Tuesday, March 24, 2015

ሔኖክ መደብር

‹‹የመጋቢት መስቀል የቀረህ እንደሆን
ከብቱም አለቀልህ ሰዎችም ሰው አንሆን››
የበልጉ ዝናም መዘግየት ያሳሰበው ያገሬ ገበሬ ያንገራጎረው
(ሔኖክ መደብር )

Saturday, March 14, 2015

ተፈራ ደግፌ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ (1918 – 2007 ዓ.ም.)

15 March 2015 ተጻፈ በ 


ባንክ በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ‹‹ባንክ ኦፍ አቢሲኒያ›› ተብሎ ከተቋቋመበት በመቀጠል በ1923 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ በማስከተልም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቋቋም በመሪነት ተቀምጠው የነበሩት የውጭ አገር ዜጐች ነበሩ፡፡ ታሪካዊቷ 1953 ዓ.ም. እስከመጣችበት ጊዜ ድረስ፡፡ ‹‹ቀን ሲደርስ አምባ ይፈርስ›› ነውና፡፡
ገንዘብ ለለውጥ ፈር ቀዳጅነት ብለው ከተነሱ ኢትዮጵያውያን መካከል ኢትዮጵያዊውን የመንግሥት ባንክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና ሥራ አስኪያጅነት ለመምራት የበቁት አቶ ተፈራ ደግፌ ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ዘመናዊ መንግሥትነት ታሪክ በፋይናንስ ዘርፍ ሁነኛ ሥፍራ የነበራቸው አቶ ተፈራ ዛሬ በአፀደ ሥጋ የሉም፡፡ ለዓመታት ይኖሩበት በነበረችው ካናዳ ዜና ዕረፍታቸው የተሰማ ሲሆን፣ ሥርዓተ ቀብራቸውም እዚያው ካናዳ ቫንኩቨር ከተማ ተፈጽሟል፡፡ አቶ ተፈራ በኢትዮጵያ ባንኮች ውስጥ የፈጸሙት አገልግሎት ከ1934 እስከ 1968 ዓ.ም. ድረስ ለ34 ዓመታት በዘርፈ ብዙ ሥምሪት የዘለቀ ነበር፡፡
የፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ድል ከተመታ በኋላ የኢትዮጵያ መንግሥት ዳግም ሲቋቋም የባንክና የገንዘብ ሥርጭት ከእንግሊዝ የምሥራቅ አፍሪካው የቅኝ አገዛዝ ጋር አቀላቅሎ ለማስተዳደር፣ በእንግሊዝ በኩል የነበረው ግፊትና ኢትዮጵያ ተነጥላ የራሷን ባንክ ለማቋቋም ስትነሳ ያጋጠመውን ብዙ ችግር ሰብሮ በመውጣት ረገድ በነበረው ጉዞ የአቶ ተፈራ ደግፌ ሁነኛ ሚናም ይጠቀሳል፡፡
አቶ ተፈራ ማኅበራዊ ጥናት መድረክ በአንድ ወቅት ‹‹ተፈራ ደግፌ የባንክ ዕድገት ለአገሪቱ ልማት ያደረገው አስተዋጽኦ›› በሚል ባዘጋጀው ‹‹ከድህነት ወደ ልማት፣ ዕውቀትን ለትውልድ ማስተላለፍ›› መድረክ ላይ ሲናገሩ፣ ‹‹በ1937 ዓ.ም. በአሜሪካ በሚስጥር ተዘጋጅቶ አዲስ የኢትዮጵያ ብር ገንዘብ ታውጆ ወጣ፡፡ በዚህ ዓይነት ነው የኢጣሊያ ሊሬ፣ የምሥራቅ አፍሪካ ሺሊንግ በአዲሱ የኢትዮጵያ ብር የተለወጠው፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የባንክ ሥራው ቀስ በቀስ እየሰመረ የሄደው፤›› ብለው ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የንግዱ ክፍል ቅርንጫፍ በካርቱም (ሱዳን) በ1950 ዓ.ም. ሲከፈት የመጀመሪያው ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተሾሙት አቶ ተፈራ፣ በወቅቱ በየድርጅቱ የውጭ አገር ዜጐች ስለነበሩ ‹‹ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክን ለመምራት ብቁ አይደሉም፤›› የሚለውን አስተሳሰብ በመስበር፣ ከ1937 እስከ 1952 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክን ከመሩት ስድስት የውጭ አገር ዜጐች መንበሩን በመጨበጥ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ሆነዋል፡፡ በእርሳቸው ፋና ወጊነት የተጀመረው መሪነት እስካሁን ዘልቋል፡፡
አቶ ተፈራ ሱዳን ለተከፈተው የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ (በአገሬው ወዳጃዊ አጠራር ‹‹ባንክ ኤል ሐበሺ››) ሥራ አስኪያጅነት በጽሕፈት ሚኒስቴር ማዘዣ ከመሾማቸው በፊት የሲቪል አቪዬሽን ዋና ዳይሬክተር ነበሩ፡፡
አቶ ተፈራ ከአባታቸው አቶ ደግፌ በላይነህ፣ ከእናታቸው ወ/ሮ እርገጫቸው ገብረ ማርያም ሰኔ 8 ቀን 1918 ዓ.ም. የተወለዱት በሸዋ ጠቅላይ ግዛት አንኮበር አውራጃ አንበሴ ቀበሌ ሲሆን፣ ያደጉት ገንዳ ውኃ ተብሎ በሚታወቀው አካባቢ ነው፡፡ ትምህርታቸውን በአሊያንስ ፍራንሴዝ፣ በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤቶች ከተከታተሉ በኋላ በ1938 ዓ.ም. ለከፍተኛ ትምህርት ካናዳ በመሄድ በካልጋሪ አልበርታ ንግድ ኮሌጅ ዲፕሎማ፣ ከዩኒቨርሲቲ ኦፍ ብሪትሽ ኮሎምቢያ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል፡፡ ለሁለት ዓመትም የሕግ ትምህርት ተከታትለዋል፡፡
የአማርኛ፣ የጣሊያንኛ፣ የመስኮብኛ (እሳቸው እንደሚሉት)፣ የፈረንሳይኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተናጋሪ የነበሩት አቶ ተፈራ፣ ከባሕር ማዶ መልስ የሠራተኛነት ጉዟቸው የተጀመረው በኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ መሥሪያ ቤት በጸሐፊነት ደረጃ ሲሆን፣ ቀፕሎም የባንኩ ነገረ ፈጅ ሆነው ነበር፡፡ በ1953 ዓ.ም. የኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ዋና ሥራ አስኪያጅ ለመሆንም በቅተዋል፡፡
 ከ1956 እስከ 1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ከ1966 እስከ 1968 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ በመሆን ማገልገላቸው ራሳቸው የጻፉት ግለ ታሪካቸው ያሳያል፡፡
አብዮቱን ተከትሎ የቀዳማዊ ኃይሌ ሥላሴ ምሥል የነበረበት የኢትዮጵያ ብር ሲለወጥ፣ አቶ ተፈራ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ቦርድ ሊቀመንበርነታቸው የእርሳቸው ፊርማ ያረፈበት ገንዘብ የታተመውና የተሠራጨው በ1969 ዓ.ም. ነበር፡፡ ወዲያው በዚያው ዓመት ደርግ ‹‹ለአብዮቱ እንቅፋት እንዳትሆን›› በማለት ለሰባት ዓመታት አስሯቸው ነበር፡፡
አቶ ተፈራ ከእስር ከተፈቱ በኋላ ቫንኩቨር የሚገኘው የብሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ፋኩልቲ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ የሰጣቸው ሲሆን፣ ጡረታ ከወጡ በኋላ እስከ ሕልፈታቸው ድረስ የኖሩት በካናዳ ነበር፡፡
ከሊቃውንቱ (ከኢንቴለጄንሺያው) መካከል የሚጠቀሱት አቶ ተፈራ ደግፌ ሁለት መጻሕፍት ‹‹A Tripping Stone ›› እና  ‹‹Minutes of an Ethiopian Century›› ሲያሳትሙ፣ ማኅበራዊ ጥናት መድረክ ከ16 ዓመት በፊት ባዘጋጀው መድረኩ ላይ በንግግር ያቀረቡትን ግለ ታሪክ ‹‹ተፈራ ደግፌ የባንክ ዕድገት ለአገሪቱ ልማት ያደረገው አስተዋጽኦ›› በሚል ርዕስ በ2000 ዓ.ም. አሳትሟል፡፡
በ89 ዓመታቸው ያረፉት አቶ ተፈራ ሥርዓተ ቀብር በካናዳ ቫንኩቨር መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. በማውንቴን ቪው መካነ መቃብር የባለቤታቸው አስከሬን ባረፈበት ቦታ ማረፉን ‹‹ኢትዮጵያ ዛሬ›› በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡ ዘገባው እንዳመለከተው አቶ ተፈራ በአዲስ አበባ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸውን አዲስ አበባ ለሚገኘው የፌስቱላ ሆስፒታል መናዘዛቸው ታውቋል፡፡ አቶ ተፈራ ከካናዳዊት ባለቤታቸው አንድ ወንድና አንድ ሴት ልጆች አፍርተዋል፡፡
አቶ ተፈራ ከ16 ዓመት በፊት ማኅበራዊ ጥናት መድረክ (ማጥመ) በጋበዛቸው መድረክ ላይ የዘመናቸውን አንድ አንጓ እንዲህ ገልጸውት ነበር፡፡ ‹‹አንዳንዴ ወዳለፈው ዘመን መለስ ብዬ ስመለከት በእኛ የሥራ ዘመን የጐደለው ቆራጥነት ይመስለኛል፡፡ በነበረን ሰፊ የአስተዳደር ሥልጣን በድፍረት ብዙ ሊሠራ ይችል ነበር፡፡ ሲያስፈልግም አስረድተን፣ ጠቀሜታውን አሳውቀን ሽንጣችንን ገትረን ብንከራከር ኖሮ የተሻለ ለውጥ አምጥተን የተሻለ አገር ለተተኪው ትውልድ እናስረክብ ነበር፡፡››
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ2003 ዓ.ም. የ60ኛ ዓመት አልማዝ ኢዮቤልዩን ሲያከብር በጊዜው የነበሩት የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ገዛኸኝ ይልማ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባንክ አመሠራረት አንስቶ ባንኩ የገጠመውን የዕድገት ውጣ ውረድ አውስተው ያለፉትን የባንኩን ባለሙያዎች አስታውሰው በሚቀጥሉት ቃላት አሞግሰዋቸው ነበር፡፡ ‹‹ታሪክ ከማይረሳቸው ከእነዚህ ቀደምት የባንክ ባለሙያዎች መስዋዕትነትን፣ የዓላማ ጽንዓትን፣ ለአገር አሳቢነትን፣ ተቆርቋሪነትን፣ ታማኝነትን እኛ በአዲሱ ዘመን የምንገኝ ዜጐች ልንማር ይገባናል፡፡››
አቶ ተፈራ በ1991 ዓ.ም. ለአቢሲኒያ ባንክ ምረቃ ተጋብዘው አዲስ አበባ በመጡበት ጊዜ ቃለ መጠይቅ ላደረገላቸው ጦቢያ መጽሔት በመደምደሚያው ላይ ላገራቸው ራዕይና ምኞት እንዲህ ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹እኔ ለኢትዮጵያ የምመኘው ከጦርነት ውጥረትና ከሚያስከትለው ጥፋት አምልጠን በመልማት ላይ እንዳሉት ሌሎች አገሮች ወደ ልማቱና ማኅበራዊ ዕድገት እንድትደርስ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ራዕይ ያለው አመራር፣ ተግባብቶ የሚኖር ሕዝብ፣ በኢትዮጵያዊነቱ አምኖ የሚኮራና አገሩን የሚያስከብር ዜጋ መኖር ወሳኝ ነው፡፡››
 
 

በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደረሰ ሰደድ እሳት የአንድ ባለሙያ ሕይወት አጠፋ

ሪፖርተር 15 March 2015 ተጻፈ በ 

በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ የደረሰ ሰደድ እሳት የአንድ ባለሙያ ሕይወት አጠፋ

የደቡብ አፍሪካ ባለሙያዎች ድጋፍ ለመስጠት አዲስ አበባ ገቡ
በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ መሰንበቻውን የደረሰውን የሰደድ እሳት አደጋ ለማጥፋት ተንቀሳቅሰው ከነበሩት ባለሙያዎች መካከል በአንዱ ላይ የሞት፣ በሌሎቹ ሁለት ባለሙያዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ ደረሰ፡፡
የደረሰውን የእሳት አደጋ ለማጥፋት ባለሙያዎችን የያዘች የደቡብ አፍሪካ እሳት አደጋ ተከላካይ አውሮፕላን መጋቢት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገብታለች፡፡
ከሳምንት በፊት በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አካባቢ የተነሳውን እሳት ለማጥፋት መጋቢት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ባለሙያዎች መካከል አንዱ የሆነው አቶ ቢንያም አድማሱ ሕይወቱን ሲያጣ፣ ሌሎች ሁለት ባለሙያዎች የመለብለብ አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን የሕዝብ ግንኙነትና የመረጃ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ዘሪሁን ዘውዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሰደድ እሳቱ ከአጠቃላዩ የፓርኩ ይዞታ አምስት ከመቶ በሚሆነው ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ በአካባቢው የተፈጠረውን ሰደድ እሳት ለማጥፋት የፓርኩን ዋርዶች ጨምሮ አጋር ድርጅቶችና ማኅበረሰቡ ባደረጉት ርብርብ በሁለት ወረዳዎች የተነሳውን እሳት ቢቆጣጠሩትም፣ ጎባ ሳይት በተባለው አካባቢ የተነሳውን ለማጥፋት በሚጥሩበት ወቅት የተነሳው ንፋስ እሳቱን በማባባሱ፣ በባለሙያዎቹ ላይ ጉዳት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡
በፓርኩ አካባቢ የደረሰው እሳት በአመዛኙ ቢጠፋም በጎባ በኩል ባለው ቁጥቋጦና ቀርከሃ ላይ የተከሰተው ግን ሙሉ ለሙሉ እንዳልጠፋ የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፣ እሳቱ ወደ ፓርኩ አለመድረሱን ግን አውስተዋል፡፡
እሳቱን ለማጥፋት እየተደረገ ያለውን ርብርብ ለማገዝ የደቡብ አፍሪካ ባለሙያዎች ከናይሮቢ የእሳት አደጋ መከላከያ አውሮፕላን ይዘው ባለፈው ዓርብ አዲስ አበባ መድረሳቸውን፣ ኮሚቴውን ወደ እሳቱ ቦታ ከማመላለስና ሙያዊ ድጋፍ ከመስጠት በተጨማሪ የእሳት ማጥፋት ሥልጠና እንደሚሰጡና ሥራቸውንም ወደ ፓርኩ መጋቢት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በመሄድ እንደሚጀምሩ ታውቋል፡፡
ፓርኩ ከ95 በመቶ በላይ ደህና መሆኑ፣ ከዱር እንስሳቱም ብዙም የተጎዱ አለመኖራቸውና እሳቱ የደረሰበት ቦታ ላይ የነበሩ እንስሳት መሰደዳቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹ብዙ የተጎዱ የሉም፤ እሳቱ ሲመጣ ይሰደዳሉ ሳሩ ሲበቅል ተመልሰው ይመጣሉ፤›› ብለዋል፡፡
 የአደጋው መንስዔ እየተጣራ መሆኑንና ያለው ጥርጣሬ ከፓርኩ ውጪ የሚገኝ አካባቢን ለከብት ግጦሽ ለመጠቀም በተለኮሰ እሳት በመሆኑ፣ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክተዋል፡፡
በአደጋው ሕይወቱ ያለፈው የወጣቱ ባለሙያ ቢንያም አድማሱ ሥርዓተ ቀብር በባሌ ዶዶላ ከተማ ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን መጋቢት 3 ቀን 2007 ዓ.ም. መፈጸሙ ታውቋል፡፡
ከሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በሥነ ጽሑፍ  ያገኘውና በቱሪዝም ዘርፍ ልዩ ልዩ ሥልጠናዎችን የወሰደው የ31 ዓመቱ አቶ ቢንያም፣ ከአካባቢ ጥበቃና ኢኮቱሪዝም ጋር የተያያዘ ሥራ በሚሠራው ፍራንክፈርት ዙኦሎጂካል ሶሳይቲ ባልደረባና የቱሪዝም ልማት አማካሪ ሲሆን፣ ከተቋሙ ጋር በመሆን በሰሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ በአቡነ ዮሴፍ የማኅበረሰብ ጥብቅ ስፍራ፣ በመንዝ ጓሳ ጥብቅ ስፍራ፣ በአርሲ አካባቢዎችና በባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አያሌ ሥራዎችን ማከናወኑ ይነገርለታል፡፡ ቀደም ሲል በኢትዮጵያ ዘላቂ ቱሪዝም ትብብር (ኢስታ) የቱሪዝም ልማት ቴክኒክ አማካሪ ሆኖ ሠርቷል፡፡
ከአዲስ አበባ 400 ኪሎ ሜትር ርቆ በደቡብ ምሥራቅ የአገሪቱ ክፍል የሚገኘውና በ1962 ዓ.ም. የተቋቋመው የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ፣ ጠቅላላ ስፋቱ ከ2,200 ካሬ ኪሎ ሜትር  በላይ ሲሆን፣ ከባሕር ጠለል ከ1,500 ጫማ እስከ 4,377 ጫማ የሚለካ ከፍታ አለው፡፡  የደጋ፣ የወይና ደጋና የቆላ ሥነ ምኅዳሮችና ትልልቅ የዕፀዋት (ቨጂቴሺን) ዞኖች አሉት፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ ከ1,600 በላይ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ዓይነት ዕፀዋት፣ 78 ዓይነት አጥቢ የዱር እንስሳትና 200 የሚጠጉ አዕዋፋት በፓርኩ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል 32 ዓይነት ዕፀዋት፣ 31 ብርቅዬና ድንቅዬ  የዱር እንስሳትና  ስድስት  ዕፀዋት በብሔራዊ ፓርኩ ካልሆነ በስተቀር በሌላው ዓለም ፈጽሞ አይገኙም፡፡
ከዚህም ባሻገር ለሳይንስና ኢኮሎጂ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው በደረታቸው የሚሳቡ ልዩ ልዩ እንስሳትና መንቆረረቶችን ፓርኩ አቅፎ ሲይዝ፣ ቡና እና ለባህል መድኃኒትነት የሚውሉ 40 በመቶ የአገሪቱ ዕፀዋትም ይገኙበታል፡፡
ብሔራዊ ፓርኩ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ ከመካተቱም በተጨማሪ፣ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ብዝኃ ሕይወት ያለው በመሆኑ በዓለም 34ኛው በጣም ጥበቃ የሚያስፈልገው የብዝኃ ሕይወት (ሴንሲቲቭ ባዮዳይቨርሲቲ) አካባቢ መሆኑም ይታወሳል፡፡ በዓለም አቀፍ የወፎች ድርጅትም የአፍሪካ አራተኛው የአዕዋፋት መናኸሪያ (በርዲንግ ሳይት) ተብሎ ተመዝግቧል፡፡

መጋቢት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. 4ኛ እሑድ ከፋሲካ በፊት እና የዓቢይ ጾም 4ኛ እሑድ፡ እኩለ ጾም፡ እሑድ ዘደብረ ዘይት

ዛሬ መጋቢት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. 4ኛ እሑድ ከፋሲካ በፊት እና የዓቢይ ጾም 4ኛ እሑድ፡ እኩለ ጾም፡ እሑድ ዘደብረ ዘይት፡፡

Saturday, March 7, 2015

ዛሬ የካቲት 29 ቀን2007 ከትንሣኤ በፊት 5ኛ እሑድ እና የዐቢይ ጾም 3ኛ እሑድ


የዐቢይ ጾም 8ቱ እሑዶች (ሰንበታተ ክርስቲያን) መጠርያ እነሆ፡፡
የካቲት 8 :  ዘወረደ እሑድ /ቅበላ፤ የካቲት 15፡ ዘቅድስት እሑድ፤ የካቲት 22፡ ዘምኩራብ፤  የካቲት 29 ዘመፃጉዕ፤ መጋቢት 6፡ ዘደብረ ዘይት፤  መጋቢት 13፡ ዘገብረ ኄር፤  መጋቢት 20፡ ዘኒቆዲሞስ፤ መጋቢት 27፡ ዘሆሣዕና፤ ሚያዝያ 4፡ ዘትንሣኤ እሑድ፡፡