15 March 2015
ተጻፈ በ
ሔኖክ ያሬድ
ባንክ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዳግማዊ ምኒልክ
ዘመን ‹‹ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ›› ተብሎ ከተቋቋመበት በመቀጠል በ1923 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ
በማስከተልም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቋቋም በመሪነት ተቀምጠው የነበሩት የውጭ አገር ዜጐች ነበሩ፡፡ ታሪካዊቷ
1953 ዓ.ም. እስከመጣችበት ጊዜ ድረስ፡፡ ‹‹ቀን ሲደርስ አምባ ይፈርስ›› ነውና፡፡
ገንዘብ ለለውጥ ፈር ቀዳጅነት ብለው ከተነሱ
ኢትዮጵያውያን መካከል ኢትዮጵያዊውን የመንግሥት ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ለመምራት የበቁት አቶ
ተፈራ ደግፌ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ መንግሥትነት ታሪክ በፋይናንስ ዘርፍ ሁነኛ ሥፍራ የነበራቸው አቶ ተፈራ
ዛሬ በአፀደ ሥጋ የሉም፡፡ ለዓመታት ይኖሩበት በነበረችው ካናዳ ዜና ዕረፍታቸው የተሰማ ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብራቸውም
እዚያው ካናዳ ቫንኩቨር ከተማ ተፈጽሟል፡፡ አቶ ተፈራ በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ የፈጸሙት አገልግሎት ከ1934 እስከ
1968 ዓ.ም. ድረስ ለ34 ዓመታት በዘርፈ ብዙ ሥምሪት የዘለቀ ነበር፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ድል ከተመታ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ዳግም ሲቋቋም የባንክና የገንዘብ ሥርጭት ከእንግሊዝ የምሥራቅ አፍሪካው የቅኝ አገዛዝ ጋር አቀላቅሎ ለማስተዳደር፣ በእንግሊዝ በኩል የነበረው ግፊትና ኢትዮጵያ ተነጥላ የራሷን ባንክ ለማቋቋም ስትነሳ ያጋጠመውን ብዙ ችግር ሰብሮ በመውጣት ረገድ በነበረው ጉዞ የአቶ ተፈራ ደግፌ ሁነኛ ሚናም ይጠቀሳል፡፡
አቶ ተፈራ ማኅበራዊ ጥናት መድረክ በአንድ ወቅት ‹‹ተፈራ ደግፌ የባንክ ዕድገት ለአገሪቱ ልማት ያደረገው አስተዋጽኦ›› በሚል ባዘጋጀው ‹‹ከድህነት ወደ ልማት፣ ዕውቀትን ለትውልድ ማስተላለፍ›› መድረክ ላይ ሲናገሩ፣ ‹‹በ1937 ዓ.ም. በአሜሪካ በሚስጥር ተዘጋጅቶ አዲስ የኢትዮጵያ ብር ገንዘብ ታውጆ ወጣ፡፡ በዚህ ዓይነት ነው የኢጣሊያ ሊሬ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሺሊንግ በአዲሱ የኢትዮጵያ ብር የተለወጠው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የባንክ ሥራው ቀስ በቀስ እየሰመረ የሄደው፤›› ብለው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የንግዱ ክፍል ቅርንጫፍ በካርቱም (ሱዳን) በ1950 ዓ.ም. ሲከፈት የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት አቶ ተፈራ፣ በወቅቱ በየድርጅቱ የውጭ አገር ዜጐች ስለነበሩ ‹‹ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክን ለመምራት ብቁ አይደሉም፤›› የሚለውን አስተሳሰብ በመስበር፣ ከ1937 እስከ 1952 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክን ከመሩት ስድስት የውጭ አገር ዜጐች መንበሩን በመጨበጥ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆነዋል፡፡ በእርሳቸው ፋና ወጊነት የተጀመረው መሪነት እስካሁን ዘልቋል፡፡
አቶ ተፈራ ሱዳን ለተከፈተው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ (በአገሬው ወዳጃዊ አጠራር ‹‹ባንክ ኤል ሐበሺ››) ሥራ አስኪያጅነት በጽሕፈት ሚኒስቴር ማዘዣ ከመሾማቸው በፊት የሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ነበሩ፡፡
አቶ ተፈራ ከአባታቸው አቶ ደግፌ በላይነህ፣ ከእናታቸው ወ/ሮ እርገጫቸው ገብረ ማርያም ሰኔ 8 ቀን 1918 ዓ.ም. የተወለዱት በሸዋ ጠቅላይ ግዛት አንኮበር አውራጃ አንበሴ ቀበሌ ሲሆን፣ ያደጉት ገንዳ ውኃ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነው፡፡ ትምህርታቸውን በአሊያንስ ፍራንሴዝ፣ በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤቶች ከተከታተሉ በኋላ በ1938 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ካናዳ በመሄድ በካልጋሪ አልበርታ ንግድ ኮሌጅ ዲፕሎማ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብሪትሽ ኮሎምቢያ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ለሁለት ዓመትም የሕግ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡
የአማርኛ፣ የጣሊያንኛ፣ የመስኮብኛ (እሳቸው እንደሚሉት)፣ የፈረንሳይኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተናጋሪ የነበሩት አቶ ተፈራ፣ ከባሕር ማዶ መልስ የሠራተኛነት ጉዟቸው የተጀመረው በኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ መሥሪያ ቤት በጸሐፊነት ደረጃ ሲሆን፣ ቀፕሎም የባንኩ ነገረ ፈጅ ሆነው ነበር፡፡ በ1953 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለመሆንም በቅተዋል፡፡
ከ1956 እስከ 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በመሆን ማገልገላቸው ራሳቸው የጻፉት ግለ ታሪካቸው ያሳያል፡፡
አብዮቱን ተከትሎ የቀዳማዊ ኃይሌ ሥላሴ ምሥል የነበረበት የኢትዮጵያ ብር ሲለወጥ፣ አቶ ተፈራ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበርነታቸው የእርሳቸው ፊርማ ያረፈበት ገንዘብ የታተመውና የተሠራጨው በ1969 ዓ.ም. ነበር፡፡ ወዲያው በዚያው ዓመት ደርግ ‹‹ለአብዮቱ እንቅፋት እንዳትሆን›› በማለት ለሰባት ዓመታት አስሯቸው ነበር፡፡
አቶ ተፈራ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ቫንኩቨር የሚገኘው የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ፋኩልቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጣቸው ሲሆን፣ ጡረታ ከወጡ በኋላ እስከ ሕልፈታቸው ድረስ የኖሩት በካናዳ ነበር፡፡
ከሊቃውንቱ (ከኢንቴለጄንሺያው) መካከል የሚጠቀሱት አቶ ተፈራ ደግፌ ሁለት መጻሕፍት ‹‹A Tripping Stone ›› እና ‹‹Minutes of an Ethiopian Century›› ሲያሳትሙ፣ ማኅበራዊ ጥናት መድረክ ከ16 ዓመት በፊት ባዘጋጀው መድረኩ ላይ በንግግር ያቀረቡትን ግለ ታሪክ ‹‹ተፈራ ደግፌ የባንክ ዕድገት ለአገሪቱ ልማት ያደረገው አስተዋጽኦ›› በሚል ርዕስ በ2000 ዓ.ም. አሳትሟል፡፡
በ89 ዓመታቸው ያረፉት አቶ ተፈራ ሥርዓተ ቀብር በካናዳ ቫንኩቨር መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በማውንቴን ቪው መካነ መቃብር የባለቤታቸው አስከሬን ባረፈበት ቦታ ማረፉን ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ›› በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡ ዘገባው እንዳመለከተው አቶ ተፈራ በአዲስ አበባ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸውን አዲስ አበባ ለሚገኘው የፌስቱላ ሆስፒታል መናዘዛቸው ታውቋል፡፡ አቶ ተፈራ ከካናዳዊት ባለቤታቸው አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጆች አፍርተዋል፡፡
አቶ ተፈራ ከ16 ዓመት በፊት ማኅበራዊ ጥናት መድረክ (ማጥመ) በጋበዛቸው መድረክ ላይ የዘመናቸውን አንድ አንጓ እንዲህ ገልጸውት ነበር፡፡ ‹‹አንዳንዴ ወዳለፈው ዘመን መለስ ብዬ ስመለከት በእኛ የሥራ ዘመን የጐደለው ቆራጥነት ይመስለኛል፡፡ በነበረን ሰፊ የአስተዳደር ሥልጣን በድፍረት ብዙ ሊሠራ ይችል ነበር፡፡ ሲያስፈልግም አስረድተን፣ ጠቀሜታውን አሳውቀን ሽንጣችንን ገትረን ብንከራከር ኖሮ የተሻለ ለውጥ አምጥተን የተሻለ አገር ለተተኪው ትውልድ እናስረክብ ነበር፡፡››
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2003 ዓ.ም. የ60ኛ ዓመት አልማዝ ኢዮቤልዩን ሲያከብር በጊዜው የነበሩት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ገዛኸኝ ይልማ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ አመሠራረት አንስቶ ባንኩ የገጠመውን የዕድገት ውጣ ውረድ አውስተው ያለፉትን የባንኩን ባለሙያዎች አስታውሰው በሚቀጥሉት ቃላት አሞግሰዋቸው ነበር፡፡ ‹‹ታሪክ ከማይረሳቸው ከእነዚህ ቀደምት የባንክ ባለሙያዎች መስዋዕትነትን፣ የዓላማ ጽንዓትን፣ ለአገር አሳቢነትን፣ ተቆርቋሪነትን፣ ታማኝነትን እኛ በአዲሱ ዘመን የምንገኝ ዜጐች ልንማር ይገባናል፡፡››
አቶ ተፈራ በ1991 ዓ.ም. ለአቢሲኒያ ባንክ ምረቃ ተጋብዘው አዲስ አበባ በመጡበት ጊዜ ቃለ መጠይቅ ላደረገላቸው ጦቢያ መጽሔት በመደምደሚያው ላይ ላገራቸው ራዕይና ምኞት እንዲህ ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹እኔ ለኢትዮጵያ የምመኘው ከጦርነት ውጥረትና ከሚያስከትለው ጥፋት አምልጠን በመልማት ላይ እንዳሉት ሌሎች አገሮች ወደ ልማቱና ማኅበራዊ ዕድገት እንድትደርስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ራዕይ ያለው አመራር፣ ተግባብቶ የሚኖር ሕዝብ፣ በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ የሚኮራና አገሩን የሚያስከብር ዜጋ መኖር ወሳኝ ነው፡፡››

No comments:
Post a Comment