Sunday, February 1, 2015

ጾመ ነነዌ (ጥር 25-27 ቀን 2007/ 2015 ዓመተ ምሕረት)



በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ አምልኮ  (ሊጡርጊያ) መሠረት ዛሬ ጥር 25 ቀን 2007 ዓመተ ሥጋዌ በፀሐይ አቈጣጠር፣ 2015 ዓመተ ምሕረት በፀሐይና በጨረቃ ጥምር መሠረት ‹‹ጾመ ነነዌ›› ተብላ የምትታወቀው የሦስት ቀኖች  ጾም ተጀምራለች፡፡ የነነዌ ጾም ሦስት ቀን ብቻ ነው፡፡ እነርሱም ሰኞ፣ማክሰኞና ረቡዕ ናቸው፡፡ ጾሙ የሚፈታበት ቀን ኀሙስ ነው፡፡

መጻሕፍት እንደሚነግሩን የነነዌ ሰዎች  [ነነዌ በአሁን ጊዜ በኢራቅ ውስጥ የምትገኝ ከተማ ናት] በነቢዩ በዮናስ ትምህርት  (ትንቢተ ዮናስ 3፡ 1-10) ንስሐ ገብተው፣ ሦስት ቀን ጾመው ከታዘዘው መቅሰፍት ስለዳኑ ንስሐ ለሚገቡ ምእመናን (ተነሳሕያን) ሁሉ አብነት (ምሳሌ) ሆነዋል፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የጥንት ቤተ ክርስቲያን በወሰነችው ቀኖና  መሠረት በኃጢአት ምክንያት ከሚታዘዘው መቅሠፍት ለመዳን ምእመናን እንደ  ነነዌ ሰዎች ሦስቱን ቀን በየዓመቱ እንዲጾሙ ታዝዛለች፡፡
ጾመ ነነዌ በሊጡርጊያ ዓመት (LItrugical year ) ውስጥ የተካተተችው በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው፡፡ በዚያው ዐረፍተ ዘመን ከሶርያና ከአካባቢው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ዘጠኙ ቅዱሳን (ተሰአቱ ቅዱሳን) እነ አቡነ አረጋዊ፣ አቡነ ገሪማ፣ ወዘተ አማካይነት  ጾሙ  በኢትዮጵያ መጀመሩ ይታመናል፡፡ በእስክንድርያ ትውፊት ውስጥ የገባውም በእስክንድርያ 62ኛው ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት /ፖፕ (975-979 ዓ.ም.) ቅዱስ አብርሃም ሶርያዊ አማካይነት ነው፡፡
ጾመ ንስሐ፣  የንስሐ ጾም በመባል የሚታወቀው ጾመ ነነዌ ከፋሲካ (ትንሣኤ) 10 ሳምንት በፊት [ዘንድሮ ሚያዝያ 4 ይውላል] የሚውል፣ ከዘመነ አስተርእዮ (ጥምቀት) የመጨረሻው እሑድ  [ዘንድሮ ጥር 24] በኋላ የሚመጣ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ዐቢይ ጾም ከሚጀመርበት 14 ቀናት [የካቲት 9 ይያዛል] በፊት የሚጾም ነው፡፡
በዘመነ ሐዲስ (በክርስትና) ለተሠሩት ከፋሲካ ጋር የሚዘዋወሩት አጽዋማትና በዓላት (ዐቢይ ጾም፣ ደብረ ዘይት፣ ሆሳዕና፣ ስቅለት፣ ረክበ ካህናት፣ ዕርገት፣ ጰራቅሊጦስ፣ ጾመ ሐዋርያት፣ ጾመ ድኅነት) መሠረታቸው በአንድ በኩል የነነዌ ቀን የሚውልበት ነው፡፡ የነነዌ ሰኞ ሁሌም የምትውለው በጥር 17 ቀን እና በየካቲት 21 መካከል ነው፡፡ በሌላ በኩልም የሁሉም ተዘዋዋሪ አጽዋማትና በዓላት መሠረት ፋሲካ (ትንሣኤ) ይሆናል፡፡
የዕለቱ ጥቅስ
‹‹የመርከቡም አለቃ ወደ እርሱ  [ዮናስ] ቀርቦ፤ ምነው ተኝተሃል?  እንዳንጠፋ እግዚአብሔር ያስበን እንደሆነ ተነሥተህ አምላክህን ጥራ አለው›› (ትንቢተ ዮናስ 1፡6)
በዚህ የጾም ጊዜ በቤተ ክርስቲያን የሚነበቡ ቅዱሳት መጻሕፍትም የጾምን ጥቅምና በረከትንም የሚያስገነዝቡ ናቸው፡፡ ይኸውም እንደሚከተለው ነው፡፡ ቀጥሎ የሚጻፉት ንባባት የተገኙት በአለቃ ያሬድ ፈንታ አራቱን ወቅቶቸ መሠረት አድርጎ  ከተዘጋጀው ‹‹መጽሐፈ ግጻዌ ሐዲስ›› ነው፡፡
ሰኞ (ጥር 25፣2007 ) ንባባት፣ ምዕራፍና ቁጥር
(1)    ዮናስ 1፡1-16  2) ሮሜ 2፡1-16  (3) ያዕቆብ 5፡ 1-11  (4) ሐዋርያት ሥራ 2፡ 37-42   
(5)  መዝሙር 2፡ 12  (ምስባክ)
‹‹ተግሣጹን ተቀበሉ ጌታ እንዳይቆጣ  እናንተም በመንገድ እንዳትጠፉ፤
ቁጣው ፈጥና ትነድዳለችና፡፡ በእርሱ የታመኑ ሁሉ የተመሰገኑ ናቸው››
(6) ማቴዎስ 12፡38-42

ምንጭ፡-
‹‹መጽሐፍ ቅዱስ የብሉይ እና የሐዲስ ኪዳናት›› (1953 ዓ.ም.)
‹‹መጽሐፈ ግጻዌ ሐዲስ ዘተሰናአወ በአርባዕቱ ክፍላተ አዝማን›› (1997) ዘአለቃ ያሬድ ፈንታ፡፡
“ The Litrugical Year of The Ethiopian church” (2001 AD) Abba emmanuel fritsch.
(ሔኖክ መደብር)


No comments:

Post a Comment