Saturday, February 14, 2015

የካቲት 8 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበት በዓል


በየካቲት 8 ቀን የምናከብረው በዓል ኤታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሙሴን ሕግ ይፈጽም ዘንድ ከከበረ ልደቱ ከአርባ ቀኖች በኋላ ወደ ቤተ መቅደስ የገባበትን ዕለት ነው፡፡

ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ እንደጻፈው፣ ለዚህ ምሥጢር አገልጋይ የሆነ ጻድቁ ዮሴፍና ጌታን የወለደችው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እርሱን ይዘው ሕግን ይፈጽሙ ዘንድ መሥዋዕትንም ሊአቀርቡ መጡ፡፡ ጻድቅ ሰው   ካህኑ ስምዖንም ሕፃኑን ተቀብሎ አቀፈው፡፡ እግዚአብሔርንም እየባረከ እንዲህ አለ፡- ‹‹ጌታ ሆይ፥ አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም  ታሰናብተዋለህ፤  ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው። ›› (ሉቃስ 2፡29-32)
ስምዖን ብሉይ ኪዳንን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ ከተረጐሙት 70 ሊቃናት አንዱ ነበረ፡፡ ይህም የሆነው አዳም በተፈጠረ በ5204 ዓመተ ዓለም፣ ከክርስቶስ ልደት 296 ዓመት ላይ በበጥሊሞስ ዘመነ መንግሥት ሲሆን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ወደ ኢየሩሳሌም ተላከ፡፡ ከአይሁድ መምህራንና ሊቃውንት መካከል 70 ውን በማስመጣት ብሉይ ኪዳንን ከዕብራይስጥ ወደ ግሪክ እንዲተረጉሙ አዘዛቸው፡፡
ዳግመኛም ሁለት ሁለት አያደረገ በተለያየ ቦታ ሆነው በሚተረጉሙበት ጊዜ በአንድ ትርጉም ላይ ስምምነት ላይ አልደረሱም ፡፡ ስምዖን ከተርጓሚዎቹ አንዱ ነበር፡፡ ስምዖን በኢሳይያስ 7፡14 የተጻፈውን ‹‹ እነሆ ድንግል ትፀንሳለች፤ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፤ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች፤›› ሲመለከት፣ ‹‹ ድንግል ትፀንሳለች›› የሚለውን ቃል ለመጻፍ ፈራና ‹‹ወጣት ሴት› › ብሎ ለመተርጎም ፈለገ፡፡  ይህ አንዴት ይሆናል ብሎ ንጉሡ እንደሚዘብትበትና ቃሉንም እንደማይቀበለው አስቧልና ተጨነቀ፡፡  የእግዚአብሔርም መልአክ በራዕይ ተገልጦ  የተጠራጠርከውን ከድንግል የሚወለደውን ጌታ ክርስቶስ እስከምታየውና እሰከምትታቀፈው  ሞትን አትቀምስም አለው፡፡
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በታኅሣሥ 29 ቀን 5501 ዓመተ ዓለም እሰከተወለደና የካቲት 8 ቀን ወደ ቤተ መቅደስ እሰከ አስገቡት ድረስ ስምዖን 300 ዓመት ኖረ፡፡ ሕፃኑን ጌታችንንም በታቀፈው ጊዜ ታውረው የነበሩ ዓይኖቹ ተገለጡ፤ ሁለመናውም ሐዲስ ሆነ፡፡ መንፈስ ቅዱስም  ‹‹የምትጠብቀው የነበረ  ሕፃንይህ ነው፤›› ብሎ ነግሮታልና እግዚአብሔርን አመሰገነው፡፡ እንዲህም አለ፡-   አሁን እንደ ቃልህ ባሪያህን በሰላም  ታሰናብተዋለህ፤  ዓይኖቼ በሰዎች ሁሉ ፊት ያዘጋጀኸውን ማዳንህን አይተዋልና፤ ይህም ለአሕዛብ ሁሉን የሚገልጥ ብርሃን ለሕዝብህም ለእስራኤል ክብር ነው። ›› (ሉቃስ 2፡29-32)
የጻድቁ ሰው ጸሎት ከእኛ ጋራ ይሁን፣ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከቸር አባቱና ይቅር ባይ ከሆነ ከመንፈስ  ቅዱስ ጋራ ክብር ምስጋና ይሁን፤ ለዘላለሙ፡፡ አሜን፡፡
-      የየካቲት ስምንት ስንክሳር
(ሔኖክ መደብር )

No comments:

Post a Comment