Saturday, March 7, 2015

ዛሬ የካቲት 29 ቀን2007 ከትንሣኤ በፊት 5ኛ እሑድ እና የዐቢይ ጾም 3ኛ እሑድ


የዐቢይ ጾም 8ቱ እሑዶች (ሰንበታተ ክርስቲያን) መጠርያ እነሆ፡፡
የካቲት 8 :  ዘወረደ እሑድ /ቅበላ፤ የካቲት 15፡ ዘቅድስት እሑድ፤ የካቲት 22፡ ዘምኩራብ፤  የካቲት 29 ዘመፃጉዕ፤ መጋቢት 6፡ ዘደብረ ዘይት፤  መጋቢት 13፡ ዘገብረ ኄር፤  መጋቢት 20፡ ዘኒቆዲሞስ፤ መጋቢት 27፡ ዘሆሣዕና፤ ሚያዝያ 4፡ ዘትንሣኤ እሑድ፡፡

ዛሬ የካቲት 29 ቀን ከትንሣኤ በፊት 5ኛ እሑድ ላይ እና የዐቢይ ጾም 3ኛ እሑድ ላይ እንገኛለን፡፡ መጠርያውም ‹‹መፃጉዕ›› ይባላል፤ አካሉ የተጎዳ ማለት ነው ፡፡ የዛሬዋ ሰንበት የምታስታውሰን ጌታችን 38 ዓመት (ሁለት ንኡስ ቀመር፡ 19*2 ) ሙሉ  ‹‹በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ›› የተያዘውን ፍጡር (ዮሐንስ 5፡5) የፈወሰበት ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ በድጓው ለሠራው መዝሙር ለዕለቱ የሰጠው ርእስ ‹‹አምላኩሰ ለአዳም›› ማለትም የአዳም ፈጣሪው የሚል ነው፡፡ የክርስቶስ ኢየሱስ ፈዋሽነትን  ዘምሮታል፡፡ ‹‹አምላኩሰ ለአዳም ለዕረፍት ሰንበተ ገብረ›› (የአዳም አምላክ ግን ሰንበትን የፈጠረው ለዕረፍት ነው)፡፡ በሰንበት- የጎበጡትን ያቀናበት እንዲራመዱ ያደረገበት፣ ዓይናቸው የተሰወረውን ያበራበት ነው፡፡
በዕለቱ የሚሰበከው ምስባክም በመዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ 40 ቁጥር 3-4 ላይ እናገኘዋለን፡፡
-        እግዚአብሔር ይረድኦ ውስተ  ዐራተ ሕማሙ፤  
         (እግዚአብሑር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል)
         ወይመይጥ ሎቱ ኵሎ ምስካቢሁ እምደዌሁ፤
         (መኝታውንም ሁሉ ከበሽታው ሁሉ የተነሣ ይለውጥለታል)
         አንሰ እቤ እግዚኦ ተሣሀለኒ፡፡
         ( እኔስ፡ አቤቱ ይቅር በለኝ አልሁ፡፡)

ምንጭ፡- 
 መጽሐፍ ቅዱስ፡ የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት (2000 ዓ.ም.)                                  አራቱ ወቅቶችን ክረምትና መፀው፣ በጋና ፀደይ- መሠረት አድርጎ የተዘጋጀው                          የአለቃ ያሬድ ፈንታ  ወልደዮሐንስ  ‹‹መጽሐፈ ግጻዌ ሐዲስ›› (1997 ዓ.ም.)
       (ሔኖክ መደብር )

No comments:

Post a Comment