Saturday, December 10, 2011

‹‹መጠሪያችን ዋዩ እንጂ ዋታ አይደለም››


በ 3 03 2004 ዓ.ም. ሪፓርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ
በኦሮሚያ ክልል ጉጂና ቦረና ዞኖች ውስጥ የሚኖረው አንድ ጎሳ ትክክለኛው መጠሪያ ስሜ ‹‹ዋዩ›› እንጂ ‹‹ዋታ›› ስላልሆነ ይስተካከልልኝ ሲል አቤቱታውን ለክልሉ ፕሬዚዳንት ቢሮ አቀረበ፡፡ አዲስ አበባ በመገኘት አቤቱታውን በግንባር ያቀረቡት የጎሳው ዐሥራ አንድ ተወካዮች ናቸው፡፡ ተወካዮቹ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በጉጂና ቦረና ዞኖች የሚገኘው ጎሳው ኦርጂናል መጠርያው ዋዩ ሆኖ ሳለ፣ ባለፈው ገዢ መደብ የመከፋፈል ሥርዓት ‹‹ዋታ›› በሚል ስያሜ ሲጠራ ኖሯል፡፡ ‹‹ዋታ›› መጥፎ ትርጉም ያለው ከሌብነት፣ ከአደን፣ ከስድብ ከዝቅተኛነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ አስነዋሪው ስም እንዲቀየር ባለፉት 16 ዓመታት ጥረት መደረጉን ከተወካዮቹ አንዱ የሆኑት አቶ ጎዳና ጡና ተናግረዋል፡፡

የአለቃ ገብረ ሐና ታሪክ በአውስትራሊያ ታተመ

በ 27 03 2004 ዓ.ም. ሪፓርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ
ዛሬ 190 ዓመታቸው በዚያው ይዘከራል

የአሥራ ዘጠነኛው ምእት ዓመት ኢትዮጵያዊ ሊቅና ቀልደኛው አለቃ ገብረ ሐና ታሪክ የሚገልጽ መጽሐፍ በአውስትራሊያ ታተመ፡፡

‹‹ሊቁ አለቃ ገብረ ሐና ከ፲፰፻፲፬-፲፰፻፺፰ ..›› የሚል ርእስ ያለውን መጽሐፍ ያዘጋጁት አቶ መሰለ ለማ ሀብተ ወልድ ናቸው፡፡ ደራሲው ከአውስትራሊያ ኲዊንስ ላንድ ብርስመን ከተማ ለሪፖርተር በቴሌፎን እንደተናገሩት፣ መጽሐፉ የአለቃ ገብረ ሐናን ሙሉ ታሪክ፣ 80 የአነጋገር ለዛና ቀልዶቻቸውን አካትቶ የቀረበበት ነው፡፡

ባለፉት ስምንት ዓመታት በእንግሊዝና በፈረንሣይ በሚገኙ ታላላቅ አብያተ መጻሕፍትን ጨምሮ በሌሎችም ተቋማት በአለቃ ገብረ ሐና ዙርያ ጥናት ማድረጋቸውንም ደራሲው ገልጸዋል፡፡

‹‹ከተሞች ውስጥ የሚሞተው ሁልጊዜ ይታወሳል ገጠሮች ላይ የሚሞተው ይጠፋል››

 
በ 24 03 2004 ዓ.ም. ሪፓርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ
ከሰባ ስድስት ዓመት በፊት የተፈጸመው የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ብዙ መከራዎችን ትቶ ማለፉ አይዘነጋም፤ እርመኛ አርበኞች የአገሪቱን ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ የብዙ ደራስያንን፣ ጸሐፍትን ቀልብ መግዛቱም አልቀረም፡፡

የፋሽስት ወንጀለኞች የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት፣ በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዝ ያደረሱትን እልቂት ትኩረት ሰጥተው ከጻፉት ደራስያን መካከል የተሰለፉት አንዱ አቶ ጥላሁን ጣሰው ናቸው፡፡ ይህንኑ የፋሺስት ክሥተት፣ የአርበኞችና የሕዝቡን ተጋድሎ የሚያወሳ ታሪካዊ ልብ ወለድ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጽፈዋል፡፡