Friday, December 19, 2014

ሴቶች የነገሡበት


ጥንታዊቷ የመቐለ ከተማ በነሐሴ መንፈቅ፣ ልዩ ድባብ የሚያለብሳት ከተሜውም ሆነ ከዚያም ውጪ ያለውን ኅብረተሰብ ቀልብ የምትገዛበት አጋጣሚን ታገኛለች፡፡ ዓመት ሄዶ ዓመት ሲመጣ 12ኛው ወር ላይ ከምትመጣው ‹‹አሸንዳ›› ጋር ትገናኛለች፡፡
ልጃገረዶችም በልዕልና የሚታዩበት፣ በነፃነት ነግሠው የሚጫወቱበት የአሸንዳ በዓል፡፡ 
ከሕፃን እስከ አዋቂ የበዓሉ መገለጫ በሆኑ አልባሳትና ማጋጊያጫዎች የሚታዩት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ 
ከቀደምት የሥነ ሕንፃ ጥበብ (እነ ሕድሞ፣ አፄ ዮሐንሰ ቤተ መንግሥት ወዘተ.) እስከ ዘመናዊዎቹ ሕንፃዎች የሚታዩባት መቐለ ከተማ ከነሐሴ 15 ቀን 2006 .. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በዘለቀው በዓልም የሸሩባዎች መዲና ያሰኛትን ገጽታም ተላብሳ ነበር፡፡ 
የፀጉር አሠራሩ ከአልባሶ እስከ ግልብጭ፣ ከጋመ እስከ ድርብ፣ ከደቃቅ እስከ ጉልህ ከሕፃን እስከ አዋቂ ተቆናጅተው የታዩበትም ጭምር ነው፡፡ ከቱባው ባህል ልብስ አንሥቶ ከዘመናዊው ስፌት ከተገኙት ጃርሲ፣ ሽፎን ቀሚስ ጋር ተውበው የሚታዩበትም ነው፡፡
ጌጣጌጡም ልዩ ልዩ ዓይነት ነው፡፡ አንገት ላይ ከሚንጠለጠለው ሕንቆ፣ እግር ላይ እስከሚጠለቀው አልቦ በልብስም በአካልም ላይ ይታያል፡፡ ኮንጎ ጫማም ቦታዋን ይዛለች፡፡ 
የበዓሉ ኩነት ለከተማው ባዳ፣ ለአካባቢው እንግዳ ለሆነው ብቻ ሳይሆን በዚያው ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ ማስደነቁ፣ ማስደመሙ ቀልብ መግዛቱ የማይሳት ነው፡፡ 
‹‹የዓይኖቿ ውበት ያንገቷ ሙስና (ውበት ማለት ነው)
ሮብ ያስገድፋል እንኳን ሐሙስና›› የሚለውን መንቶ ግጥም የሚያስታውሰው ቆነጃጅቱ ዓይናቸው ላይ የተኳሉት ኩል በቤት ተወቅጦ የተዘጋጀ ነው፡፡ 
የአሸንዳ መንፈስ፣ በፀጉር አሠራርና በአልባሳት፣ በመዋቢያ ቁሶችና በመጋጋጪያዎች ብቻ አይደለም የሚገለጠው፣ ርሱን የሚያገዝፉ የሚያጎሉ የተለያዩ ዘፈኖች ይገኙበታል፡፡ 

ነሐሴ 16 ቀን ከሚከበረው የፍልሰታ ለማርያም በዓል ጋር የተያያዘው አሸንዳን ማክበር የተጀመረው በዋዜማው ነው፡፡ ነሐሴ 15 ከሰዓት በኋላ በመቐለ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች በቀረበ ትዕይንት በዓሉ መድረሱ ተበስሯል፡፡ ከተለያዩ የትግራይ ዞኖች የመጡትን የአሸንዳ ልጃገረዶች፣ 
‹‹መፀት መፀት
     ኣሸንዳ ዕምባባ መፀት››
(መጣች መጣች፣ አሸንዳ አበባ መጣች) እያሉ ከታላቁ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት አደባባይ ተነሥተው በፒያሳ ሐውዜን አደባባይ በኩል በዋና ዋና ጎዳናዎች የተጓዙትና መቐለ ስታዲየም ‹‹ባሎኒ›› የደረሱት በክልሉ የፖሊስ ማርሽ ባንድ በመታጀብ ነበር፡፡ 
እንደክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ከበደ አማረ በላይ አገላለጽ ከሆነ፣ አሸንዳ ከትግራይ ሰባት ዞኖች አምስቱ በድምቀት እንደሚያከብሩትና  ስድስተኛው ዞን ሽሬ በተመሳሳይ መልኩ በዓሉን ለማክበር እናቶች ልጆቻቸውን ለማሠልጠን እየተጉ ናቸው፡፡ 
አሸንዳ በባሎኒ (ስታዲየም) ውስጥ ከነበረው የመክፈቻ አከባበሩ ይልቅ በዕለቱ በከተማዋ እንብርት ሮማናት አደባባይ (የአፄ ዮሐንስ 4 ሐውልት ሊተከልበት የታሰበበት ቦታ) 10 ሰዓት እስከ ምሽት የዘለቀው ጭፈራ ገጽታ ልዩ ነበር፡፡ 
ከስድስት አቅጣጫዎች ወደ ሮማናት አደባባይ በቡድን በቡድን ሆነው ከበሮዋቸውን እየመቱ ክብ ሠርተው እንደራያ፣ ተምቤን፣ እንደርታ ወዘተ ባህል ሲጫወቱ ላየ ቀልብ የሳቡለት ሆነዋል፡፡ ወንዶችም በጭፈራው አልተለይዋቸውም፡፡ 
አበበች ብርሃኑ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ፋኩልቲ 3 ዓመት ተማሪ ነች፡፡ በሌሎች ቡድኖች ውስጥ የሚታዩት ሴቶች እንደለበሱት በኅብረ ቀለማት በታጀበው ጀርሲና ዲስካ ሳይሆን እንደርሷ አገላጽ፣ የራያ ባህላዊ አለባበስና የአሸንዳ መገለጫ የሆነው ሹፎን ነው፡፡ በአበበች ቡድን ውስጥ ሆነው ይጫወቱ የነበሩት በሙሉ የመጡትም ከራያ (ደቡባዊ ትግራይ) ነው፡፡
ከለበሰችው ቀሚስ በላይ የደረበችው ጉፍታ ሙስሊሞች ፀጉር ለመሸፈን የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ጌጣ ጌጦችም አንዱም አልቀረባትም፡፡ ማይጨው ተወልዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በጥላሁን ግዛውና ማጂክ ካርፔት ትምህርት ቤቶች ያጠናቀቀችው አበበች፣ ሞዴልና የዘንድሮ ወይዘሪት መቐለ ዩኒቨርሲቲ ስትሆን፣ በቴሌቪዥን ድራማ ‹‹ጎጆ›› በተዋናይነት ሠርታለች፤ በአሸንዳውም መሪዋ እሷ ናት፡፡ 

በክረምት ወቅት ከሚበቅለው የአሸንዳ ተክል ስሙን የወረሰውና በአብዛኛው ትግራይ ልጃገረዶች አሸርጠው የሚጫወቱበት የአሸንዳ በዓል አከባበር በዋናነት የትግራይ ሴቶች በዕድሜ ደረጃቸው ተቧድነው የሚያከብሩት ነው፡፡ ከትግራይ ከሚዋሰኑት ጋርም ባህላዊ መወራረስ ስላለ በሰሜን ወሎ ቆቦ (ሶለል ይባላል) በዋግ ህምራ ሰቆጣ (ሻደይ) በላስታ ላሊበላ (አሸንድዬ) በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ኤርትራ ጭምር ይከበራል፡፡ 

ልዩ ልዩ ስያሜዎች  
በዓሉ በመቐለ፣ በእንደርታ፣ በተምቤን፣ በራያ በተመሳሳይ ‹‹አሸንዳ›› ሲባል፣ በዓዲግራት፣ በውቕሮ ‹‹ማርያ›› ይሰኛል፡፡ ይህም በኦርቶዶክሳውያኑ ምዕመናን ከሁለት ሳምንት ጾም በኋላ ከሚያከብሩት ከቅድስት ድንግል ማርያም ስም ጋር የተያያዘ ነው፡፡ በዓጋመ ‹‹ዋዒምቦ›› የሚል ስም ጥሪ ሲኖረው በአክሱምና በዓድዋም ‹‹ዓይኒ ዋሪ›› ይባላል፡፡ በተለይ ዓይኒ ዋሪ ከነሐሴ 24 (ተክለሃይማኖት) ዋዜማ ጀምሮ እስከ መስከረም 17 (መስቀል) ድረስ እየተከበረ ይዘልቃል፡፡
አሸንዳ ሙስሊሞችን ያሳትፋል፡፡ በዓቢ ኣዲ (ተምቤን) ከተማ ማይለሚን ከክርስቲያኖች ጋር ስትጫወት ያገኘናት ሙስሊሟ ሶፊያ መሐመድ ኑር፣ ‹‹ወላሂ አሸንዳ በጣም ቆንጆ ነው፤ እኛ የምንለየው በሥጋ መብል እንጂ ሁሉ ባህላችን አንድ ነው፡፡ አብረን እየዞርን እንጨፍራለን፤›› ብላለች፡፡ በባህላዊ አለባበስ የአሸንዳ መለያ የሆኑ ጌጣ ጌጦች ድኮት፣ ዕንቁ፣ ማዕጠቆ፣ ሙፀ (መደርቢያ) አድርጋ ጃርሲ ለብሳ ጋማ ዓረብ (ሹሩባ) ተሠርታ ነው በዓሉን ስታደምቅ የነበረው፡፡ 
‹‹ዝለሊየ ዘለሊየ ቆልዓ ተምቤን
ዝለሊየ ዝለሊየ ቆልዓ ተምቤን››
(የተምቤን ልጅ ዝለዪ ዝለዪ እያሉ በአውርስ የአጨፋፈር ስልት በዓሉን አድምቀውታል፡፡
አሸንዳ ሴቶች ነፃነታቸውን የሚያውጁበት የሚነግሡበት፣ ጥብቅ የሆኑ ወላጆችና ባሎች ልጆቻቸውንና ሚስቶቻቸውን በበዓሉ እንዲታተደሙ የሚፈቅዱበት ዕለት እንደሆነ በሮማናት አደባባይ ያገኘናት ዕንቁባሕሪ ጥላሁን አውግታናለች፡፡
‹‹ኣይኾንን እንተበላ እነኺየ
ይኾን በሊየን በዓል ኺየ››
(አይሆንም ካሉሽ እናትሽ
ይሆናል በይ ራስሽ)
የዕንቁባሕሪ አስተያየት በፀጋይ ሓድሽ ጽሑፍም ተንፀባርቋል፡፡ ሴቶች ነፃነታቸውን የሚያውጁበት ብቻ ሳይሆን፣ ነፃነታቸውን በተሟላ መልኩ እንዲሰፋ የሚያግዝ ነው፡፡ በያዛቸው ቁም ነገሮችም እንደ ባሕር ነው፡፡ ብዙዎች የዕደ ጥበብ ውጤቶች የሚቀርቡበት፣ ለትምህርት ዕድገትና ለፈጠራ ጽሑፍ የሚሆን ሀብት የተከማቸበት፣ ለቱሪስት መስህብነትም የሚውል ነው፡፡ 
‹‹አሸንዳ ከወላጆቻችን የወረስነው ባህል ነው›› የሚሉት በመቐለ ከተማ ግዙፍና ዘመናዊ ሆቴል (ባለአምስት ኮከብ) የመሠረቱት የፕላኔት ሆቴል ባለቤት አቶ ይርዳው መኰንን ናቸው፡፡
በዓሉ በዓለም ባይታወቅም ትልቅ ፌስቲቫል ነው፡፡ ‹‹ፈረንጆች ሳይቀሩ ባህላዊ ልብሱን ለብሰው ጫማው ተጫምተው የሚታዩበት ነው፤›› የሚሉት አቶ ይርዳው፣ በዓሉን ከመንግሥትም ከኅብረተሰቡም ጋር በመተባበር ማስፋት አለብን ይላሉ፡፡ አክለውም ተናገሩ፡፡ ‹‹አሸንዳ አንደኛ የገቢ ምንጭ ነው፡፡ ለዚህ በዓል ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ታዳሚ ሲመጣ ብዙ ወጪ ስለሚያወጣ፣ ሕዝቡም ይንቀሳቀሳል፡፡ የመንግሥትም ታክስ ያድጋል፡፡››
በዓሉን በተለይ በቱሪስት መስህብነት ለማዋል በቅድሚያ የማስፋፋት ሥራ መሠራት እንዳለበት የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ ወልደሚካኤል የትግራይ ባህል ማኅበር ዋና ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ከቱሪስት መስህብነት ባለፈም አከታትሎም በዓለም ረቂቅ ባህላዊ ቅርሶች (ኢንታንጀብል ካልቸራል ሄሪቴጅ) መዝገብ ውስጥ እንዲገባ ጥረት መደረግ እንዳለበት ያምናሉ፡፡ በተለይ በዓለም ደረጃ ታዋቂ ፌስቲቫል ከሆነ ብዙ ጎብኚዎችን ለመሳብ ያስችላል፡፡ 
እንደ አቶ ብርሃኑ አገላለጽ፣ የአሸንዳ አከባበር መነሻው አክሱም አካባቢ ነው፡፡ ምክንያቱም ከክርስትና ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው፡፡ የኦርቶዶክስ ክርስትና መስፋፋት የጀመረውም 3ኛውና 4ኛው ክፍለ ዘመን በአክሱም ነው፡፡ አሸንዳውም ከአክሱም ተነሥቶ ወደ ኤርትራና ወደ ደቡብ እስከ ላስታና ሰቆጣ ዋግ ድረስ ሊሄድ ችሏል፡፡ 
ከዘመነ ዘመናት ተነሥቶ እስከ ዘውዳዊው ሥርዓት ፍጻሜ (1967 ..) ድረስ በተለይ በትግራይ ይከበር የነበረው አሸንዳ ዳግም ማንሰራራት የጀመረው 1983 .. ወዲህ ነው፡፡ 
አሸንዳ፣ የትግራይ ከተሞች እምብርቷን መቐለን ጨምሮ ጌጥ መሆን የጀመረው 1995 .. በኋላ ነው፡፡ እንደ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ከበደ አማረ በላይ አገላለጽ፣ ትውፊቱ መገጫገጭ ቢያጋጥመውም ባህሉ ግን ተጠብቋል፡፡ በአሁን ጊዜ ሕዝባዊ መሠረት ይዟል፡፡ በአገር ውስጥ የማስተዋወቅ ሥራ፣ የገቢ ማስገኛ ማድረግ ይገባል፡፡ የልብስ ዓይነቱ ብዙነት የፀጉር አሠራሩ ሰፊነት ብዙዎችን ተጠቃሚ አድርጓል፡፡ ባህላዊ ትስስርን የፈጠረው አሸንዳ መስህብ ሆኖ እንዲቀጥል በአገር ውስጥ ማስረፅ የመጀመሪያ ትኩረት ነው፤ እንደ አቶ ከበደ አገላለጽ፡፡
‹‹አሸንዳ ናይ ዓሚ
ናይ ዓሚ›› 
ተጋነና ሎሚ›› (አሸንዳ የዓምናዬ፣ የዓምናዬ ተገናኘን ዘንድሮ)
ብለው ማክበር የጀመሩትን አሸንዳ፣ በመቐለ ከተማ ከሦስት ቀናት በኋላ ሲያጠናቅቁ ባጋጣሚው ባረፍንበት ፕላኔት ሆቴል ደጃፍ ላይ ያገኘናቸው የአሸንዳ ልጆች ከበውን ሲጫወቱ፣ ‹‹ከደት ከደት ኣሸንዳ›› (አሸንዳ ሄደች ለከርሞ ያገናኘን) በማለትም ምኞታቸውን ገልጸውልናል፡፡ ሸልማቱንም ስላልነፈግናቸውም ‹‹ፈሰሰ ከም ማይ ነሓሰ›› (እንደ ነሐሴ ውኃ ፈሰሰ) በማለትም አወደሱን፡፡  ለከርሞም እንዲያደርሰንም ተመኘን፡፡  
 ምንጭ- ሪፖርተር (31 August 2014  )

No comments:

Post a Comment