Saturday, December 27, 2014

‹‹ሰው ያልፋል ታሪክ ግን ይተርፋል››ከ12 ዓመት በፊት  ታኅሣሥ ወር በባተ በ29ኛው ዕለት በጀርመን ሙኒክ ከተማ ያረፉት ታላቁ የታሪክና የቲኦሎጊያ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ  ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ (1921- 1995)፣ ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  የመታሰቢያ ዝግጅት ሲደረግላቸው አንድ አባት ‹‹ሰው ያልፋል ታሪክ ግን ይተርፋል›› ብለው እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ለዚች ትውስታዬ መነሻ የሆነኝ On this day late us remember Prof Sergew Hable Selassie (1929-2003)  በሚል መንደርደርያ በስንክሳራዊ ያጻጻፍ መነሻ አበበ ሐ. ወይን  በፌስቡክ ገጻቸው የጻፉት ዝክረ ሥርግው ነው፡፡

ነፍስ ኄር (The late) ፕሮፌሰር ሥርግው በርግጥም ታሪክን አትርፈውልናል፡፡ ከአዲስ አበባ ቅድስት ልደታ ማርያም ደብር የተጀመረው የትምህርት ማዕዳቸው በቅድስት ሥላሴ ትምህርት ቤት ቀጥሎ እስከ ግሪኳ ቆሮንቶስ እና አቴና ድረስ ዘልቋል፡፡ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን  በቲኦሎጊያ (ነገረ መለኮት) ከአቴና ዩኒቨርሲቲ (1945 ዓ.ም.) ሲያገኙ፣ ለድኅረ ምረቃ ማሳረጊያቸው የሆነውን በጥንታዊ ታሪክ ምርምር በጀርመን አገር ከሚገኘው ቦን ዪኒቨርሲቲ የዱክትርና ዲግሪያቸውን በማዕረግ አግኝተዋል፡፡
ለመታሰቢያቸው የተዘጋጀው ገጸ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው፣ በያኔው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ (በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ) ከ1953 ዓ.ም. እስከ 1970 ዓ.ም. የቲዎሎጊያ እና የጥንታዊና መካከለኛ ዘመን ሥልጣኔና ታሪክ የመጀመርያ ምሁር ሆነው ሠርተዋል፡፡ አስተምረዋል፡፡

በሎንዶን፣ በሐርቫርድ፣ በፕሪንስተን፣ በሔይድልበርግና በላይደን ዩኒቨርሲቲዎች በፌይሎፕሺፕ የተለያዩ ጥናቶች ያደረጉት የስምንት ቋንቋዎች አዋቂው ሊቀ ልሳናት ፕሮፌሰር ሥርግው፣ ለተማሪዎችና ለተመራማሪዎች የሚጠቅሙ እጅግ ጠቃሚ የሆኑ የሚሆኑ መጻሕፍትና ጥናቶች በተለያዩ ቋንቋዎች አበርክተዋል፡፡
(ሀ)  በእንግሊዝኛ ቋንቋ በ1961 ዓ.ም. የታተመው Bibliography of Ancient and Medieval Ethiopian History, 1969
(ሁ) በእንግሊዝኛ ቋንቋ በ1963 ዓ.ም. የታተመው Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270
(ሂ) በእንግሊዝኛ ቋንቋ በጥንታዊ ዘመን የነበረውን የኢትዮጵያ/የግእዝ ሥነ ጽሑፍ አጻጻፍና የመጽሐፍ አጠራረዝ የሚገልጸውና በ1964 ዓ.ም የታተመው Bookmaking in Ethiopia, 1972
(ሃ) በአማርኛ ቋንቋ  በ1970ዎቹ መጨረሻና በ1980ዎቹ መጀመርያ ያቀነባበሩት ባለ 14 ቅጽ አማርኛ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መዝገበ ቃላት በየጊዜው በጥራዝ ለንባብ በቅቷል፡፡
(ሄ) በመጨረሻም በ1992 ዓ.ም. በአማርኛ ቋንቋ የዳግማዊ ምኒልክ ታሪክን  (?በናይሮቢ?) አሳትመዋል፡፡ መጽሐፉ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከውጭው ዓለም ጋር ኢትዮጵያን እንዴት እንዳገናኝዋት የሚያብራራ ነው፡፡  ክቡር እም ክቡራን ዶክተር ሥርግው፣ ለኢትዮጵያችን ካበረከቷቸውና ምንጊዜም ሲታወሱ ከሚኖሩባቸው ዐበይት ተግባሮቻቸው አንዱ የኢትዮጵያ ብራና መጻሕፍት ድርጅት መሥራችና የመጀመርያው ሥራ አስኪያጅ ሆነው ያገለገሉበት ነበር፡፡ ከ1966 ዓ.ም. ዠምሮ ለአምስት ዓመታት በተለያዩ ገዳማትና አድባራት በመዘዋወር በብዙ መቶ የሚቈጠሩ የጥንት የብራና ላይ ጽሑፎችን በማይክሮፊልም ተቀርፀው ለታሪክና ለትውልድ እንዲቆይ ያደረጉ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡
ፕሮፌሰር ሥርግው ከ49 ዓመት በፊት በወርኃ ሐምሌ በታዕካ በዓታ ለማርያም ገዳም ከክብርት ወይዘሮ ሰላማዊት መኰንን ጋር የሠርግ ነ ሥርዓታቸውን የፈጸሙ ሲሆን አምስት ልጆችን አፍርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ በ7507 ዓመተ ዓለም፣ በ2007 ዓመተ ሥጋዌ (በፀሐይ)፣ በ2015 ዓመተ ምሕረት (በፀሐይና በጨረቃ አቈጣጠር)፣ በ1731 ዓመተ ሰማዕታት፣ በዘመነ ሉቃስ፣ በ2326 ዓመተ እስክንድር፣ በ5775 ዓመተ ፍጥረት ዘአይሁድ ቴቬት 6 ቀን፣ በ1436 ዓመተ ሒጅራ ረቢ ዐወል 6 ቀን፣ እሑድ ታኅሣሥ 19 ቀን በፀሐይ፣ ጥር 6 ቀን በጨረቃ፣ በጎርጎርዮሳዊ ቀመር ዲሴምበር 28 ቀን 2014 ዓመተ እግዚእ (AD)፣ በዩሎሳዊ ቀመር ዲሴምበር 15 ቀን 2014 ዓመተ እግዚእ፣ በኮፕቲክ (ግብፅ) ኪያክ 19  ቀን 1731 ዓመተ ሰማዕታት፣ በሊቀ መላእክቱ ቅዱስ ገብርኤል በዓል ነፍስ ኄር ፕሮፌሰር ሥርግው ሐብለ ሥላሴን በቀለም አበባ ዘከርናቸው፡፡ ስወደፊት አሟልተን ለመጻፍ ተሰፋ አለን፡፡
(ሔኖክ መደብር )


No comments:

Post a Comment