በ 3 03 2004 ዓ.ም. ሪፓርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ
በኦሮሚያ ክልል ጉጂና ቦረና ዞኖች ውስጥ የሚኖረው አንድ ጎሳ ትክክለኛው መጠሪያ ስሜ ‹‹ዋዩ›› እንጂ ‹‹ዋታ›› ስላልሆነ ይስተካከልልኝ ሲል አቤቱታውን ለክልሉ ፕሬዚዳንት ቢሮ አቀረበ፡፡ አዲስ አበባ በመገኘት አቤቱታውን በግንባር ያቀረቡት የጎሳው ዐሥራ አንድ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተወካዮቹ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጉጂና ቦረና ዞኖች የሚገኘው ጎሳው ኦርጂናል መጠርያው ዋዩ ሆኖ ሳለ፣ ባለፈው ገዢ መደብ የመከፋፈል ሥርዓት ‹‹ዋታ›› በሚል ስያሜ ሲጠራ ኖሯል፡፡ ‹‹ዋታ›› መጥፎ ትርጉም ያለው ከሌብነት፣ ከአደን፣ ከስድብ ከዝቅተኛነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ አስነዋሪው ስም እንዲቀየር ባለፉት 16 ዓመታት ጥረት መደረጉን ከተወካዮቹ አንዱ የሆኑት አቶ ጎዳና ጡና ተናግረዋል፡፡
ከአራት ገዳ በፊት የጎሳው መጠሪያም ሆነ የሚደረገው ጫና ተገቢ አይደለምና ይቀየር ተብሎ ቢታወጅም፣ ከከንፈር ንግግር አለማለፉን ያመለከቱት ተወካዮቹ፣ ኢሕአዴግ ከመጣም በኋላ ባለፉት ሁለት ገዳዎች (16 ዓመት) እንዲስተካከል ሲታወጅ ሕዝቡ ይህን ተቀብሎ ይለወጥልናል ብሎ ሲጠብቅ ምንም ለውጥ አለመምጣቱን ጠቅሰዋል፡፡
ከዚህም የተነሣ የጎሳው ኅብረተሰብ በጉጂ ዞን ሊበን ወረዳና በቦረና ዞን ወንዶ ባደረገው ስብሰባ፣ ‹‹ኦሪጅናል ስማችን ዋዩ ነውና ሒዱና ለመንግሥት አስታውቁልን›› ብለው እንደወከሏቸውና፣ ‹‹በንቀት ስሙ ምክንያት ጤናቸው የተቃወሰ አሉ፡፡ ስማችንን አሳውቁልን፡፡ በሕጋዊ መንገድ እንጠራ፤›› ብለዋል፡፡
ተወካዮቹ በኦሮሚያ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት በተገኙበት ጊዜ ምክትል አፈ ጉባኤው ኅዳር 29 ቀን በሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ባህላቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ እንደሚዘጋጅላቸው እንደነገሯቸው አውስተዋል፡፡
አቤቱታቸውን የተቀበለው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት ቢሮ ያቤሎና ነገሌ ለሚገኙት የቦረና እና ጉጂ ዞኖች ባስተላለፈው ደብዳቤ፣ ከተለያዩ ወረዳዎች የመጡት የዋዩ ጎሳ ሽማግሌዎች ያቀረቡት የስም ይታረም ጥያቄ የጎሳው ስለመሆኑ ጠይቃችሁ በአስቸኳይ ሪፖርት አድርጉ ብሏል፡፡
No comments:
Post a Comment