ዘመን በተለወጠ ዓመት በተቀመረ ቁጥር ልዩ ስሜት የሚሰጠኝ በተለይ ከመስከረም በኋላ ተከታትለው የሚመጡት የጥቅምትና የኅዳር የታኅሣሥ ወሮች ናቸው፡፡
ምክንያቴም ክረምት ካለፈ በኋላ የሚመጣው የአበባና የነፋስ ወቅት የሆነው መፀው ብዙ ትሩፋቶችን ይዞ ስለሚመጣ
ነው፡፡ አንደኛውና ቀዳሚው የእሸት መድረስ ነው፡፡ ‹‹እህልን በጥቅምት ልጅን በጡት›› እንዲል፡፡ ኅዳሩም ቢሆን
ምርቱ የሚታፈስበት ባቄላው፣ ሽምብራ ሸቱ ሁሉ ከገጠር ወደ ከተማው የሚወጣበት፣ ከተሜውም ከጎዳና እስከ ቀዬው
እየጠረጠረ የሚቀምስበት በመሆኑ በረከቱ ሲሞላ ደስታ ይሰፍናል::
መሰንበቻውን ከአዲስ አበባ እስከ መቐለ ያጋጠመኝ ሽምብራ እሸቱ ባቄላው ወዘተ. የአምናው በልግ (ፀደይ) እና
ክረምት መልካምነትን የዘመኑን አሪፍነት ያመላከተኝ ነው፡፡ ደስታ ብቻ ሳይሆን ደስፈቅ (ደስታና ፍንደቃ)
አድርጎኛል፡፡ ስሸማምት ገንዘቤን ከፍዬና ተቀብዬ ብቻ አይደለም ከነጋዴው የምለየው፤ ‹‹ለከርሞውም ያድርሰን››
በማለት ጭምር እንጂ፡፡
ሰሞኑን ሽምብራ ሸቴን እየጠረጠርኩ በራስ ሙሉጌታ መንገድ ሳቀና በትዝታ ሠረገላ ወደ ኋላ መመለሴ አልቀረም፡፡
በሕይወት ውስጥ መልካም ትውስታ ብቻ አይደለም የሚኖረው አሳዛኝም፣ አስደንጋጭም፣ ዘግናኝም አይታጣበትም፡፡ እንዲህ
እንደ ዘንድሮው በጥቅምትም ሆነ በኅዳር በታኅሣሥም እሸት ያላየሁበት፣ ሽምብራ ያልጠረጠርኩበት ዓመት፣ የከፋ ዓመት
አጋጥሞኝ ነበር፡፡
ከ31 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ ምድር በተለይም በሰሜናዊ ክፍላተ ሀገር ዝናቡ ርቆ ደመናው ሸሽቶ፣ ፀሓዩ ነድዶ፣
ሐሩሩ ገርሮ፣ የበልግ ዝናብም ሆነ ክረምቱ በመራቁ አርሶ አደሩ የሚዘራው አይደለም፣ የሚበላው የሚጠጣው አጥቶ
መከራ የሰፈነበት ዓመተ ፍዳ የሆነበት፣ ሚሊዮኖችን ለሞት ዳርጎ ሌላውም ቀዬውን ትቶ የተሰደደበት ነበር፡፡
‹‹ራቤ ጥማቴ እርዛቴ ሦስቱ
ይደበድቡኛል ባንድ እየዶለቱ›› እያለ አርሶ አደሩ ያንጎራጎረበት ነበር፡፡
ያ ዘመን በተረትና ምሳሌ ‹‹እህልን በጥቅምት›› መሆኑ ቀርቶ ‹‹ሞትን በጥቅምት›› ሆኖ ታየ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደየእምነቱ በተለይም በአዲስ አበባ ከ31 ዓመት በፊት በየደጀ ሰላሙ ምሕላውን ጸሎቱን
ጾሙን ሲያካሂድ፣ የዘመኑ መንግሥት ግን ጉዳዬ ሳይለው ድርቁን ደብቆ ረሀቡን ሸፍኖ ምንም እንዳልተደረገ ቆጥሮ
‹‹ኢሠፓአኮ›› የሚባለውን የኢትዮጵያ ሠርቶ አደሮች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን ወደ ኢሠፓነት ለመለወጥ ሽር ጉድ ያለበት
ነበር፡፡ የኢሠፓን መሥራች ጉባኤ የሚያካሂድበትን ጉባኤ አዳራሽ ለመገንባት (የሰው ሕንፃ እየፈረሰ) እየተጣደፈ
ነበር፡፡ የከተማውን አደባባይ ያሸበርቅ ነበር፡፡
ድርቅ የነገሠበት 1976 ወደ 1977 ሲሸጋገር የከፋ ረሀብ እልቂት ሊያስከትል እንደሚችል ኅብረተሰቡም ሆነ ዕማማኮ (ዕርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን)፡-
‹‹ተራበ አሉት ያ ገበሬ
ምሰሶዋ የሀገሬ››
እያሉ ኧረ መላ ይበጅ፣ አንድ ይባል ቢሉም ሊገነዘብ ያልፈቀደው ደርግ የርሱ ቁብ ፓርቲው ነበርና ሰሚ ጆሮ
አልነበረውም፡፡ በሌኒንና በማርክስ ሐውልቶችም ግንባታ ተወጥሮ ነበር፡፡ በ‹‹አብዮት›› አደባባይ በተናጠል
የነበሩትን የካርል ማርክስ፣ ፍሬድሪክ ኤንግልስና ቭላድሚር ኢሊዪች ሌኒን ምስሎችን በከፍተኛ ወጪ ባንድነት በግንብ
ላይ ምስላቸውን፣ እንዲሁም የዋና ጸሐፊውን ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መስል ሲተክል ነበር፡፡ አዲስ
አበቤም የነማርክስን ምስል አይቶ ቁጭቱን የገለፀው ‹‹በአንድ ጆሮ ሦስት ደንቆሮ›› በማለት ነበር፡፡
የኢትዮጵያ ሬዲዮም ሆነ ቴሌቪዥኑ ሞገድ አሳብሮ የሚያስደምጠን
‹‹የደስ ደስ እሰይ የደስ ደስ
ለፓርቲው ምሥረታ ስንደርስ
የደስ ደስ እንበል ሁላችን
ባንድነት ለፓርቲያችን›› እያለ አገር አማን መሆኑን እያወጀ ነበር፡፡
በተቃራኒው በባሕር ማዶ የሚገኙ የአሜሪካና የጀርመን ሬዲዮኖች ድርቁንና ረሀቡን የተመለከቱ ዘገባና ዝግጅቶች ሲያቀርቡ ጥላሁን ገሠሠ በ1966ቱ ረሀብ ጊዜ ባቀነቀነው፡-
‹‹ዋይ ዋይ ሲሉ
የረሀብን ጉንፋን ሲስሉ›› በማጀብ ነበር፡፡
10ኛው የአብዮት በዓል መስከረም 2 ቀን 1977 ዓ.ም. በጊዜው አጠራር በአብዮት አደባባይ ሲከበር በክብር
ትሪቡኑ በኩል የግድ ተሰልፈው እንዲያልፉ የተደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የተደበቀው ድርቅና ረሀብ
አንገብግቧቸው ነበርና ንዴታቸውን የገለጹት በወቅቱ ስለ ፓርቲው ምሥረታ ይዘፈን የነበረውን ‹‹ፓርቲያችን ኢሠፓ
የትግል ውጤታችን?›› የሚለውን በመቀየር ‹‹ፓንታችን ይሰፋ በልክ በቁጥራችን›› እያሉ በነሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ
ፊት ያለፉት፡፡
ቢቢሲን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ድርቅና ረሀቡን ለዓለም በማስተጋባታቸው ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም
ለዕርዳታ ተሰለፈ፡፡ “We are the World” የተሰኘው ታላቅ የሙዚቃ ሥራም በነቦብ ጌልዶፍ ተከናወነ፡፡
ገበሬው ግን 1976 ላይ ደመናው መጣ እያለ ሲቀርበት ጭንቅ ውስጥ ሲገባ ያለው፡-
‹‹እርሻ በደመና ይመረት በነበር
ያንን ሰባ ሰባት እሻገረው ነበር፡፡›› ነበር፡፡
ያኔ 1971 ዓ.ም. ‹‹አድሃሪያንን ብቻ ሳይሆን ተፈጥሮንም በቁጥጥራችን ሥር እናውላለን›› ይል የነበረው ደርጋዊው ሥርዓት ከአባዜው ባለመላቀቁ ገበሬው በፊናው፡-
‹‹አሥራ አምስት ኮሚቴ ሲያናፋ ሲያናፋ
በሰማይ ዳመና በምድር ዝናብ ጠፋ›› ነበር ያለው፡፡
ምስጋና ለ‹‹ሰሚ ያጡ ድምፆች›› ጸሐፊው ፈቀደ አዘዘ ይሁንና የገበሬውን እንጉርጉሮ አኑሮልናል፡፡ በ1977
ዓ.ም. በረሀብ የተጠቃው ሰሜን ሸዋ ኅብረተሰብ ለረሀቡ ‹‹አጉርጣቸው›› የሚል ስም ሰጥቶታል፡፡ በ1948 ዓ.ም.
በአካባቢው ደርሶ ከነበረውና ‹‹አጉርጣቸው›› ብሎ ከሰየመው ረሀብ ጋር አያይዞ ገልጾታል፡፡
‹‹የዱባለ ወንድም አጉርጣቸው ነኝ
እቤት አልገባሁም ከገበያ ላይ ነኝ››
ከ41 ዓመት በፊት የካቲት 1966ን አብዮት ያስከተለው ድርቅና ረሀብ ለዘውዳዊ ሥርዓት መገርሰስ አንዱ ሰበብ
ሆኖ እንዳላለፈ 10 ዓመቱን ጠብቆ ድርቅና ረሀብ ሲመጣ በወቅቱ ለመቋቋም ፈቃደኛነት ያልነበረው (ፓርቲውን ከመሠረተ
ከወራት በኋላ ርብርብ መጀመሩን ልብ ይሏል) ደርግ ቁብ የሰጠው የዓለም ኮሚኒስቶችና ሶሻሊስቶች ከምሥራቅም
ከምዕራብም የነበሩ (ያሉ) ለመጀመሪያና ለመጨረሻ ጊዜ በአንድ መድረክ በኢትዮጵያ ተሰባስበው የኮሚኒዝምን የቁም
ተዝካር የበሉበትን የኢሠፓ ምሥረታ ማከናወን ነበር፡፡
ጳጉሜን 1976 ዓ.ም. ዘመኑ በኢትዮጵያ ትውፊት በዘመነ ዮሐንስ፣ በአዲስ አበባው የአራት ኪሎው ጉባኤ
አዳራሽ የኢሠፓ ጉባኤተኛው ከስኮትላንድ በመጣው ውስኪ ሲራጭ በገጠር ግን ሕዝቡ በረሀብና ጠኔ ሲያልቅ ነበር፡፡
አርሶ በሌውም፡-
‹‹ዘመነ ዮሐንስ ሁለተኛ አትምጣ
እንኳን የእህል ቅንጣት ዛፉ ቅጠል አጣ›› እያለ አንጎራጉሯል፡፡
‹‹ልጅ ‹እንጀራ እንጀራ!
እናት ‹የለም! የለም!›
ቀኑ እኮ አጉርጥ ነው
ጠግቦም መብላት የለም››ም ተብሏል፡፡
እነ ቢቢሲ የድርቁንና የረሀቡን ዘመን 30ኛ ዓመት እያሉ ቢዘክሩትም እኛ ግን 31ኛ ዓመቱን ነው ምናስበው፡፡
ገበሬው እንዳለው ‹‹ይኸ ሰባ ሰባት ይቅር አይነሣ
እርጉዝ ላሜን ሸጥኳት
ለሁለት ቀን ምሳ፡፡››
(ዶሴ ዘእንደራሴ ከአዲስ አበባ)
No comments:
Post a Comment