‹‹መፀው ባተች፣ ልቤም እንዳበባ ፈካች፣
እንደ ግልገል፣ እንደ
እንቦሳ ናጠች።
ትንፋሼም ረዘመ፣ ጠለቀ፣ ውስጤን አጠራው፣
የመፀው አየር ሳንባዬን ሞላው።
ይክበር ይመስገን፣ አምላክ ደግ ነው፣
የእፎይታዬ ምንጭ ባተችልኝ መፀው።›› ላምሮፍ የተባለ ጸሐፊ ያሰረው ስንኝ
ነው፡፡
አዲስ ዓመት ከባተ፣ መስከረም ከጠባ
ሦስት ወር
ከአምስት ቀን
ሆኖታል፡፡ በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢ የክረምቱ ወቅት አብቅቶ የአበባና የነፋስ ወቅት የሆነው መፀው ከገባም ሰነባብቷል፡፡
መስከረም 26 ቀን የተጀመረው ‹‹መፀው›› የአበባ ወቅት፣ በኦሮሞ ‹‹ቢራ››፣ በከምባታ ‹‹በሪ ወሎተ›› (ማሬ)፣ በጠምባሮ ‹‹በሪ ወሊሱ››፣ በሐላባ ‹‹ማላታ››፣ በዳውሮ ‹‹አይሌ››፣ በሐዲያ ‹‹ፌቴ›› (ብራ)፣ በባስኬቶ ‹‹ጉፃፃ›› (የአበባ ወራት)፣ በቤንች ‹‹ቤያርግ›› (አዲስ
ዓመት የአደይ አበባ በብዛት የሚበቅልበት)፣ በየም
‹‹ማር››፣
በጉራጌ ‹‹ዊጠገና››፣ በአማራ ‹‹ጥቢ››፣ በትግራይ ‹‹ቀውዒ›› ይሰኛል፡፡ በሌሎች ብሔረሰቦችም የተለያየ ስም አለው፡፡ እስከ ታኅሣሥ 25 ቀን ድረስ የሚቆየው ወቅቱ
ሌላው መጠርያ መኸር ይሰኛል፡፡
ዘመነ መፀው 90 ቀናት ሲኖሩት ዕለታቱን የሚካፈሏቸው ወራት አራት ናቸው፡፡ የእነዚህ ወራት ስያሜ የት መጣ ከእርሻ ተግባር ጋር
የተያያዘ መሆኑን የቋንቋና ባህል ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ እንዲህም ያፍታቱታል፡፡
መስከረም (መሐሰ-ከረመ)፡- (ባለ 5 ቀን) ገበሬ መሬትን አርሶ አለስልሶ እንዳከረማት ሁሉ
ለዘር የተመቸች ሆና ተገኝታ ነበርና መሐሰ (ቆፈረ) እና ከረመ የሚሉትን ሁለቱ ግሶች በማቀነባበርና በማስተባበር መስከረም ተባለ፡፡ ይህም
አጥብቆ ታርሶ
ከረመ እንደማለት ስሙን ከግብሩ ነስቶ
የሚጠራበት ነው፡፡ በሌላ በኩልም ‹‹መዝከረም›› ብለው ‹‹መዘክረ ዓም››
የዓመት መታወሻ፣ መዘከርያ መነሻ ከሚል አገላለጽ ስሙ
መገኘቱም ይወሳል፡፡
ጥቅምት (ጥቅም-ጥንት)፡- (ባለ
30 ቀን) የጥቅም መጀመሪያ፡፡ ከመሬት ብዙ
ጥቅም የሚገኝበት እህልና ተክል ሁሉ ፍሬ የሚሰጥበት የፍሬ ወር ማለት ነው፡፡ በሌላም በኩል
“ጠቀመ” (ገነባ) ብለው ይፈቱትና ከዓለም ፍጥረትና ከዓለም መገንባት፣ መፈጠር ጋር ያያይዙታል፡፡
‹‹ልጅን በጡት
እህልን በጥቅምት›› እንዲሉ፡፡
ኅዳር (ኀደረ)፡- (ባለ 30 ቀን) ያዝመራ ወራት፡፡ ሰዎች
ሁሉ ሰብላቸውን ከዝንጀሮ ለመጠበቅ ጐጆ
እየሠሩ በየዱሩ የሚያድሩበት ስለሆነ ኅዳር
ተባለ፡፡ ከነምሳሌው ‹‹ኅዳር ከፈለግህበት ማደር››
እንዲሉ፡፡
ታኅሣሥ (ኀሠሠ)፡- (ባለ 25 ቀን) ማሠሥ መፈለግ፤ መጥረግ፤ የእህል አጨዳ የሚፈጸምበት ጊዜ ወይ ማብቂያው ስለሆነ ታኅሣሥ ተባለ፡፡
ከታኅሣሥ 26 በኋላ የሚመጣው በጋ ሲሆን፣ ዘመኑን መጋቢት 25 ቀን ከፈጸመ በኋላ
በማግስቱ ለፀደይ ያስረክባል፤ ፀደይም እስከ
ሰኔ 25 ቆይቶ
በማግስቱ ለክረምት ቦታውን ይለቃል፡፡ ቀለልና ለስለስ ያለ ዝናብ የሚኖርበት በልግ
በከፊል በጋ
ላይና ፀደይ
ውስጥ የሚገኝ ነው፡፡
አደይ አበባንና አበባን፣ እሸትንና ነፋስን አማክሎ የያዘው ዘመነ መፀው ለሠዓልያን፣ ለዘማርያን፣ ለደራስያን፣ ለሙዚቀኞች፣ ለድምፃውያን ሰበበ ድርሰት ለመሆን ታድሏል (አንዳንዶች ከፀደይ ጋር ቢያደባልቁትም)፡፡
ዘመነ መፀውን ካወደሱ መካከል ታላቁ
ባለ ቅኔ
ነፍስ ኄር
ዮሐንስ አድማሱ ይገኝበታል፤ የዛሬ 50 ዓመት ‹‹ይሰለቻል ወይ?››
በሚለው ግጥሙ
ከኮረዳ ጋር
አያይዞ አሰናኝቷል፡፡
‹‹ይሰለቻል ወይ?
የመፀው ነፋስ
የጥቅምት የኅዳር የትሣሥ አየር አብራጃው ሲነፍስ…››
ምንጭ፡-ሪፖርተር
No comments:
Post a Comment