ሕይወት አጠፋ

የደቡብ አፍሪካ ባለሙያዎች ድጋፍ ለመስጠት አዲስ አበባ ገቡ
በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ መሰንበቻውን የደረሰውን የሰደድ እሳት አደጋ ለማጥፋት ተንቀሳቅሰው ከነበሩት ባለሙያዎች መካከል በአንዱ ላይ የሞት፣ በሌሎቹ ሁለት ባለሙያዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደረሰ፡፡
የደረሰውን የእሳት አደጋ ለማጥፋት ባለሙያዎችን የያዘች የደቡብ አፍሪካ እሳት አደጋ ተከላካይ አውሮፕላን መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብታለች፡፡
ከሳምንት በፊት በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆነው አቶ ቢንያም አድማሱ ሕይወቱን ሲያጣ፣ ሌሎች ሁለት ባለሙያዎች የመለብለብ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና የመረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ዘውዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሰደድ እሳቱ ከአጠቃላዩ የፓርኩ ይዞታ አምስት ከመቶ በሚሆነው ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በአካባቢው የተፈጠረውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት የፓርኩን ዋርዶች ጨምሮ አጋር ድርጅቶችና ማኅበረሰቡ ባደረጉት ርብርብ በሁለት ወረዳዎች የተነሳውን እሳት ቢቆጣጠሩትም፣ ጎባ ሳይት በተባለው አካባቢ የተነሳውን ለማጥፋት በሚጥሩበት ወቅት የተነሳው ንፋስ እሳቱን በማባባሱ፣ በባለሙያዎቹ ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡
በፓርኩ አካባቢ የደረሰው እሳት በአመዛኙ ቢጠፋም በጎባ በኩል ባለው ቁጥቋጦና ቀርከሃ ላይ የተከሰተው ግን ሙሉ ለሙሉ እንዳልጠፋ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ እሳቱ ወደ ፓርኩ አለመድረሱን ግን አውስተዋል፡፡
እሳቱን ለማጥፋት እየተደረገ ያለውን ርብርብ ለማገዝ የደቡብ አፍሪካ ባለሙያዎች ከናይሮቢ የእሳት አደጋ መከላከያ አውሮፕላን ይዘው ባለፈው ዓርብ አዲስ አበባ መድረሳቸውን፣ ኮሚቴውን ወደ እሳቱ ቦታ ከማመላለስና ሙያዊ ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ የእሳት ማጥፋት ሥልጠና እንደሚሰጡና ሥራቸውንም ወደ ፓርኩ መጋቢት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በመሄድ እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡
ፓርኩ ከ95 በመቶ በላይ ደህና መሆኑ፣ ከዱር እንስሳቱም ብዙም የተጎዱ አለመኖራቸውና እሳቱ የደረሰበት ቦታ ላይ የነበሩ እንስሳት መሰደዳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ብዙ የተጎዱ የሉም፤ እሳቱ ሲመጣ ይሰደዳሉ ሳሩ ሲበቅል ተመልሰው ይመጣሉ፤›› ብለዋል፡፡
 የአደጋው መንስዔ እየተጣራ መሆኑንና ያለው ጥርጣሬ ከፓርኩ ውጪ የሚገኝ አካባቢን ለከብት ግጦሽ ለመጠቀም በተለኮሰ እሳት በመሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክተዋል፡፡
በአደጋው ሕይወቱ ያለፈው የወጣቱ ባለሙያ ቢንያም አድማሱ ሥርዓተ ቀብር በባሌ ዶዶላ ከተማ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. መፈጸሙ ታውቋል፡፡
ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በሥነ ጽሑፍ  ያገኘውና በቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን የወሰደው የ31 ዓመቱ አቶ ቢንያም፣ ከአካባቢ ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ጋር የተያያዘ ሥራ በሚሠራው ፍራንክፈርት ዙኦሎጂካል ሶሳይቲ ባልደረባና የቱሪዝም ልማት አማካሪ ሲሆን፣ ከተቋሙ ጋር በመሆን በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ በአቡነ ዮሴፍ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ፣ በመንዝ ጓሳ ጥብቅ ስፍራ፣ በአርሲ አካባቢዎችና በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አያሌ ሥራዎችን ማከናወኑ ይነገርለታል፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ዘላቂ ቱሪዝም ትብብር (ኢስታ) የቱሪዝም ልማት ቴክኒክ አማካሪ ሆኖ ሠርቷል፡፡
ከአዲስ አበባ 400 ኪሎ ሜትር ርቆ በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘውና በ1962 ዓ.ም. የተቋቋመው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ጠቅላላ ስፋቱ ከ2,200 ካሬ ኪሎ ሜትር  በላይ ሲሆን፣ ከባሕር ጠለል ከ1,500 ጫማ እስከ 4,377 ጫማ የሚለካ ከፍታ አለው፡፡  የደጋ፣ የወይና ደጋና የቆላ ሥነ ምኅዳሮችና ትልልቅ የዕፀዋት (ቨጂቴሺን) ዞኖች አሉት፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ከ1,600 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት ዕፀዋት፣ 78 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሳትና 200 የሚጠጉ አዕዋፋት በፓርኩ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል 32 ዓይነት ዕፀዋት፣ 31 ብርቅዬና ድንቅዬ  የዱር እንስሳትና  ስድስት  ዕፀዋት በብሔራዊ ፓርኩ ካልሆነ በስተቀር በሌላው ዓለም ፈጽሞ አይገኙም፡፡
ከዚህም ባሻገር ለሳይንስና ኢኮሎጂ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው በደረታቸው የሚሳቡ ልዩ ልዩ እንስሳትና መንቆረረቶችን ፓርኩ አቅፎ ሲይዝ፣ ቡና እና ለባህል መድኃኒትነት የሚውሉ 40 በመቶ የአገሪቱ ዕፀዋትም ይገኙበታል፡፡
ብሔራዊ ፓርኩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ ከመካተቱም በተጨማሪ፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ብዝኃ ሕይወት ያለው በመሆኑ በዓለም 34ኛው በጣም ጥበቃ የሚያስፈልገው የብዝኃ ሕይወት (ሴንሲቲቭ ባዮዳይቨርሲቲ) አካባቢ መሆኑም ይታወሳል፡፡ በዓለም አቀፍ የወፎች ድርጅትም የአፍሪካ አራተኛው የአዕዋፋት መናኸሪያ (በርዲንግ ሳይት) ተብሎ ተመዝግቧል፡፡

No comments:

Post a Comment