Sunday, November 27, 2011

‹‹ታሪክን እጠብቃለሁ፤ ግን ሌላ ዓይን እንክፈት››


                                                       በ 10 03 2004 ዓ.ም. ሪፓርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ

‹‹እናትነት ያልሆነ ምን አለ? የቆምንበት ሁሉ እናት ነው፡፡ የተፈጥሮም ሆነ የሰው ልጅ ማሕፀን እናትነትን ያሠርፃል፣ ያወጣል፤›› የሚለውን ኃይለ ቃል ያስተጋባው ሠዓሊውና ካርቱኒስቱ ኤልያስ አረዳ ነው፡፡
ባለፈው ረቡዕ ቦሌ አካባቢ በሚገኘው በማኩሽ አርት ጋለሪ ለሦስት ቀን የቆየውን ‹‹እናትነት›› የተሰኘውን የሥዕል ዐውደ ርዕይ ባሳየበት ወቅት በአንዱ ሥዕሉ፣ ከመሬት ውስጥ እየወጣች ያለች እንስትን አስመልክቶ የገለጸልን ነው፡፡ ከሠላሳ ሥዕሎቹ ከዘጠና እጅ በላይ በሴቶች ገጽታ ላይ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ የሁሉንም ሥዕሎች አርእስት ‹‹እናትነት›› ብሎታል፡፡

ሥዕሎቹ ከባህልና ታሪክ፣ ቅርስና ማንነትን፣ አካባቢና ፍትሕ የተቀዱ ናቸው፡፡ እነርሱኑ ከእናትነት ጋር አወራርሶ አቅርቦታል፡፡

ከማን ይማሩ?

                                      በ 17 03 2004 ዓ.ም. ሪፓርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ


መሰንበቻውን ስድስተኛው የኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ፊልም ፌስቲቫል አዲስ አበባ አስተናግዳ ነበር፡፡ በተለያዩ የፊልም ዘውጎች ላቅ ያለ ተግባር ያከናወኑ በአዘጋጆቹ መስፈርት መሠረት ለስኬት የበቁ ፊልሞችና ጓዞቻቸው ለሽልማት በቅተዋል፡፡ ተሳትፎው ምልዐት ባይኖረውም ፌስቲቫሉ ዓመቱን ጠብቆ መከናወኑ ይበል ይበል ያሰኛል፡፡
ስለፌስቲቫሉ ሒደት የፊልም ዳይሬክተሩና ምሁሩ ብርሃኑ ሽብሩን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አነጋግሮ ነበር፡፡ የፊልም ባለሙያው አቶ ብርሃኑ፣ በአገሪቱ የፊልም ጉዞ ያስገረማቸውን ነገር ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ፊልማቸው አማርኛ ሆኖ ርእሳቸው ‹‹እንግሊዝኛ›› የሆኑ ፊልሞች ነገር እንዴት ነው ነገሩ? አሰኝቷቸዋል፡፡
እንዴት ነው ነገሩ?

Friday, November 25, 2011

ትውስታ በሙዚየም ቀን


‹‹ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› እስከ ‹‹ሕዳሴ››
       በግንቦት 14 2003 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የወጣ
ግንቦት 10 ቀን 2003 .. የዋለው የዘንድሮውን የዓለም ሙዚየም ቀን፣ ሸዋንና ጎጃምን ከሚያዋስነው በታሪካዊው የዓባይ ወንዝ  ከዱሮውና ከአዲሱ ድልድይ በመገኘት ለማክበር ያመራነው፣ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም አዘጋጅነት ነው፡፡

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሥር በሚገኘው ብሔራዊ ሙዚየሙ (የቅርስ ልማት ዳይሬክቶሬት) ለዘጠነኛ ጊዜ ዕለቱን ለማሰብ የመረጠው ሥፍራ ከተመረቀ ሦስተኛ ዓመቱን እያገባደደ ባለው የዓባዩ ‹‹ሕዳሴ ድልድይ›› ነበር፡፡
በዓለም ደረጃም 34 ጊዜ የተከበረው የሙዚየም ቀን መሪ ቃሉ ‹‹ሙዚየም እና ትውስታ›› በሚል ነው፡፡ በዩኔስኮ ሥር ባለው ዓለም አቀፉ የሙዚየሞች ምክር ቤት (አይኮም) አገላለጽ ሙዚየሞች ትውስታዎችን ይጠብቃሉ፤ ታሪኮችንም ይናገራሉ፡፡ በስብስባቸውም በርካታ ቁሶችንና ነገሮችን በመያዛቸው በዋናነት የማኅበረሰቦች ትውስታዎች ይሆናሉ፡፡ 

የቅርስ ልማት ዳይሬክቶሬት በዋዜማው የበዓሉን ታሪካዊነት የሚያጎላ ዐቢይ ክንውን የፈጸመበት ዕለት ነበር፡፡

በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት (1881 – 1906 ..) ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት መኪናዎች አንዷ የኾነችውን መኪና ብሔራዊ ሙዚየሙ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን መረከቡ ነበር፡፡

በመሪ ቃሉ መሠረት በተደረገው ሲምፖዚየም ከትውስታ መገለጫ መካከል አንዱ ስለሆነው ሐውልት ተሳታፊዎችን አነጋግሮ ነበር፡፡ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ታሪካዊ መገለጫ ያላቸው ሐውልቶች የመኖራቸውን ያህል ተገቢ እንክብካቤ ያላገኙ፣ ባለፈው መንግሥታዊ ሥርዓት የፈረሱ፣ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት መገለጫ የነበሩት በሙዚየሙ ግቢ ውስጥ የሚገኙ ሐውልቶች ዳግም የሚነሡበት ዕድል እንዲፈጠር ያሳሰቡ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ በፋሺስት ኢጣሊያ ወራሪ ላይ የተቀዳጀቻቸውን አኩሪ ድል ሊያስታውሱ የሚችሉ የታላላቅ አርበኞች ፎቶ ግራፎች በብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ ለእይታ መብቃት አለባቸው ያሉት ጄኔራል ዋሲሁን ንጋቱ ናቸው፡፡ ፎቷቸው መግባት አለበት በማለት በምሳሌነት ያነሧቸው የነራስ አበበ አረጋይ፣ አቡነ ጴጥሮስ፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ወይዘሮ ሸዋረገድ ገድሌን ነበር፡፡ 

‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› እና ‹‹ሕዳሴ››
ረቡዕ ግንቦት 10 ቀን ጎሕ ሲቀድ የዘንድሮው የሙዚየም ቀን ወደሚከበርበት ሸዋንና ጎጃምን ወደሚያዋስነው የዓባይ መሻገሪያ ሁለት ድልድዮች ለማምራት መነሻው ወደኾነው ብሔራዊ ሙዚየም ዘለቅሁ፡፡ ትውስታ ነው፡፡ እኔም በትውስታ ተጓዝኩ፡፡ 1920ዎቹ መገባደጃ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የጦር ሚኒስትር በነበሩት ራስ ሙሉጌታ ስም ከተሰየመው ራስ ሙሉጊታ ሰፈር ተነሥቼ፣ በራስ ሙሉጌታ መንገድ ካዛንቺስ ቶታል ደርሼ፣ በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ መንገድ፣ በዳግማዊ ምኒልክ ቤተመንግሥት (ታላቁ ቤተመንግሥት) አድርጌ የአምስቱ ዘመን ተጋድሎና ድል መታሰቢያ በኾነውና ዘንድሮ 70 ዓመቱ በተከበረበት ሚያዝያ 27 አደባባይ በኩል ብሔራዊ ሙዚየም ደረስሁ፡፡

ያቺ የዘመነ ምኒልክ መኪና በክብር የቆመችበት ሥፍራ በሙዚየሙ ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኘው የዱሮ ሕንፃ ደጃፍ ላይ ነው፡፡ ሕንፃው በፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ጊዜ 1928 .. መገንባቱና በወቅቱ ከፋሺስት ኢጣሊያ የጦር መሪዎች አንዱ ለሆነውና አዲስ አበባን ሲያስተዳድር ለነበረው መኖርያ ቤት እንዲሆን የተሠራ ነበር፡፡ ሙዚየሙ ካሰራጨው በራሪ ጽሑፍ እንደተጠቀሰው፣ ድኅረ ፋሺስት ሕንፃው ለልዑል መኰንን ኃይለ ሥላሴ መኖርያነት ካገለገለ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ነበርበት፡፡

በመካነ ሙዚየሙ አፀድ ውስጥ ቆመውና ወድቀው ካሉት ታሪካዊ ሐውልቶች መካከል በሸራ የተሸነፈው በኢትዮጵያ ሀገር ፍቅር ማኅበር (የአሁኑ የሀገር ፍቅር ቴአትር) ግቢ ውስጥ ቆሞ የነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የተማሪዎች ሐውልት ከነ ጉስቁልናው ይታያል፡፡ ከግርጌውም የንጉሡንና የልዑላኑ ሸርፍራፊ ሐውልቶች ከተለያዩ ቦታዎች ተለቅመው የመጡ ይታያሉ፡፡

በቀድሞው የልዕልት ፀሐይ ሆስፒታል (የአሁኑ ጦር ኃይሎች) ግቢ የነበረው የልዕልት ፀሐይ (ነርስ) ሐውልት እጁ እንደተሰበረ ከሙዚየሙ ፊት ለፊት ቆሟል፡፡ 

በቀድሞው የልዑል መኰንን ሆስፒታል (የአሁኑ ጥቁር አንበሳ) ቆሞ የነበረው የልዑሉ ሐውልት ከነሙሉ ክብሩ እንዳለ ይታያል፡፡ እነዚህንና ሌሎቹን የነገሥታቱን ዘመን የሚያስታውሱ ሐውልቶች ተገቢው ክብር ሊሰጣቸው ይገባል በማለት በዋዜማው ሲምፖዚየም አስተያየታቸውን ከሰጡባቸው መካከል ይገኙባቸዋል፡፡ 

ከሙዚየሙ ወደ ዓባይ ድልድይ ጉዞው የተጀመረው በንጉሥ ጆርጅ 6 መንገድ ወደ ስድስት ኪሎ በማምራት ነው፡፡ በፋሺስት ኢጣሊያ የካቲት 12 ቀን 1929 .. ለተጨፈጨፉት ኢትዮጵያውያን መታሰቢያ  በቆመው የሰማዕታት ሐውልትና ‹‹የካቲት ፲፪ አደባባይ››በኩል በአፍንጮ በር አድርጎ ማምራቱን ቀጠልን፡፡

ከአዲስ አበባ 208 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙትና ሸዋንና ጎጃምን (ሰሜን ምዕራብ ሸዋንና ምሥራቅ ጎጃምን) ከሚያዋስኑት ከታላቁ የዓባይ ወንዝ ሁለት ድልድዮች ዘንድ በመጓዝ የሙዚየምን ቀን ለማክበር ቻልን፡፡

ሁለቱ ድልድዮች ታሪካውያን ናቸው፡፡ የመጀመርያው ድልድይ ‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድልድይ›› ሲሰኝ፣ በድልድዩ ላይ በእምነበረድ የተጻፈው ጽሑፍ ታሪካዊነቱን እንዲህ ይገልጸዋል፡፡

ቀዳማዊ፡ ኃይለ፡ ሥላሴ፡
ድልድይ
ይህ ድልድይ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፈቃድና ትእዛዝ 17ተኛው ዘመነ መንግሥታቸው 1939 .. በዐባይ ወንዝ ላይ ተመሠረተ፡፡ ግርማዊነታቸው ከባሕር ማዶ ተመልሶ ኢትዮጵያን ነፃ ለማውጣት ጠላቶቻችንን ኢጣሊያኖችን በወጋቸው ጊዜ እነርሱን እያባረረ የሰላም ጐዳና ከሆነው ከጐጃም ላይ ደረሰ፡፡ ከዚህም በኋላ በሚያዝያ 20 ቀን 1933 .. በድል አድራጊነት ግርማ ይህን ወንዝ ተሻገረው፤ አሁንም ለሀገር ልማት ለሕዝብ ጥቅም የሚያገለግለው ይህ ድልድይ እዲሠራበት አደረገ፡፡ ይኸውም ለስም መታሰቢያ የታሪክ ማስታወሻ ሆኖ በኋላ ዘመን ለመጪው ትውልድ ምስክር ይሆን ዘንድ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድልድይ ተባለ፡፡

ጥር 21 ቀን 1939 ..
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ድልድይ በተመሠረተ 62 ዓመቱ፣ በሦስተኛው ሺሕ (ሚሌኒየም) መባቻ፣ 2001 .. ‹‹ሕዳሴ›› የተሰኘው ሁለተኛው ድልድይ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ተመረቀ፡፡
እንዲህም ተጽፎበታል፡፡
‹‹ኅዳሴ ድልድይ በጃፓንና በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መካከል ያለውን ወዳጅነት እና ትብብር ለማጠናከር በጃፓን ሕዝብና መንግሥት እርዳታ የተሠራ፤ 2001፡፡

በሕዳሴው ድልድይ ዳርቻ ላይ ‹‹የኢትዮጵያ ሚሌኒየም 2000›› - ከሚያመላክተው የቁጥር ሰሌዳ አቅራቢያ ለተገኙት የአዲስ አበባ የበዓሉ ታዳሚዎች በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የቅርስ ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሯ / ማሚቱ ይልማ (በቀድሞው አጠራር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም ሥራ አስኪያጅ) ባደረጉት ንግግር፣ ሙዚየምና ትውስታን ከአገሪቱ ታሪክና ባህል ጋር በማስተሳሰር ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ 

‹‹ታሪካችንንና ባህላችንን ጠብቀን ስለአገራችን ባህልና ታሪክ አውቀን፣ በማንነታችን የምንኮራ ትውልዶች እንድንሆን ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ይህ ትውስታ ያለፉት አባቶች የሠሩትን፣ የዛሬው ትውልድ የሚሠራውንና ለሚቀጥለው ትውልድ የምናስተላልፍበት ነው፡፡››

ከዳይሬክተሯ ንግግር በፊት የመሥርያ ቤታቸው የቅርስ ባልደረቦች በአኮርዲዮን በታጀበ ሙዚቃ ዓባይን የማወደሱ፣ ለሕዳሴው ግድብ ስኬት ይበልጥ እንደሚተጉ የሚያመላክት ጭፈራም ተስተውሏል፡፡

አቶ መንክር ቢተው ካሰሙት ግጥም የተገኘው አንዱ አንጓ የሚከተለው ነበር፡፡
‹‹አለው የደስ ደስ
አለው የደስ ደስ
ስደት ይበቃል ብሎ
ዓባይ ወደ ሀገር ሲመለስ
ፈሰሰ እንደ ጅረቱ ድርሳነ ግዮን መወድስ
ገሐድ አስተርአየት ኢትዮጵያ ስትታደስ››

ዓባይን ከመንቶቹ ድልድይ ሆኜ እያፈራረቅሁ ሳየው፣ ወደ ትውስታ ጓዳ የወሰደኝ ወደ ስመ ጥሩ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁ ‹‹ፍቅር እስከ መቃብር›› ልብወለድ ድርሰት ነው፡፡ ሰብለ ወንጌል እና በዛብህ፣ ጉዱ ካሳም ከፌቴ ድቅን አሉብኝ፡፡ ‹‹አባ ዓለም ለምኔ›› ኾና ዓባይን ተሻግራ ከአዲስ አበባ 186 ኪሎ ሜትር ላይ ከምትገኘው ጎሐ ጽዮን የደረሰችው ሰብለወንጌል ከበዛብህና ጉዱ ካሳ ጋር የተገናኘችበት ግጥምጥሞሽ የፍቅር እስከ መቃብርን ገጽታ አመላክቶኛል፡፡

በተንጣለለው የአዲስ አበባ ባሕር ዳር አውራ ጎዳና መሐል የሚገኘው የዓባይ ድልድይ እንዲህ ቀልጠፍ ተብሎ ከመደረሱ በፊት ዱሮ፣ ያኔ በጥንት ስለነበረው የመንገዱ ገጽታ ‹‹ከፍቅር እስከ መቃብር›› መጽሐፍ የተሻለ የሚገልጸው ያለ አይመስልም፡፡

‹‹ዓባይ ለቆላው የመኪና መንገድ፣ ለወንዙ ድልድይ ሳይሠራለት፣ ከጎጃም ወደአዲስ አበባ ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም የሚሔድ መንገደኛ ሁሉ ጎሐ ጽዮን ወይም ደጀን እስኪደርስ ድረስ ልክ የመከራ ትንቢት እንደተነገረበት ሰው፣ ካሁን አሁን መከራው ደረሰብኝ ብሎ ልቡ እየፈራና እየራደ የሚያልፍበት ቦታ ነበር!››
ጉዞው እየተገባደደ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ መመለስ ጀምረናል፡፡ ከዓባይ ፍቼ ስንደርስ የታወሱኝ ከዳግማዊ ምኒልክ በኋላ የዘውዱን መንበር የተረከቡት ልጅ ኢያሱ ናቸው፡፡ ፍቼ ሥልጣናቸውን ካጡ በኋላ የተጋዙበት ሥፍራ ናት፡፡
‹‹የበላሁት ጮማ የጠጣሁት ጠጅ ሆዴን ቆረጠው
እንደምን አድርጌ ተፍቼ ላውጣው››
ብለው ሹመኛቸው የነበሩት ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ የገጠሙት ሰምና ወርቅ ፍቼ ስደርስ ታወሰኝ፡፡ ነጋድራስ ተሰማም ወደጂማም ተግዘው ስለነበር፣ 
‹‹ጠጅም አልጠጣን ከተለየናችሁ 
አውራው ከተያዘ  ማሩን እባካችሁ››
የሚለውም ‹‹ሙዚየምና ትውስታ›› በተሰኘው የዘንድሮ በዓል ክሡት ኾነልኝ፡፡ ሰላሌ ፍቼ የሰማዕቱ አርበኛ ሊቀጳጳስ አቡነ ጴጥሮስም መሠረት ናት፡፡ 

ትውስታ ማለቂያ የለውም፡፡ የሙዚየም ቀን ትውስታን ባለቅኔው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን 40 ፈሪ (39) ዓመታት በፊት፣ ‹‹ዓባይ›› ብለው በተቀኙትና መታሰቢያነቱን ከጎጃም ዓባይን ተሻግረው አዲስ አበባ ለዘለቁት የኢትዮጵያ ፊደል፣ የካምና አፍሪካዊነት አቀንቃኝ ለነበሩት የኔታ አስረስ የኔሰው ካደረጉት ሥነ ግጥም አንዱን አንጓ ለማሳረጊያ እነሆ፡፡
ጥቁር ዓባይ የጥቁር ምንጭ
የካም የሥልጣኔ ፍንጭ
የቅድመ ታሪክሽ ጥርጊያ
ከደም-ቢያ እስከ -ቢያ
የኢትዮጲስ ደም የኩሽ እናት
ዓባይ የጥቁር ዘር ብሥራት
የዓለም ሥልጣኔ ምስማክ
ከጣና በር እስከ ካርናክ
በጡትሽ እቅፍ እንዲላክ
ለራህ ለፀሐዩ ግማድ፣ ለጣህ ለከዋክብት አምላክ
ከጥንተ-ፍጡራን ጮራ፣ የመነጨሽ ከኩሽ አብራክ፤
ሰሃራን እንደምሁር ተልም
ያለመለምሽ በወዝሽ ደም
የቅድመ-ጠቢባን አዋይ
ዓባይ የምድር ዓለም ሲሳይ፡፡