Saturday, December 27, 2014

‹‹ሰው ያልፋል ታሪክ ግን ይተርፋል››



ከ12 ዓመት በፊት  ታኅሣሥ ወር በባተ በ29ኛው ዕለት በጀርመን ሙኒክ ከተማ ያረፉት ታላቁ የታሪክና የቲኦሎጊያ ፕሮፌሰርና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሊቅ  ዶክተር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ (1921- 1995)፣ ዜና ዕረፍታቸውን ተከትሎ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል  የመታሰቢያ ዝግጅት ሲደረግላቸው አንድ አባት ‹‹ሰው ያልፋል ታሪክ ግን ይተርፋል›› ብለው እንደነበረ አስታውሳለሁ፡፡ ለዚች ትውስታዬ መነሻ የሆነኝ On this day late us remember Prof Sergew Hable Selassie (1929-2003)  በሚል መንደርደርያ በስንክሳራዊ ያጻጻፍ መነሻ አበበ ሐ. ወይን  በፌስቡክ ገጻቸው የጻፉት ዝክረ ሥርግው ነው፡፡

ፀሐይዋ እየጠለቀች ያለው ‹‹በስሜን ተራራ›› ነው? ወይስ ‹‹በሰሜን ተራራ?››

ፀሐይዋ እየጠለቀች ያለው ‹‹በስሜን ተራራ›› ነው? ወይስ ‹‹በሰሜን ተራራ?›› ብዙ ጊዜ በጽሑፍም ሆነ በንግግር ‹‹ሰሜን ተራራ ብሔራዊ ፓርክ›› እየተባለ የሚጠቀሰው ስህተት ነው፡፡ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት (ደርግ) ከ40 ዓመት በፊት ክፍለ ሀገሩን ጎንደር (በኢሕዲሪ ዘመን ሰሜን ጎንደር እና ደቡብ ጎንደር መባሉን ልብ ይሏል) ብሎ ከመሰየሙ በፊት፣ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በጌምድርና ስሜን ጠቅላይ ግዛት ይባል ነበር፡፡ ፓርኩም ስሜን ይባል ነበር፡፡

Saturday, December 20, 2014

የሳምንቱ ገጠመኝ

ዘመን በተለወጠ ዓመት በተቀመረ ቁጥር ልዩ ስሜት የሚሰጠኝ በተለይ ከመስከረም በኋላ ተከታትለው የሚመጡት የጥቅምትና የኅዳር የታኅሣሥ ወሮች ናቸው፡፡
ምክንያቴም ክረምት ካለፈ በኋላ የሚመጣው የአበባና የነፋስ ወቅት የሆነው መፀው ብዙ ትሩፋቶችን ይዞ ስለሚመጣ ነው፡፡ አንደኛውና ቀዳሚው የእሸት መድረስ ነው፡፡ ‹‹እህልን በጥቅምት ልጅን በጡት›› እንዲል፡፡ ኅዳሩም ቢሆን ምርቱ የሚታፈስበት ባቄላው፣ ሽምብራ ሸቱ ሁሉ ከገጠር ወደ ከተማው የሚወጣበት፣ ከተሜውም ከጎዳና እስከ ቀዬው እየጠረጠረ የሚቀምስበት በመሆኑ በረከቱ ሲሞላ ደስታ ይሰፍናል::
 መሰንበቻውን ከአዲስ አበባ እስከ መቐለ ያጋጠመኝ ሽምብራ እሸቱ ባቄላው ወዘተ. የአምናው በልግ (ፀደይ) እና ክረምት መልካምነትን የዘመኑን አሪፍነት ያመላከተኝ ነው፡፡ ደስታ ብቻ ሳይሆን ደስፈቅ (ደስታና ፍንደቃ) አድርጎኛል፡፡ ስሸማምት ገንዘቤን ከፍዬና ተቀብዬ ብቻ አይደለም ከነጋዴው የምለየው፤ ‹‹ለከርሞውም ያድርሰን›› በማለት ጭምር እንጂ፡፡


Friday, December 19, 2014

ሴቶች የነገሡበት


ጥንታዊቷ የመቐለ ከተማ በነሐሴ መንፈቅ፣ ልዩ ድባብ የሚያለብሳት ከተሜውም ሆነ ከዚያም ውጪ ያለውን ኅብረተሰብ ቀልብ የምትገዛበት አጋጣሚን ታገኛለች፡፡ ዓመት ሄዶ ዓመት ሲመጣ 12ኛው ወር ላይ ከምትመጣው ‹‹አሸንዳ›› ጋር ትገናኛለች፡፡
ልጃገረዶችም በልዕልና የሚታዩበት፣ በነፃነት ነግሠው የሚጫወቱበት የአሸንዳ በዓል፡፡ 
ከሕፃን እስከ አዋቂ የበዓሉ መገለጫ በሆኑ አልባሳትና ማጋጊያጫዎች የሚታዩት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ ነው፡፡ 
ከቀደምት የሥነ ሕንፃ ጥበብ (እነ ሕድሞ፣ አፄ ዮሐንሰ ቤተ መንግሥት ወዘተ.) እስከ ዘመናዊዎቹ ሕንፃዎች የሚታዩባት መቐለ ከተማ ከነሐሴ 15 ቀን 2006 .. ጀምሮ ለሦስት ቀናት በዘለቀው በዓልም የሸሩባዎች መዲና ያሰኛትን ገጽታም ተላብሳ ነበር፡፡ 
የፀጉር አሠራሩ ከአልባሶ እስከ ግልብጭ፣ ከጋመ እስከ ድርብ፣ ከደቃቅ እስከ ጉልህ ከሕፃን እስከ አዋቂ ተቆናጅተው የታዩበትም ጭምር ነው፡፡ ከቱባው ባህል ልብስ አንሥቶ ከዘመናዊው ስፌት ከተገኙት ጃርሲ፣ ሽፎን ቀሚስ ጋር ተውበው የሚታዩበትም ነው፡፡
ጌጣጌጡም ልዩ ልዩ ዓይነት ነው፡፡ አንገት ላይ ከሚንጠለጠለው ሕንቆ፣ እግር ላይ እስከሚጠለቀው አልቦ በልብስም በአካልም ላይ ይታያል፡፡ ኮንጎ ጫማም ቦታዋን ይዛለች፡፡ 
የበዓሉ ኩነት ለከተማው ባዳ፣ ለአካባቢው እንግዳ ለሆነው ብቻ ሳይሆን በዚያው ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ ማስደነቁ፣ ማስደመሙ ቀልብ መግዛቱ የማይሳት ነው፡፡ 
‹‹የዓይኖቿ ውበት ያንገቷ ሙስና (ውበት ማለት ነው)
ሮብ ያስገድፋል እንኳን ሐሙስና›› የሚለውን መንቶ ግጥም የሚያስታውሰው ቆነጃጅቱ ዓይናቸው ላይ የተኳሉት ኩል በቤት ተወቅጦ የተዘጋጀ ነው፡፡ 
የአሸንዳ መንፈስ፣ በፀጉር አሠራርና በአልባሳት፣ በመዋቢያ ቁሶችና በመጋጋጪያዎች ብቻ አይደለም የሚገለጠው፣ ርሱን የሚያገዝፉ የሚያጎሉ የተለያዩ ዘፈኖች ይገኙበታል፡፡ 

ነሐሴ 16 ቀን ከሚከበረው የፍልሰታ ለማርያም በዓል ጋር የተያያዘው አሸንዳን ማክበር የተጀመረው በዋዜማው ነው፡፡ ነሐሴ 15 ከሰዓት በኋላ በመቐለ ከተማ ዋና ዋና ጎዳናዎች በቀረበ ትዕይንት በዓሉ መድረሱ ተበስሯል፡፡ ከተለያዩ የትግራይ ዞኖች የመጡትን የአሸንዳ ልጃገረዶች፣ 
‹‹መፀት መፀት
     ኣሸንዳ ዕምባባ መፀት››
(መጣች መጣች፣ አሸንዳ አበባ መጣች) እያሉ ከታላቁ ንጉሠ ነገሥት አፄ ዮሐንስ ቤተ መንግሥት አደባባይ ተነሥተው በፒያሳ ሐውዜን አደባባይ በኩል በዋና ዋና ጎዳናዎች የተጓዙትና መቐለ ስታዲየም ‹‹ባሎኒ›› የደረሱት በክልሉ የፖሊስ ማርሽ ባንድ በመታጀብ ነበር፡፡ 
እንደክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ አቶ ከበደ አማረ በላይ አገላለጽ ከሆነ፣ አሸንዳ ከትግራይ ሰባት ዞኖች አምስቱ በድምቀት እንደሚያከብሩትና  ስድስተኛው ዞን ሽሬ በተመሳሳይ መልኩ በዓሉን ለማክበር እናቶች ልጆቻቸውን ለማሠልጠን እየተጉ ናቸው፡፡ 
አሸንዳ በባሎኒ (ስታዲየም) ውስጥ ከነበረው የመክፈቻ አከባበሩ ይልቅ በዕለቱ በከተማዋ እንብርት ሮማናት አደባባይ (የአፄ ዮሐንስ 4 ሐውልት ሊተከልበት የታሰበበት ቦታ) 10 ሰዓት እስከ ምሽት የዘለቀው ጭፈራ ገጽታ ልዩ ነበር፡፡ 
ከስድስት አቅጣጫዎች ወደ ሮማናት አደባባይ በቡድን በቡድን ሆነው ከበሮዋቸውን እየመቱ ክብ ሠርተው እንደራያ፣ ተምቤን፣ እንደርታ ወዘተ ባህል ሲጫወቱ ላየ ቀልብ የሳቡለት ሆነዋል፡፡ ወንዶችም በጭፈራው አልተለይዋቸውም፡፡ 
አበበች ብርሃኑ የመቐለ ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ፋኩልቲ 3 ዓመት ተማሪ ነች፡፡ በሌሎች ቡድኖች ውስጥ የሚታዩት ሴቶች እንደለበሱት በኅብረ ቀለማት በታጀበው ጀርሲና ዲስካ ሳይሆን እንደርሷ አገላጽ፣ የራያ ባህላዊ አለባበስና የአሸንዳ መገለጫ የሆነው ሹፎን ነው፡፡ በአበበች ቡድን ውስጥ ሆነው ይጫወቱ የነበሩት በሙሉ የመጡትም ከራያ (ደቡባዊ ትግራይ) ነው፡፡
ከለበሰችው ቀሚስ በላይ የደረበችው ጉፍታ ሙስሊሞች ፀጉር ለመሸፈን የሚጠቀሙበት ነው፡፡ ጌጣ ጌጦችም አንዱም አልቀረባትም፡፡ ማይጨው ተወልዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በጥላሁን ግዛውና ማጂክ ካርፔት ትምህርት ቤቶች ያጠናቀቀችው አበበች፣ ሞዴልና የዘንድሮ ወይዘሪት መቐለ ዩኒቨርሲቲ ስትሆን፣ በቴሌቪዥን ድራማ ‹‹ጎጆ›› በተዋናይነት ሠርታለች፤ በአሸንዳውም መሪዋ እሷ ናት፡፡ 

በክረምት ወቅት ከሚበቅለው የአሸንዳ ተክል ስሙን የወረሰውና በአብዛኛው ትግራይ ልጃገረዶች አሸርጠው የሚጫወቱበት የአሸንዳ በዓል አከባበር በዋናነት የትግራይ ሴቶች በዕድሜ ደረጃቸው ተቧድነው የሚያከብሩት ነው፡፡ ከትግራይ ከሚዋሰኑት ጋርም ባህላዊ መወራረስ ስላለ በሰሜን ወሎ ቆቦ (ሶለል ይባላል) በዋግ ህምራ ሰቆጣ (ሻደይ) በላስታ ላሊበላ (አሸንድዬ) በሰሜን ጎንደር፣ በደቡብ ኤርትራ ጭምር ይከበራል፡፡