በ 17 03 2004 ዓ.ም. ሪፓርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ
መሰንበቻውን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል አዲስ አበባ አስተናግዳ ነበር፡፡ በተለያዩ የፊልም ዘውጎች ላቅ ያለ ተግባር ያከናወኑ በአዘጋጆቹ መስፈርት መሠረት ለስኬት የበቁ ፊልሞችና ጓዞቻቸው ለሽልማት በቅተዋል፡፡ ተሳትፎው ምልዐት ባይኖረውም ፌስቲቫሉ ዓመቱን ጠብቆ መከናወኑ ይበል ይበል ያሰኛል፡፡
ስለፌስቲቫሉ ሒደት የፊልም ዳይሬክተሩና ምሁሩ ብርሃኑ ሽብሩን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አነጋግሮ ነበር፡፡ የፊልም ባለሙያው አቶ ብርሃኑ፣ በአገሪቱ የፊልም ጉዞ ያስገረማቸውን ነገር ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ፊልማቸው አማርኛ ሆኖ ርእሳቸው ‹‹እንግሊዝኛ›› የሆኑ ፊልሞች ነገር እንዴት ነው ነገሩ? አሰኝቷቸዋል፡፡
እንዴት ነው ነገሩ?
‹‹ሹገር ዳዲ››፣ ‹‹ሲቲ ቦይስ››፣ ‹‹ኮመን ኮርስ››፣ ‹‹ቴክ ኢት ኢዚ››፣ ወዘተ. እያልን ብንደረድር በርካታ ፊልሞች ርእሳቸውን ከባዕድ አፍ ነስተው እናገኛቸዋለን፡፡
እንዴት ነው ነገሩ?
የፊልም ዳይሬክተሩ እንዳሉት፣ የጣሊያን ፊልሞች በጣሊያንኛ ሆነው ርእሳቸውን ጣሊያንኛ እንጂ እንግሊዝኛ አያደርጉም፡፡ ሌሎችም ቋንቋዎች እንዲሁ፡፡ የኛ ፊልም ደራሲዎች ምን ነካቸው? ብለውም ይጠይቃሉ፡፡
እንዴት ነው ነገሩ?
የፊልም ደራሲዎቻችን ከማን ይማሩ?
‹‹አባቱን አያውቅ አያቱን ናፈቀ›› የሚለውን ብሂል የዕለት ቁርሳቸው፣ የዓመት ጉርሳቸው ያደረጉት እነርሱ ብቻ አይደሉም፡፡ ‹‹ሳይቸግር ጤፍ ብድር›› ሆኖ በየመንግሥታዊም ሆነ ግላዊ ተቋማት የስያሜና የትርጉም ቃላት መች ለከት አገኘ?
ዘርፍ እያለ ‹‹ሴክተር››፣ መምርያ እያለ ‹‹ዳይሬክቶሬት›› ወዘተ. እየተባለ መጠራቱስ እንዴት ነው ነገሩ?
በቋንቋ ውሰት ቢኖርም እንዳለ ሁሉን እየገለበጡ መቀጠሉ ለቋንቋው፣ ለባህሉ፣ ለቅርሱ እየሰጠን ያለነውን ቦታ የሚያሳይ ነው፡፡ አማርኛ ሳይሆኑ ‹‹አማርዝኛ›› (የእንግሊዝኛ አማርኛ) የሆኑ፣ እየሆኑ ያሉ የትየለሌ ናቸው፡፡ ‹‹take the chair›› የሚለውን ‹‹አረፍ በል›› ከማለት ይልቅ ‹‹ወንበር ውሰድ›› እንደተባለው፣ ‹‹Core Process Owner›› የሚለውን ሐረግ ‹‹ዋና የሥራ ሒደት ባለቤት›› ብሎ መመለሱ አማርኛ ነው? ወይስ አማርዝኛ? እንዴት ነው ነገሩ?
የበጎ አድራጎትና ማኅበራት ምዝገባ ጽ/ቤት መጠርያ ስማቸውን በሁለት ቋንቋ አማርኛና እንግሊዝኛ ያደረጉ ‹‹ስም አይተረጐምም›› በሚል ፈሊጥ አንዱን ምረጡ በማለቱ የአብዛኞቹ መጠርያ አማርዝኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?
በጽ/ቤቱ አካሔድ ከሆነ እንደ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ዓይነቱ ታዲያ ለምን ኮሜርሻል ባንክ ኦፍ ኢትዮጵያ አልተባለም? ከሁለቱ አንዱን እንዲመርጡና እንዲሔዱስ አልተደረገ? ‹‹ግማሽ ጎፈሬ! ግማሽ ልጩ›› ሆነሳ፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?
እንደሚወራው ማንም ተቋም በፈለገው መልኩ ስያሜውን ማቅረብ ይችላል የተባለው እውነት ከሆነ፣ ነገሮች ሁሉ ለመዘባረቃቸው ማን ተጠያቂ ሊሆን ነው?
ለዚሁ ክፍተት መንስኤው አገሪቷ እስካሁን የቋንቋ ፖሊሲ ባለቤት አለመሆኗ ነው፡፡ ሁለት አሠርት ቢቁጠርም በየዓመቱ እየተንከባለለ ነወ፡፡ ጉዳዩ የሚመለከተው ሚኒስቴር እያዘጋጀሁ ነው እያለ ነው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?
የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የአገሪቱ ይፋ ቋንቋ፣ በመርሐ ልሳኑ (አካዴሚ) አማካይነት መድበለ ቃላቱ ባዕድ ወረር እንዳይሆን ያወጣው ዓይነት መመርያ ዓይነት እስካሁን በዘመናችን አለመውጣቱስ እንዴት ነው ነገሩ?
ኢትዮጵያ ሁለተኛ ዓመቱን ያስቆጠረው አገራዊ እቅዷን ‹‹Growth and Transformation Plan›› ብላ ወደ አማርኛ ‹‹ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ›› ብላ የመለሰችው አማርኛ ነው? ወይስ አማርዝኛ? እንዴት ነው ነገሩ?
ለ‹‹ትራንስፎርሜሽን›› ተተኪ ቃል ጠፍቶ ነው ቃሉ እንዳለ የተገለበጠው? እንዴት ነው ነገሩ?
እና የፊልም ደራሲዎቻችን ፊልማቸው በአማርኛ፣ ርእሳቸው በእንግሊዝኛ ማድረጋቸው ከማን ተምረው ነው? ከግብር አባቶቻቸውስ አይደለምን?
ለቋንቋዎቻችንና ለባህሎቻቸው የአምስቱ ዓመት እቅድ የሚለው አንዳች ነገር አለ ወይ? እንዴት ነው ነገሩ?
ዓይን እቅርቡ ቅንድብ እያለለት አለማየቱስ አይሆንምን? እንዴት ነው ነገሩ?
No comments:
Post a Comment