Saturday, December 10, 2011

‹‹ከተሞች ውስጥ የሚሞተው ሁልጊዜ ይታወሳል ገጠሮች ላይ የሚሞተው ይጠፋል››

 
በ 24 03 2004 ዓ.ም. ሪፓርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ
ከሰባ ስድስት ዓመት በፊት የተፈጸመው የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ብዙ መከራዎችን ትቶ ማለፉ አይዘነጋም፤ እርመኛ አርበኞች የአገሪቱን ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ የብዙ ደራስያንን፣ ጸሐፍትን ቀልብ መግዛቱም አልቀረም፡፡

የፋሽስት ወንጀለኞች የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት፣ በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዝ ያደረሱትን እልቂት ትኩረት ሰጥተው ከጻፉት ደራስያን መካከል የተሰለፉት አንዱ አቶ ጥላሁን ጣሰው ናቸው፡፡ ይህንኑ የፋሺስት ክሥተት፣ የአርበኞችና የሕዝቡን ተጋድሎ የሚያወሳ ታሪካዊ ልብ ወለድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፈዋል፡፡
ሻማ ቡክስ ያሳተመውና ‹‹Trying Times (ትራዪንግ ታይምስ) ብለው የሰየሙት መጽሐፍ፣ ባለፈው ዓርብ መስቀል አደባባይ በሚገኘው የቡክ ወርልድ መጻሕፍት መደብር አስመርቀዋል፡፡

ትራዪንግ ታይምስ በአንድ በኩል የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራን ታሪክ ሲያሳይ በሌላ ገጹ ልብ ወለዳዊ ነው፡፡ ለቤተሰባቸው ሳያሳውቁ ከገጠር የዘመቱ ሴቶች ታሪክም ይዟል፡፡ ታሪክና ልብ ወለድን አጣምሯል፡፡ በልብ ወለዱ ታዋቂ የሆኑ አርበኞች እነራስ አበበ አረጋይ፣ በሻህ አቦዬ፣ ግዛቸው ኃይሌ፣ መኩሪያ መንገሻ ተጠቅሰዋል፡፡

1928 
.. ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን የወረረችው፣ በቅኝ በያዘቻቸው በሰሜን በኤርትራ በኩልና በደቡብ ምሥራቅ በኢጣሊያን ሶማሊላንድ በኩል 400 ሺሕ ወታደሮች፣ 300 የጦር አውሮፕላኖች 30 ሺሕ ተሽከርካሪወችና 400 ታንኮች አማካይነት መሆኑ ያመለከተው የልብ ወለዱ የጀርባ ሽፋን መግለጫ፣ ሙሶሎኒ በወቅቱ የደረሰበትን ሽንፈት ለመቋቋምና ለመቀልበስ የወሰደው እርምጃ ሠራዊቱ በመርዝ ጋዝ እንዲጠቀም ማዘዙ ነው፡፡

የታኅሣሥ 18 ቀን 1928 .. የሙሶሎኒ ትዕዛዝ በተምቤንና በሐሸንጌ ሐይቅ ለሺዎቹ እልቂት ሰበብ ሆኗል፡፡

ደራሲ ጥላሁን የመርዝ ጭፍጨፋውን 75 ዓመት 2003 .. ለማሰብ ያዘጋጁት ‹‹ትራዪንግ ታይምስ›› እንዳሰቡት በወቅቱ ባይወጣም 76 ዓመቱ ለመታተም በቅቷል፡፡

ደራሲው በመጽሐፉ ምረቃ ወቅት እንደገለጹት፣ ታሪኩን በእንግሊዝኛ መጻፍ ያሰኛቸው 700 ሺሕ ያህል ሰዎች በኬሚካል ጦርነት ያለቁበትን ሁኔታና አተያይ ከኢትዮጵያ አንጻር ለውጩዎቹ ለማሳየት ነው፡፡ ‹‹በተምቤን ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵያውያን ዘመናዊ ባልሆኑ መሣርያዎች ድል አድርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ጦር ድል በማድረጉ ፋሺስት የኬሚካል ጥቃቱን ፈጸመ፡፡ በዚያን ጊዜ ያለቁት 700 ሺሕ የሚደርሱ ናቸው፡፡››

አቶ ጥላሁን፣ በተምቤን ጦር ግንባር አዛዥ የነበሩት ራስ ካሳ በመጽሐፋቸው የገለጹትን፣ ከፈረንሣይኛ ተተርጉሞ ያገኙትን አውስተዋል፡፡ ‹‹የተምቤን ጦርነት ጊዜ አሸነፍን፤ ዋናው ነገር [ኢጣሊያ] ሩቅ የሚመታ መሣርያ አላቸው፤ እኛ በቅርብ ሆነን ማጥቃት እንችላለን፡፡ በዚህ ሁኔታ ላይ ተዝናንተን ሳለን አንድ ቀን የእነርሱ አውሮፕላኖች ቢመጡ እንፈትሻቸዋለን ስንል በጣም ከርቀት ሆነው አውሮፕላኖቹ ለእርሻ አረም ማጥፊያ በሚሆን መርጪያ ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ ጥይት የሚደርስበት አይደለም፡፡ ዝም ብሎ ይወርዳል ኬሚካል ሰልፈር (ድኝ) አለው፡፡ መስተርድ ጋዝና ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ጣሉ፡፡ ሰውም መቃጠል አገርም በሙሉ መቃጠል ጀመረ፡፡ ዋሻው ውስጥም ሆኖ መቋቋም አይቻልም ሰው ሁሉ አለቀ፡፡ አንድም ጣሊያን ከዚያ በኋላ አልሞተም፡፡››

የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች በተለይ የፋሺስት ደጋፊ የሆኑት፣ በተምቤን ስለተካሔደው ጦርነት ‹‹የመጀመርያው የተምቤን ጦርነት›› ‹‹ሁለተኛው የተምቤን ጦርነት›› በማለት ታሪኩን ያዛባሉ፡፡

‹‹
የመጀመርያው የተምቤን ጦርነት የሚሉት ኢትዮጵያውያኑ የተወሰነ ድል አገኙ፡፡ ሁለተኛው የተምቤን ጦርነት ላይ ግን በራስ ካሳና ራስ እምሩ ሥዩም የሚመራውን ጦር አሸነፉት ይላሉ፡፡›› አቶ ጥላሁን እነዚያን ጸሐፍት ከመሞገት አልተመለሱም፡፡

‹‹
ሁለተኛ የተምቤን ጦርነት የሚባል ነገር አይኖርም፡፡ ሒሮሺማና ናጋሳኪ ላይ የአቶሚክ ቦንብ በመውደቁ የሒሮሺማና የናጋሳኪ ጦርነት የሚባል ነገር እንደሌለ ሁሉ አንድም ሰው በውጊያ ባልሞተበት በአውሮፕላን በተረጨ መርዝና ከሰልፈር (ድኝ) እና በተቀጣጣይ ፈንጂ በተደበላለቀ ሁሉ ማለቁን ያወሩናል፡፡

በሐሸንጌ ሐይቅ ስለደረሰው እልቂት የራስ ካሳ እይታንም ደራሲው አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ሁሉም የቀይ መስቀል ፈረንጆች ሠራተኞች ከተመለሱ በኋላ በሐሸንጌ ሐይቅ ሜዳ ላይ የሔዱት ሰዎች ሐይቁ ከተመረዘ በኋላ በሙሉ ያልቃሉ፡፡››

ይህ ዘግናኝ ክሥተት በውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች ሲቀርብ የተገለጸው ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ ጦር መሸነፉን በሐሸንጌ ሐይቅ ውስጥ በሞላው ሬሳ አወቅነው፤›› ተብሎ ነው፡፡

የዚያን ጊዜ ያለቁት ከወንድሞቻቸው ጋር ወደ ጦር ሜዳ የሔዱ በአብዛኛው ሴቶች፣ ሲቪልና ጥቂት ቁስለኞች መሆናቸውን ያመለከቱት አቶ ጥላሁን፣ አጽንዖት የሰጡበት ነገርም አለ፡፡ ‹‹እኛ አዲስ አበባ ውስጥ ስለተደረገውና ጥቂት ሺሕ ሰዎች ስላለቁበት እናስባለን፡፡ ያኛው በገጠር የተከናወነው ግን እየተረሳ ይሔዳል፡፡ ከተሞች ውስጥ የሚሞተው ሁልጊዜ ይታወሳል፡፡ ገጠሮች ላይ የሚሞተው ይጠፋል፡፡››

አቶ ጥላሁን እንዳሉት የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራው የኢትዮጵያ ጦር በተምቤን ላይ የተቀዳጀውን የመጀመርያ ድል 75 ዓመቱን በልዩ ዝግጅት አምና ላይ ለማሰብ አልመው የነበረው በዓለም የኬሚካል ጦርነትን በመቃወም አቶሚክ ቦምብን ጨምሮ ሌሎቹንም ለማስወገድ ከመታገል አኳያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማክበር ነበር፡፡

ባለ 239 ገጹ ‹‹ትራዪንግ ታይምስ›› በውስጡ 10 የካርቱን ሥዕሎች አሉት፡፡ አብዛኞቹ ካርቱኖች የሰር ዴቪድ አሌክሳንደር (1883-1956) ናቸው፡፡ 1920ዎቹ ስለነበረው የፋሺዝም አነሣሥ በሚያወሱ ዝነኛ ካርቱኖች ሰር ዴቪድ ይታወቃል፡፡

በታሪካዊ ልብ ወለድ የመጨረሻው ክፍል አስር የሚታየው የካርቱን ሥዕል ሙሶሎኒ እንቅልፍ ደብቶት ሲያቃዠው፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በብሩኅ ገጽ ካባ ደርበው ከመኝታ ክፍሉ ሲዘልቁ ሙሶሎኒ በረአድ በፍርሃት ቅዠት ውስጥ ይታያል፡፡

No comments:

Post a Comment